November 11, 2019
Source: https://www.zehabesha.com/amharic/archives/98400
2019-11-10 (እ.ኤ.አ)
ሰሞኑን የጃዋርን የድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ በአገራችን በልዩ ልዩ ቦታዎች በወገኖቻችን ላይ አሳዛኝ ክስተት ተፈጽሟል። ብዙ ህጻናት፣ አዛውንቶች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ የሃይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች ያለአግባብ በግፍ ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ ከቦታቸውም ተፈናቅለዋል፣ የእምነት ተቋማትም ተቃጥለዋል ወይም የመቃጠል ጥቃት ተሞክሮባቸዋል። ይህ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው አሳዛኝና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ባንድ ሰው የድረሱልኝ ጥሪ ባየነውና በሰማነው መጠን መከሰቱ ብዙዎችን አስደንግጧል፤ አስፈርቷልም። ከሰሞኑ እልቂት በፊትም ቢሆን በየጊዜው ተመሳሳይ የሆነ መከራ በሕዝባችን ላይ በተለያየ ጊዜና ቦታ በተደጋጋሚ ተከስቷል። ለነኚህ ሁሉ እልቂቶችና መከራዎች ባገራችን ባለፉት ሰላሳና አርባ አመታት ሲሰበክና ሲተገበር የነበረው በዜጎች መሃል መቃቃር እንዲኖር ተደርጎ የተሰራው የጥላቻና ከፋፋይ ፖለቲካ ያስከተለው መዘዝ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይሆንም። በወያኔ የበላይነት ዘመን በተለያዩ የሕዝብ ክፍሎች መሃል ግጭት መኖሩ ባይካድም አብዛኛዎቹ ግጭቶች ግን ከወያኔ ጋራ ከሚደረገው ትግል ጋራ በቀጥታ የተገናኙና በወያኔም ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ። በአሁኑ ሰዐት ግን የሚታዩት ግጭቶች ለብዙ አመታት ተዋልደውና ተዛምደው አብረው በኖሩ ወገኖቻችን መሃል መሆኑና፣ አንደኛው ዜጋ በሌላው የሚያደርሰው ጥቃት እየጨመረና ብዙ ደም መፋሰስ ማስከተሉም ነው እንደአገር የመቀጠሉን ሁኔታ ወደአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚያደርሰው።
ይህ አደገኛ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣቱ በፊት መንግሥት ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል፤ <<ሳይቃጠል በቅጠል>> እንደሚባለው። የጃዋርን ድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ የተፈጠረው የብዙ ንጹሃን ሞት፣ ጉዳትና ሃብት መውደም ዙሪያ እጃቸው አለበት የሚባሉትን ሁሉ መንግሥት በሕግ ፊት ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል። ለወደፊቱም ይህ አይነቱ ኢሰባዊ ድርጊት እንዳይከሰት የሚገባውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ማድረግና የዜጎችንም ደህንነት አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማስጠበቅ ይኖርበታል ። መንግሥት የሕግ የበላይነትን ሲያስከብርና ዜጎችም ያለፍርሃት ወጥተው መግባት ሲችሉ ብቻ ነው መንግሥትን እንደመንግሥት ሊያዩት የሚችሉትና አገርም እንደ አገር ሊቀጥል የሚችለው። በርግጥ ዛሬ መንግሥት ተጠያቂ ናቸው የሚባሉትን ሃይሎች በሙሉ እጃቸውን ይዞ ለፍርድ ሲያቀርባቸው አይታይም፤ በተለይ በየብሔራቸው ተሰሚነት/ተቀባይነት አላቸው የሚባሉትን አክራሪዎች። መንግሥት ሁሉንም ለፍርድ ለማቅረብ አለመቻሉ በሃገሪቱ ሰላምና ህልውና ላይ የሚያስከትለውን አደጋ/መዘዝ በማገናዘብ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ይሁን እንጂ ውሎም አድሮም ቢሆን የነኚህ ወንጀለኞች ተጠያቂነት አይቀሬ መሆኑን ማስገንዘቡ አስፈላጊ ነው፤ መቼም ቢሆን ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረቡ ወንጀሉ እንዳይደገም ለሌሎች መቀጣጫና ትምህርትም ሰጪ ስለሚሆን።
ዛሬ የሚታየው ብሔረተኝነትን ምርኩዝ ያደረገ ቅራኔ በሕዝብ መሃል ግጭት እንዲፈጠር ግፊት የሚያደርግ መሆኑ ነው ሁኔታውን በጅጉ አሳሳቢ የሚያደርገው። በዚህ ላይ ያለው ድህነትና የማኅበራዊው ችግር ተጨምሮበት የአገራችንን ቀጣይነት የባሰ ፈተና ላይ ጥሎታል፤ ለጽንፈኞቹም ከምንግዜውም የበለጠ ሁኔታውን የተመቻቸ እንዲሆን አድርጎላቸዋል። የነኚህ ሁኔታዎች ድምር ነው ዛሬ እንደአገር እንቀጥላለን ወይስ አንቀጥልም የሚል ወሳኝ የሆነ የታሪክ መገናኛ መንገድ ላይ ያደረሰን። እንደአገር ልንቀጥል ባንችልና ብንለያይም ሶሪያና ሊቢያ ውስጥ እንደሚታየው መቋጭያ እንዳጣው የርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንደማንገባ ምንም ዋስትና የለም፤ የመለያየቱ አደጋ ቢከስትም እንኳን ተለያይተን በሰላም እንኖራለን ማለቱ እንደማይቻል ነው የምንረዳው።
እኛ እንደአገር መቀጠል አለመቀጠላችን ያሳስበናል የምንል ዜጎችም በጋራ በመቆም የመፍትሄው አካል መሆን ይጠበቅብናል። የጽንፈኞች አገር አፍራሽ ሴራ ብቻ ሳይሆን በጋራ አለመቆማችን በአገራችን ቀጣይነት ላይ አሉታዊ ተጽኖ እነደሚኖረው ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። በጋር ቆመን ከስሜትና ከጀብደኝነት በራቀ መንፈስ ምክንያታዊና ገንቢ አስተሳሰቦችን እያቀረብን አገራችንን ለመታደግ መጣር ይኖርብናል። ስትራተጂያችንም የአገሪቱን ሰላምና ህልውና አደጋ ላይ የማይጥል፣ ሁኔታንና ጊዜን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት። ባሁኑ ሰዐት አገራችንን ልትሰበር እንድምትችል የሸክላ ሳህን ልንከባከባት ይገባል። ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ አልፈን የዲሞክራሲ ተቋሞቻችንን ከገነባንና የዲሞክራሲ ባህልንም ካጠናከርን በኋላ ከብረት የጠነከረች አገር ልንፈጥር እንችላለን፤ ያኔ እኛ ብቻ ሳንሆን ሥርአቱ በራሱ አገራችንን ሊታደግልን ይችላል።
የሰሞኑን የድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ የተከሰተው እልቂት ባለፉት ሰላሳና አርባ አመታት ውስጥ ሆን ተብሎ የተገበረው የጥላቻና የከፋፋይ ፖለቲካ ውጤት ነው ማለት ቢቻልም፤ አንዳንድ የኦሮሞ ሊሂቃን ባለመታከት የሚያራምዱት የተዛባና በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ትርክት ያስከተለው መዘዝም ጭምር ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፤ በተደጋጋሚ ከተሰሙ በአንዳንድ የኦሮሞ መሪዎች አላስፈላጊ የሆኑ መርዛማ አነጋገሮች ጋራ ተያይዞ የተቀሰቀሰው ጥላቻም ለእልቂቱ የራሱ የሆነ አስተዋጾ እንደሚኖረው ለመገመት አያስቸግርም። ሁኔታው ኢትዮጵያን በመገንባት ትልቅ ድርሻ ባላቸው በኦሮሞና በአማራ ብሔሮች መካከል የነበረውን የሕዝብን ትሥሥር እንዳሻከረ ግልጽ ነው። እንዲህ አይነቱ አፍራሽ የብሔረተኝነት/የዘረኝነት ፖለቲካ ካልቆመና የተባሉትም ጽንፈኛ ሊሂቃኖች ካልተገሩ ሰሞኑን ያየነው አሳዛኝ ሁኔታ ላለመደገሙ ምንም ዋስትና ሊኖር አይችልም፤ በሕዝቡ ውስጥ ያለውም ፍራቻ የሚወገድ አይሆንም።
ስቶክሆልም
አገር እናድን ቡድን