November 11, 2019

ምንም አይነት ምክንያት መደርደር ወልዲያ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ ሊያቃልለው አይችልም። ግፍን በግፍ ማወዳደር የግፈኞች መገለጫ ነው። ሁለት ሰብአዊ ፍጡራንን በጭካኔ በገደለ ሰው እና ጥቅምት 11/12 በርካታ ንፁሀንን በጨፈጨፉት አረመኔዎች መካከል አንዳች የሞራል ልዩነት የለም። እንደነዚህ አይነት የጭካኔ ድርጊቶችን በአሀዝ ስሌት ለማቃለል መሞክር በየትኛውም ደረጃ የሚፈፀምን ግፍ ከመደገፍ ያልተናነሰ ድርጊት ነው።
አንድስ ቢሆን ለምን ይሙት!? አንድስ ቢሆን ለምን አካሉ ይጉደል፣ ለምንስ ቀሪው ህዝብ የፍርሀትና የመንፈስ ሰቆቃ ይድረስበት!? ተስፋዎቻቸው ሲቀጠፉ መንፈሳቸው እንክት በሚለው እናቶች ፣ ቅስማቸው በሚሰበረው አባቶች ጫማ እራሳችንን አስገብተን የሀዘኑን ልክ መረዳት አለብን። ፍትህ እንዲሰፍን ስንጠይቅ እንደ ዜጋ ለሁሉም እንጂ፣ ወደ ዘራችን ተጠምዘን እያዬን ሊሆን አይገባም።
አቶ ሽመልስ በጉዳዩ ላይ የተናገሩት ምናልባትም በሌሎች ቢነገር የተሻለ ነበር። አቶ ሽመልስ በክልላቸው ስለተደረገው ጭፍጨፋ በኦፊሴል ሲያወግዙ አላየንም። ጭራሽ የመንጋውን ድርጊት “ሰልፉ/ጥያቄው ትክክለኛ ነበር” በማለት በሰላባዎቹ፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በመላው የሀገሪቱ ህዝብና በሀገራችን ላይ ጭምር ተሳልቀዋል። ከድርጊቱ ጠንሳሽ ጋርም “ወንድማችን” ሲሉ አብረዋል።
በነገራችን ላይ ኦሮሚያም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች የነበሩት ፅንፎች ሰማይ የነኩት ከአቶ ሽመልስ የኢሬቻ ንግግር በኋላ ነው ። አቶ ሽመልስ ለደረሰው እልቂት፣ የአካል መጉደልና ንብረት መውደም ከጃዋር እና ከ OMN ባላነሰ እንዳውም በበለጠ (የክልል ፕሬዝዳንት እንደመሆናቸው) ተጠያቂ ናቸው።
በሚያስተዳድሯት ኦሮሚያ ለተፈፀሙትና በንግግሮቻቸው ለተፈጠሩት ምስቅልቅሎች ሁሉ፣ እንኳን ይቅርታ ሊጠይቁ እውቅናና ሀዘናቸውን ባልገለፁበት ሁኔታ፣ በወልዲያም ሆነ ቤትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚደርስን ማናቸውንም ድርጊት ለመኮነን አቶ ሽመልስ ምንም አይነት የሞራል ብቃት አይኖራቸውም። በተናገሩት “የተካይና የተነቃይ” ንግግር ሚሊዮኖች አንጀታቸው በተቃጠለበትና ፅንፈኝነት ባሻቀበበት ምህዳር ላይ ቆመው ስለ ሀዘንና ስለ ህግ በላይነት ቢደሰኩሩ አንሰማም፣ አንለማም። ኦሮሚያ ውስጥ የተጨፈጨፉት ምስኪኖች እና ጨፍጫፊዎቹ እኮ ወልዲያ ውስጥ እንደተገደሉት እና እንደ ገዳዮቹ ሁሉ ሰው ናቸው። ላንዱ ፍትህን ያልጠየቀ ለሌላው መጠየቅ አይችልም። ላንዱ ልቡ ያልተሰበረ ለሌላው የሚሆን እንጥፍጣፊ ርህራሄ ሊኖረው አይችልም።
የአማራ ክልል የፀጥታ ሀይል ሁኔታውን በቁጥጥር ስር ለማዋል የወሰደው እርምጃ፣ ባለስልጣናቱ የሰጧቸው መግለጫዎችና የወልድያ ህዝብ ለተማሪዎቹ እያሳዬ ያለው ሀዘኔታ እና ፍቅር ሊወደስ ይገባዋል። “ወልዲያ ውስጥ ያሉ የሌላ ክልል ተማሪዎች ሁሉ ልጆቻችን ናቸው” የሚለው የወልዲያ ህዝብ መፈክር ከምንጊዜውም ምርጥ መፈክሮቻችን ውስጥ አንዱ ሆኖ ሊመዘገብ ይገባል።
ፍትህ በግፍ ለተገደሉ የወልድያ ዩኒ ተማሪዎች!!!
ፍትህ በኦሮሚያ ለተጨፈጨፉት ንፁሀን!!!
የግፍ ሰለባ ለሆኑ ሁሉ ነብስ ይማር!!!