November 11, 2019
https://radiodownloaddw-a.akamaihd.net/Events/dwelle/dira/mp3/amh/7FD6AAB3_2_dwdownload.mp3

ኢትዮጵያ፣ ከግጭት ግድያ ትወጣ ይሆን?

DW : ኢትዮጵያ የግጭት፣ግድያ፣የመፈናቀልን ጥፋት ዐመት ሸኝታ፣ ያዲስ ግጭት፣ግድያ መፈናቀል ዓመት መቀበል የፖለቲካ ሒደቷ አብነት ከመሰለ አምስት ዓመት አለፈ። እስከ መጋቢት 2010 ድረስ የነበረዉ ግጭት-ግድያ በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ወይም መንግሥት በሚያደራጃቸዉ ታጣቂዎችና የመንግስትን ጭቋኝ አገዛዝ በሚቃወመዉ ሕዝብ መካከል ሥለነበረ አነሰም በዛ አጥፊና ጠፊዉን መለየት፣ በዳዩን ማዉገዝ፣ለተበዳዩ መጮሕ አይገድም ነበር።

ኢትዮጵያን በጎሳዊ አስተዳደር ለ27 ዓመታት የገዘዉ ኢሕአዴግ የመሪዎች ለዉጥ ካደረገ ከመጋቢት 2010 ወዲሕ ግን ግጭት፣ግድያ፣መፈናቀል ጥፋት ዉድመቱ በአብዛኛዉ ጎሳንና ኃይማኖትን የተላበሰ ነዉ።

ከኢትዮ-ሶማሌ መስተድር አዋሳኝ ድንበር እስከ መሐል ኢትዮጵያ ቡራዩ፣ከደቡብ ጌዲኦ እስከ ሰሜን ምዕራብ ቅማንት፣ከምዕራብ ወለጋ እስከ ምስራቅ ሐረርጌ፣ ከሲዳማ እስከ ጉሙዝ፣ ሰሞኑን ደግሞ ከአዳማ (ናዝሬት) እስከ ዶዶላ በተደረጉ የጎሳና የኃይማኖት ግጭቶች ሺዎች አልቀዋል።ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል።የድሆች-ደሐይቱ ሐገር በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሐብት ንብረቷን ለእሳት ገብራለች።

ለወትሮዉ በአብዛኛዉ ሕዝብ ዘንድ የሚከበሩ ቤተ-እምነቶች ጋይተዋል፣ተመዝብረዋል፣ወድመዋልም። ሕግና ሥርዓት ማስከበር የሚገባዉ የመንግስት ፀጥታ አስከባሪ በተለይ ፖሊስ አንዳድ ስፍራ ግጭት-ግድያ ጥፋቶቹን አይቶ እንዳለየ ማለፉ ሲዘገብ፣ሌላ አካባቢ ደግሞ የፖሊስ አባላት ከየጎሳቸዉ አብረዉ የጥፋቱ አካላት መሆናቸዉ ይነገራል።

የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት ግጭት ጥፋቱ እንዳይነሳ ለመከላከል፣ ሲነሳ ፈጥኖ ለማብረድ፣ ጥፋቱ ከደረሰ በኋላ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ጠንካራ እርምጃ ለመዉሰድ ያመነታሉ ወይም ዳተኛ ናቸዉ የሚል ወቀሳ በተደጋጋሚ እየተሰነዘረ ነዉ። የግጭት፣ግድያ፣መፈናቀሉ ዑደት መቀጠሉ፣የጎሳና የሐይማኖቱ ጠብ መካረሩ፣የሥራ አጡ ወጣት ቁጥር ማየል፣በፀጥታ አስከባሪዉ መሐል ሳይቀር ጎሰኝነት መንፀባረቁ ከመንግስት ዳተኝነት ጋር ተዳምሮ፣ አንዳዶች ሟርት ቢሉም፣ ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ የመፍረስ አለያም እንደ ሩዋንዳ የመተላለልቅ ጥፋት እየተደገሰላት እንዳይሆን ብዙዎችን አስግቷል።