ማይክሮፎን

በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁን ሰዓት በተለያዩ ቋንቋዎች ፕሮግራማቸውን የሚያሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይገኛሉ። እነዚህ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ያስተላልፋሉ።

ሁሉም የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የሚያመሳስላቸው ነገሮች ይላሉ ዝግጅቶቹን የሚታደሙ አስተያየት ሰጪዎች፤ ውይይታቸውን የሚያካሂዱት ከአንድ ሰው ወይንም ተመሳሳይ ሀሳብ ካላቸው ሁለትና ከዚያ በላይ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ነው።

መስፍን ነጋሽ በጋዜጠኝነት ለረዥም ዓመታት ሰርቷል። ለመስፍን ውይይቶች መብዛታቸው መልካም ነው “ነገር ግን ይላል ተናጋሪዎቹ መገናኛ ብዙኀን ይቀይራሉ እንጂ ተመሳሳይ ሰዎች ናቸው” በማለት በርከት ያሉ ተወያዮችን ከተለያዩ የሕይወት ልምድና አውድ በማምጣት ማሳተፍ እንዳለባቸው ይገልፃል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጋዜጠኞች ተስፋ

አቶ ቀጀላ ቀና በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ውስጥ በኃላፊነት አገልግለዋል፤ በጋዜጠኝነትም ቢሆን ረዥም ዓመት ሰርተዋል።

አቶ ቀጀላ፤ አሁን በአገሪቱ ውስጥ ለተፈጠረው አለመረጋጋት ወይንም የሠላም መደፍረስ የመገናኛ ብዙኀን ምክንያት ባይሆኑም “ጉዳዩን በማራገብ ግን አባብሰውታል” ይላሉ።

አክለውም አገሪቱ ላለችበት ሁኔታ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም “መገናኛ ብዙኀን ግን ችግሩ እንዲፈታ ሳይሆን ችግሩ እንዲባባስ የሚያደርጉ ናቸው” ይላሉ።

ጋዜጠኝነትን በማስተማርና በዘርፉ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በመጻፍ የሚታወቁት ብርሃኑ ኦላና (ዶ/ር)፤ የመገናኛ ብዙኀን የሚፈጥሩት ችግር በአንድ ጀንበር የሚፈጠር ሳይሆን፤ በትንሽ በትንሹ የሚዘግቡት ተከማችቶ ዛሬ የተደረሰበት ቦታ ላይ መደረሱን ይናገራሉ።

ብርሃኑ (ዶ/ር) እንደሚሉት አንዳንድ መገናኛ ብዙኀን “ትንሹን ነገር አግዝፈው ይዘግባሉ፤ ሌሎች ደግሞ ሕዝቦችን የሚከፋፍል ዘገባ ያቀርባሉ።”

አክለውም በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በጋዜጦች ላይ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ጫፍ ይዘው መዘገብ እንዲሁም ነገሮች እንዲባባሱ የሚያደርጉ ዘገባዎች ሲያቀርቡ መታዘባቸውን ይጠቅሳሉ።

ለመስፍን ስጋት የሚያጭረው ሌላው ነገር የፖለቲካ ውጥረት በሚኖርበት ወቅት የሚደረጉ ውይይቶች ሁኔታውን ተመልካቹ እንዲረዳ ከማድረግ ይልቅ፣ በዚያ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ያሉትን ተዋንያን እያመጡ በመሞገት ፈንታ “እሳቱ ላይ ነዳጅ የሚጨምሩ” ውይይቶች ሆኖ እንዳገኛቸው አልሸሸገም።

በእነዚህ የፖለቲካ ውይይቶች ላይ ተጋብዞ የሚመጣው ሰው የሚናገረውን ‘አሰስ ገሰስ’ ያለከልካይና ያለሞጋች ሀሳብ አውርቶ እንደሚሄድ ማስተዋሉንምና በውይይታቸው ላይ የተነሱ ሃሳቦች የሞገቱ የመገናኛ ብዙኀን ወይንም ጋዜጠኞች እንኳ ቢኖሩ አልፎ አልፎ መሆኑን ያስታውሳል።

ውይይቶች በሚቀርቡበት ወቅት ለአንዱ ሰው ጥሩ የሙግት መንገድ መስሎ የሚታየው ነገር ለሌላ ተመልካችና አድማጭ የሚያስቆጣ ሊሆን እንደሚችል የሚናገረው መስፍን፤ ዞሮ ዞሮ መለካት ያለበት ለአድማጭ ተመልካቹ ምን ሰጠሁ በሚለው መሆኑን ያመለክታል።

ሽመልስ ዐቢይ አሕመድን ያገኘ ‘ለት

“የትኛውም ዓይነት አቀራረብ ይሁን መጨረሻ ላይ አድማጩ ያገኘው የሰማው ነገር ምንድን ነው?” የሚለው መመዘን እንዳለበት በማብራራት፤ አሁን በመገናኛ ብዙኀን የሚደመጡት ውይይቶች በዚሁ ከቀጠሉና በሀገሪቱ የሚታየው ውጥረት በዚሁ ከቀጠለ፣ መገናኛ ብዙኀኑ አድማጭ ተመልካቾቻቸውን ከማሳወቅ፣ ሌላውን ወገን እንዲረዳ ከማድረግና በዚህ መስመር በማገልገል ፈንታ ወደ ጫፍ እንዲሄዱ የሚያደርግ ይሆናሉ ሲል ስጋቱን ይጠቅሳል።

ግጭትአዘጋገብ

አቶ ቀጀላ በበኩላቸው እንደ ሰርቢያና ሩዋንዳ ባሉ ሀገራት የዘር ጭፍጨፋ እንዲካሄድ ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት የመገናኛ ብዙኀን መሆናቸውን በማስታወስ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ጨምረውም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን በሀገሪቱ ሰላም እዲሰፍን የሚያደርጉ ዘገባዎችን በመስራት ረገድ የሚጠበቅባቸውን ያህል አልተወጡም ብለው ያምናሉ።

በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ባጋጠሙ ግጭቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ብዙዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ስለእነዚህ ግጭቶች በስፋት የሚዘግቡት ግን ከመንግሥት የመገናኛ ብዙኀን ይልቅ በግለሰቦች አልያም በአክቲቪስቶች የተቋቋሙት ሚዲያዎች ናቸው።

የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ከእንደዚህ ዓይነት ዘገባ ለምን እንደሚሸሹና በጉዳዩ ላይ የመንግሥት መግለጫን ብቻ ማስተላለፍ ለምን እንደሚመርጡ ሲናገር “ከአፈጣጠራቸው ጀምሮ የሚታይባቸው ችግር አሁንም ስላልተላቀቃቸው ነው” በማለት ያለውን ክፍተት መስፍን ይነቅሳል።

እነዚህ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ላይ የአመራር ለውጥ ቢደረግም ይላል መስፍን፤ በመሰረታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ባላቸው አስተሳሰብና አሰራር ለውጥ አለማምጣታቸውን እንደሚያስተውል ይናገራል።

ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣና ሬዲዮ

በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከዜና ጀምሮ ምንም ዓይነት ለውጥ አይታይም የሚለው መስፍን እንዲህ ያለውን የሚዲያዎች ዘገባ “ኃላፊነት የሚጎድለው ነው” ሲል ይተቸዋል።

“አገሪቱ ውስጥ የተከሰተን አንድ ትልቅ ክስተት እንዳልተከናወነ አድርጎ ማለፍ፤ ለዚያውም ከሕዝብ በሚሰበሰብ ግብር ለሚተዳደር ትልቅ የመገናኛ ብዙኀን ትልቅ ኃላፊነት የማጉደል ድክመት አድርጌ ነው የምመለከተው” ሲልም ያክላል።

መስፍን በእነዚህ የመገናኛ ብዙኀን ውስጥ የቦርድ አባል በመሆን የሚያገለግሉ ግለሰቦች በእያንዳንዱ ፕሮግራም ይዘት ላይ መግባት ባይጠበቅባቸውም በእንዲህ ዓይነት አገራዊ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ መስጠት፣ የራሳቸውን አጠር ያለ ግምገማ የሚሰጣቸው ቡድን በማቋቋም ምን እየተካሄደ መሆኑን የሚያስረዳቸው ቡድን ማቋቋም እንደሚገባቸውም ይመክራል።

አምነስቲ በቅርቡ የታሰሩ ጋዜጠኞች ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥትን ነቀፈ

በዓለም ላይ ያሉ ጋዜጠኞችም ሆኑ መገናኛ ብዙኀን ግጭቶች በሚከሰቱ ጊዜ ለመወሰን በሚያስቸግር መንታ መንገድ ላይ እንደሚወድቁ የሚናገረው መስፍን፤ እውነቱን እንዳለ ዘርግፎ መናገር ወይንም የተፈጠረውን በደምሳሳው የሚያሳይ ልጓም ያለው አቀራረብ መኖር አለበት የሚል መሆኑን ያብራራል።

መስፍን በግሉ ልጓም ያለው አቀራረብን አንደሚደግፍ በማስረዳት “በግጭት ወቅት የመገናኛ ብዙኀን ያዩትን የሰሙትን እንደወረደ ማቅረብ ሰብዓዊም አይደለም” ሲል ይከራከራል።

አክሎም እውነት ሁሉ አደባባይ ይሰጣ ማለት እንደ ህብረተሰብም አይጠቅምም ካለ በኋላ በግጭት ወቅቶች የሚሰሩ ዘገባዎች በተቻለ መጠን በውይይት መሰራት እንዳለባቸው ይመክራል። የግጭት ዘገባዎች የአንድ ሰው ብቻ አስተያየት እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እንደሚገባም ያብራራል።

ግጭቶች በሚኖሩ ወቅት በርካታ ሠራተኞች ያሏቸው የመገናኛ ብዙኀን የራሳቸውን ውስጣዊ የአሰራር ደንብ ቢያወጡ መልካም መሆኑንም ይመክራል።

መስፍን አክሎም ግጭት አዘጋገብ ላይ ቁርጥ ያለአቋም መያዝ አስቸጋሪ መሆኑን በማንሳት በጋዜጠኞቹ የግል አመለካከት፣ በልምድ ማነስ፣ ለጉዳዩ ከሚኖር ግለሰባዊና ስሜታዊ ቅርበት፣ የተነሳ ዘገባው አቀራረብ ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖ እደሚያሳርፍ ያብራራል።

“በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ተቀባይነት ማሳጣት የሚሹ ግጭቱን አባብሰውታል” ቢልለኔ ስዩም

ይህንን ተጽዕኖ ለመቀነስም የተለያዩ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ዘገባው ከመውጣቱ በፊት እንዲመለከቱት ማድረግ ሚዛኑን እንዳይስትና ዜናው ከወጣ በኋላ የሚያደርሰውን አሉታዊ ውጤት በመቀነስ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳለው ያነሳል።

የሚዲያ ሥራ ከሰላም ይልቅ ለግጭቶች እንደሚያደላ በጥናቶች ጭምር መረጋገጡን በማስታወስ “ይህ ተፈጥሯዊ ድክመት ሙያው እንዳለበት ማስታወስ ያስፈልጋል” ሲል ይመክራል።

የግጭቶችን ዘገባ በሚመለከት ይኽው የሙያው ተፈጥሯዊ ድክመት እየጎተተው እንደሆነ ሁሌም መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል ሲል ያስረዳል። ሙያውን አድጎ እንደጨረሰና ሁሉ ነገር በግልጽ እንደሚታወቅበት ሞያ መቁጠር የለብንም ሲል አጽንኦት ይሰጣል።

ጋዜጠኞች ነጻነት ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት አለብን ሲሉ መስማቱንም በማስታወስ። ኃላፊነት ተጠያቂነትን መያዙን በማንሳት በሚሰሩባቸው ተቋማት ውስጥ ተጠያቂነትን የሚያለማምዱ አካላት አሉ ወይ? የሚለውን ማየት እንደሚያስፈልግ መስፍን ይናገራል።

በተመሳሳይ መገናኛ ብዙኀን በነጻነት መዘገብ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው የሚናገሩት ብርሃኑ ኦላና (ዶ/ር) “ነጻነት ግን ነጻ መሆን አይደለም” ሲሉ ይናገራሉ።

“ነጻነት ከተጠያቂነት ጋር አብሮ ይሄዳል” በማለትም መገናኛ ብዙኀን ለመዘገብም ቢሆን ሀገር እንደሚያስፈልጋቸው በመጥቀስ ለሰላም መስራት እዳለባቸው ይናገራሉ።

በተጨማሪም ሐይማኖትንና ብሔርን የሚመለከቱ ጉዳዮችን መገናኛ ብዙኀን በሚዘግቡበት ወቅት በኃላፊነት ስሜት መስራት እንዳለባቸው ይመክራሉ።

አቶ ቀጀላም ቢሆኑ በብርሃኑ (ዶ/ር) ሀሳብ ይስማማሉ። ጋዜጠኞች የሚሰሩት ዘገባ አንድን ሕዝብ ወይንም ኃይማኖት የሚያንቋሽሽ ሌላውን ደግሞ ከፍ የሚያደርግ ነገር ሊሰሩ ስለሚችሉ በእንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ወቅት የተለየ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራሉ።

የመፍትሄ አማራጮች

ማህበረሰቡ መገናኛ ብዙኀን የሚሉት ነገር ሁሉ እውነት ነው ብሎ የመውሰድ አዝማሚያ በመኖሩ ሕዝቡ ሚዲያዎች ላይ ባዳበረው አመለካከት ላይ መስራት እንደሚገባም አቶ ቀጀላ ይጠቁማሉ።

በሌሎች አገራት ውስጥ ከዝቅተኛ የትምህርት ክፍል ጀምሮ ስለ ሚዲያ አዘጋገብ ትምህርት እንደሚሰጥ በመጥቀስም መገናኛ ብዙኀን ሲዘግቡ የሚጨምሩትና የሚቀንሱት እውነት መኖሩን ማሳወቅ እንደሚገባም ይመክራሉ።

ለዚህም ደግሞ ጋዜጠኝነትን በትምህረት ሥርዓቱ ውስጥ በማካተት ማስተማር ተመራጭ መሆኑንም ይናገራሉ።

እውነታውን መርምሮ የሚቀበል ማህበረሰብ ለመፍጠርም መገናኛ ብዙኀን መስራት እንደሚኖርባቸውም ይህንንም የሚሰሩ ሚዲያዎች መበረታታት እንዳለባቸውም ብርሃኑ ኦላና (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

የብሮድካስት ባለሰልጣን በእርግጥ መገናኛ ብዙኀን የሚያስተላልፉትን ፕሮግራሞች የመመከታል፣ የማስጠንቀቅ፣ የማሳሰብ ከሕግ ውጪ ሲሆኑ ደግሞ በሕግ እርምጃ የማስወሰድ ስልጣኑም ኃላፊነትም አለው የሚለው መስፍን “አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ሁሉንም ነገር ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ የምንፈታው አይመስለኝም” ሲል ያስረዳል።

የብሮድካስት ባለስልጣን “ቢችልና ቢያደርግ የምወደው” ይላል መሥፍን፤ የሚዲያ ተቋም ኃላፊዎችን በተለይ ደግሞ አዘጋጆችን በቋሚነት የሚያነጋግርበት መድረክ ቢኖረው ነው።

መስፍን አክሎም እነዚህ ባለሙያዎች ጋዜጠኞች፣ አዘጋጆች፣ የሚዲያ ባለቤቶች በራሳቸው ተነሳሽነት እየተገናኙ የሚነጋገሩበት ሲያስፈልግም የሚወቃቀሱበት መድረክ ቢፈጥሩ የሚዲያ ካውንስሉ፣ በቅርብ የተቋቋመው የአርታዒያን ማህበር አባላት እየተገናኙ አስተያየት መሰጣጠትና መወያየት ቢችሉ መልካም መሆኑን ያሰምርበታል።

“በመንግሥት መዋቅር ሥር ሆነውም ግጭቶችን የሚያባብሱ እንዳሉ እናውቃለን” ኢዜማ

አለዚያ ግን የመገናኛ ብዙኀኑ አሁን በያዙት አቀራረብና አዘጋገብ የሚታየውን የፖለቲካ መካረር የሚያንጸባርቁና የሚባብሱ ነው የሚሆኑት ሲል ያለውን ስጋት ያስቀምጣል።

የብሮድካስት ባለስልጣን አይን ያወጣና የተደጋገመ ጥፋት የፈጸሙ የሚዲያ ተቋማትን ጠርቶ ማነጋገር እንዳለበት በማስታወስም የሚዲያ ተቋማቱ፣ ጋዜጠኞቹና ባለሃብቶቹ ተመልካች እንዳለ እንዲረዱ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳል።

መገናኛ ብዙኀኑ የተቋቋሙበት ታሪካዊ፣ የገንዘብና ተቋማዊ ግንኙነቶች ለሚያንጸባርቁት ባህሪና ለዘገባቸው መልክና ልክ ተጽዕኖ እንዳለው የሚናገረው መስፍን እነዚህ ሚዲያዎች ያቋቋማቸውንና ገንዘብ የሚሰጣቸውን አካል ፍላጎት በሆነ መልኩ ማንጸባረቅ አለባቸው፤ በማለት የአዘጋገባቸውን ምንጭ መረዳት አስፈላጊ መሆኑን ያስታውሳል።

አንዳንዶቹ የመገናኛ ብዙኀን የሚኖሩለት ዓላማ አንድ የፖለቲካ መስመርን ማቀንቀን መሆኑን በማንሳት እነዚህን የሚዲያ ተቋማት በሕግ ብቻ መልክ ማስያዝ ፈታኝ እንደሚሆን ይልጻል።

አንድን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም መደገፍ ለአንድ ሚዲያ ተቋም ነውር አይደለም የሚለው መስፍን፤ ነገር ግን የሌሎችን ሀሳብና ርዕዮተ ዓለም ማስተናገድ ለአድማጮቻቸውም ለአገርም ይጠቅማል የሚለውን በውይይት ለማስረዳት መሞከር ተገቢ ነው ይላል።

የአንድ ብሔረሰብ መብትን ለማስከበር የቆመ ሚዲያ ቢኖር ችግር የለውም የሚለው መስፍን፤ ነገር ግን ከባለሙያና ባለቤቶቹ ጋር መነጋገር የሚያስፈልገው ይህንን ማድረግ የሚችሉት አገር በሚባል ማዕቀፍ ውስጥ በመሆኑ ያንን ለማፍረስ መሞከር በመጨረሻ የቆሙለትን ብሔርም እንደሚጎዳ ማሳየት ተገቢ ነው ሲል ይመክራል።

በተጨማሪም የተለያዩ ድምጾችን በዘገባዎቻቸው ውስጥ ባካተቱ ቁጥር ለሀገር እንደሚጠቅሙ መነጋገርና ማሳየት ተገቢ መሆኑን ማሳየት እንደሚያስፈልግ ያሰምርበታል።