November 7, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የሲዳማ የክልልነት አደረጃጀትን ተከትሎ የመራጮች ምዝገባ ሲካሄድ መዋሉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ የተጀመረውን የመራጮች ምዝገባ እና የህዝበ ውሳኔውን ሂደት አስምለክተው ማምሻውም መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔ 15 የማስተባበሪያ ማዕከላት የተቋቋሙ ሲሆን፥ በአንድ ማዕከል ከ2 እስከ 3 ወረዳዎች እንዲካተቱ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህ መሰረትም በ1 ሺህ 692 የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች፤ 6 ሺህ አስፈፃሚዎች ተመድበው ምዝገባው በዛሬው ዕለት መጀመሩን አስታውቀዋል።
የመራጮች ምዝገባ ከተያዘለት የጊዜ አቅድ አኳያ አንድ ቀን ዘግይቶ የጀመረ ቢሆንም፤ በሁሉም የምዝገባ ማዕከላት አስፈላጊ ቁሳቁስ እና ሁኔታዎችን በማመቻቸት ዛሬ ሲካሄድ መዋሉንም ነው ወይዘሪት ብርቱካን ያስታወቁት።
ሆኖም ብላቴ ዙሪያ ወረዳ ከዚህ ቀደም በቅርብ ጊዜ ግጭት ተከስቶበት የነበረ አንድ ቀበሌ፤ የመራጮች ምዝገባ ከሰዓት በኋላ እንደተጀመረ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል።
ከፀጥታ አኳያም በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች አስፈፃሚዎች ከመላካቸው አስቀድሞ የፀጥታ አካል በእቅድ እንዲሰማራ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን አክለውም፥ ከጥቅምት 25 እስከ 30 የቅስቀሳ ጊዜ እንዲሆን መፈቀዱን ተከትሎ የተለያዩ የቅስቀሳ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ቅስቀሳው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ያስታወቁ ሲሆን፥ በአንድ አካባቢ ብቻ ለቅስቀሳው ከተፈቀደው ወሰን አልፎ የመቀስቀስ አዝማሚያ ተስተውሎ እንዲቆም መደረጉንም ገልፀዋል።
ከቅስቀሳው ጋር ተያይዞ ወይዘሪት ብርቱካን፥ ህዝበ ውሳኔው የሁለት አማራጮች (የእንለይ እና እንቆይ) ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን በቅስቀሳው ወቅት በነባሩ ደቡብ ክልል እንቀጥል ለሚለው የጎጆ ቤት ምልክት ተወካይ እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት የተደረገ ቢሆንም፤ ጥያቄውን ከመሰረቱ ያቀረበው ሲዳማ ዞንም ሆነ የደቡብ ክልል ምክር ቤቶች በመሆናቸው፤ የቅስቀሳ ተወካይ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል።
በመሆኑም በራስ አስተዳደር ከደቡብ ክልል ለመውጣት አማራጭ አደርጎ የሚንቀሳቀሰው ወገን የሻፌታ ምልክት በቅስቀሳ ወቅት በስፋት መስተዋሉ የሚዛናዊነት ችግር አለመሆኑን አስታውቀዋል።
የምርጫ አስፈፃሚዎች ጋር ተያይዞም አስፈፃሚዎች ከየትኛውም የመንግሰት ባለስልጣናት መዋቅር በአሰራሩ መሰረት የሚፈቀድ ድጋፍ እንጂ አላስፈላጊ ግንኙነቶች በድጋፍ ሰጪውም ሆነ ተቀባዩ መካከል የተከለከለ መሆኑን እና በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ሶስት ሶስት የምርጫ አስፈፃሚዎች መሆኑን በመግለጽ፤ በምርጫ ጣቢያ ማዕከላት የአንድ ወገን መገለጫ የሆኑ አርማዎችን፣ አልባሳትን እና ሌሎች ምልክቶችን ተጠቅሞ መገኘት የተከለከለና በአስፈፃሚዎች የምርጫ ስነ ምግባር የሚያስቀጣ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የህዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጡ በሀገሪቱም ሆነ በክልሉ የመጀመሪያ በመሆኑ፤ በምርጫ አስፈፃሚዎች ስምሪት፣ በሎጂስቲክስ እና ሌሎች ዘርፎች የተነሱ ቅሬታዎችን ለማሻሻል እንደሚሰራም ገልፀዋል።
በሶዶ ለማ