የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)         Ethiopian People's Revolutionary Party (EPRP) 

ሃገር የማዳን ጥሪ
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ገና ሲመሠረት ጀምሮ ኅብረብሄራዊ የሆነ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ ለሃገሪቱ የግዛት አንድነት የማያወላውል አቋም በማንገብ አሁን ድረስ ያኔ የተነሱትን መሠረታዊ የፖለቲካ አቋሞቹን በማጠንከር ትግሉን ቀጥሏል። ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ዋና ዋን አቋሞቹን በማንገብ ያለማወላወል ታግሏል፣ አታግሏልም።

  1. የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስከበር፣
  2. እኩልነት የሰፈነባትና ዜጎች በመፈቃቀድ አብረው የሚኖሩባት አገር መገንባት፣
  3. ሉዓላዊነቷን የጠበቀች ሀገር በሁሉም መስክ መገንባት፣
  4. ለሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ በቀዳሚነት በመታገል፣
  5. የመሬት ላራሹን ጥያቄ በማንሳት ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትኅ ጥያቄዎችን በማንሳት፣
    አሁንም እነዚህን አቋሞቹን አጠንክሮ በመያዝ፣ በሀገራችን ውስጥ የተፈጠረውን ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ተጠቅሞ ትግሉን በሰላማዊ መንገድ ቀጥሏል። ነገር ግን ይህ አዲስ የተፈጠረው ተስፋ ሰጪ ሁኔታ እየደበዘዘ መሄዱንም አስተውሏል። በተለያየ መልክ ይህን የመደብዘዝ ሁኔታ ለመንግሥትና ለሰፊው ሕዝብ በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎችና ቃለ መጠይቆች አመላክቷል። ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል ሁኔታውን ተገንዝቦ የሕግ የበላይነትን በማስከበር እርምት በመውሰድ ፈንታ በትዕግሥት ስም ዝም ብሎ ክቡር የሆነ የሰው ልጆች ሕይወት ሲጠፋና ንብረት ሲወድም ማየትን መርጧል።
    ይህ አካሄድ ግን ሕዝቧንና አገሪቱን ወደ ከፋ ሁኔታ እየወሰድ ነው። በአሁኑ ስዓት አገሪቱ ህልውናዋ አስጊ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል፣ ሕዝቡም ወደ አሰቃቂና ዘግናኝ ግድያ፣ መፈናቀል ገብቷል። ኢሕአፓ ይህንን ዘግናኝ ሁኔታ ዝም ብሎ የሚታለፍ ነው ብሎ አያምንም።
    ይህን ሁኔታ የፈጠሩት ኃይሎች ምን ዓይነት ኃይሎች መሆናቸው ለማንም ግልጽ ነው። አሁን ዋጋ እያሰከፈለን ያለው በ1981 ዓ. ም በህወሓት መሪነት ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በመሆን የፈጠሩት ሕገ መንግሥት ሥርዓት ውጤት ነው። እኒህ ኃይሎች አክራሪ ብሄርተኞች በሥጋና በደም ተዋህዶ፣ ለዓመታት ተዋዶ፣ ተከባብሮ በአንድነት የአገሪቱን
  6. Phone :0251944223216 e-mail: eprp@eprp-ihapa.com

ነፃነት አስከብሮ የኖረን ሕዝብ “እኛና እነሱ” እያሉ በመከፋፈል ደም የሚያፋስሱና የሚያቃቡ መሆናቸውን ልቦናውን ክፍቶ ለሚያይ ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም።
ይህ ለዓመታት ሲብላላ የነበረና ሰሞኑን ቁልጭ ብሎ የወጣው አስከፊና አስነዋሪ ሁኔታ አገራችንን ወደ መበታተን ሊያደርስ የሚችል አደጋ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ እታገላለሁ ለሚል አገር ወዳድ ሁሉ ይህ ሁኔታ ዝም ተብሎ የሚታይ አይደለም። ይህን ለማሰብ የሚሰቀጥጥ አስከፊ ሁኔታን በቆራጥነት ከመታገል ሌላ አማራጭ የለም። ትግሉ ደግሞ የአንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት ኃላፊነት ብቻ አይደለም።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሁሉንም አገር ወዳድ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎችና ወኪሎች፣ የሙያ ማኅበራት ተጠሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሕግ አዋቂዎች፣ የሀገር አዛውንቶች በሙሉ በአንድነት ቁመው ይህን የሃገሪቱን አንድነትና የሕዝቧን ሉዓላዊነት በማፍረስ የተሰማራውን ኃይል እንዲታገሉት ጥሪ ያቀርባል።
ይህ የትብብር ጥሪ የቁርጥ ቀን ጥሪ ነው። ከላይ የተዘረዘሩት አካላት ሁሉ በአንድ ላይ መክረው መንግሥት ሕግን እንዲያስከብር፣ አጥፊዎችን ወደ ሕግ እንዲያቀርብ በትብብር መጠየቅ አለብን።
አሁን አገሪቱ ያለችበት አስጊ ሁኔታ ለነገ የማይባል ሁኔታ ነው። በትዕግሥትና በይሉኝታ ሊታለፍ የሚችል አይደለም። እኒህ በታኝ ኃይሎች በግልፅ ምንነታቸው ተነግሯቸው፣ ትዕግሥታችንም የተሟጠጠ መሆኑ ሊነገራቸው ይገባል።
ባለፉት አሥርተ-ዓመታት የነበረን ትዕግሥት ተሟጧል። አደብ መግዛት ከቻሉ መልካም፣ ምሬታችን አልገባ ብሏቸው የተጠናወታቸው አባዜ አለቅ ካላቸው ግን ሕዝባችንን አስተባብረን የሃገራችንን አንድነት ለመጠበቅና የሕዝባችንን ሰላም ለማስከበር መነሳታችንን እንዲያውቁት እንፈልጋለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ኅብረትና አንድነት ለዘላለም ትኑር ! እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ !

ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ. ም