
November 8, 2019
ወደምስራቅ ተመልከቱ የሚለው ቃል ሰማያዊ መልዕክት እንዳለው አውቃለሁ፡፡ ይህን ቃል የሱማሌው ክልል ምሁርና በማሕበረ ገጽ ጸሐፊ ሙክታሮቪች ኢስማኖቪች (ሙክታር ኡስማን) ወደምስራቅ ተመልከቱ የተባለው አለአግባብ እንዳልሆነ የገለጸበትን ጽሁፉን ስመለከት በዚህ (በሱማሌ) ክልል ያሉ ምሁራንን እይታ ለአንድ አፍታ ሳስብ እጅግ ገረመኝ፡፡ እርግጥ ነው ስለሱማሌ ክልል ተወላጅ ምሁራን ማስተዋል ከጀምርኩ ቆይቻለሁ፡፡ የአሁኑ የክልሉ ፕሬዘደንት ሙስጠፌ ወደስልጣን ሳይመጡ በፊት በሚሰጧቸው ሁለንተናዊ አስተያየቶች ከሚደነቁ ነበርኩ፡፡ በጣም የሚገርምና ፊትለፊት ያለን እውነታ እንድናስተውል ነው የሙስጠፌ ፍልስፍናዊ አተያይ፡፡ በጅምላ ዩኒቨርሳሊዝምና በተምታታ ማንነት አደለም፡፡ ዓለም ዓቀፋዊ የሆኑ የዲሞክራሲና የሰበዓዊ መብት ተንታኝ የሚሆኑ ግን ከሰፈር ጉሮኖ ያልወጡ ኩርንችት አሳቢዎችን በምናስብ ጊዜ እጅግ ያሳዝነኛል፡፡ ሙስጠፌ የኢትዮጵያዊ ወገንተኝነቱን አልፎም ሶማሌን ጨምሮ የሐበሻን ወገንተኝነቱን ሳይደብቅ የስብዕናንና ዩኒቨርሳሊዝምን እንድናስተውል የሚረዳንን ፍልስፍናውን ነው በልበ ሙሉነት እየነገረን ያለው፡፡ አሁን አሁን ግን ይሄ አስተሳሰብ የሙስጠፌ ብቻ ሳይሆን የበርካታ የሱማሌ ክልል ተወላጅ ምሁራን እንደሆነ እያስተዋልን በኢትዮጵያዊነት ፉከራ ለምናቅራራውም በዘር ጥብቆም ተጣብቀን ጉሮኗችን ውስጥ ለተከረቸምን በራሳችን እንድናፍር እያደረጉን ነው፡፡
ሙክታሮቪች አንዱና ወጣት የእነ ሙስጠፌ ፍልስፍናና አስተሳሰብ አራማጅ ነው፡፡ ሰሞኑን በኤል ቲቪ ቀርበው ብዙዎችን በሚያስደምም ሁኔታ ሲናገሩ የታዩት የብራስልሱ መሐመድ ሀሰን ከምሁርነትም በላይ ከልጅነት ጀምሮ ብዙ ነገሮችን በማስተዋል የኖሩና አንባቢ የብዙ ልምድ ባለቤት እንደሆኑ ታዝበናል፡፡ ከዚህ ቢት ሌላ በእድሜ ከመሀመድም የተለቁ ምን ዓልባትም በአረጋዊነት ምድም ያሉ እንዲሁ ከዚህ ክልል የሆኑ ሰውን ስለኢትዮጵያዊነት የተናገሩትን አጋርቻችሁ ነበር:: https://www.youtube.com/watch?v=mu4ghQ_SzBQ ከ18ኛው ደቂቃ በኋላ የሚናገሩት ናቸው፡፡ ይሄ ትልቅ ተሰፋ ነው!
በአሁኑ ወቅት ከሁሉም ክልሎች ይልቅ የሰሱማሌ ክልል በምሁሮች መመራት ብቻም ሳይሆን መሪዎቹ በሙሉ በወያኔ ዳረጎትና የአስታሰብ ባርነት ያደጉ ሳይሆን በነጻ ተፎካካሪነት ዕውቀትን ከተለያዩ አለማት የቀሰሙና ስለሕዝባቸው የሚቆጩ ናቸው፡፡ በሌሎቹ ክልል ግን አሁንም ያሉት በወያኔ የአስተሳሰብና የተንኮል ባርነት የወደቁ ከዚህ ከወጡ መውደቂያ የሌላቸው ናቸው፡፡ ዛሬ በአማራ በሉት በኦሮሚያ ዋና የፖለቲካ መሪ የሆኑት ከጅምሩ ጀምሮ በወያኔ ያደጉና ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ክልል መሪ ነኝ የሚለውን ግለሰብና ሙስጠፌን በምንም መስፈርት ማወዳደር አይቻልም፡፡ እንግዲህ ምሁር ጠፍቶ አይመስለኝም ችግሩ ምሁርና በነጻ የሚያስቡ በዚህ ክልል እንደ ጠላት ስለሚታዩ እንጂ፡፡ ሰሞኑን ታዬ ደንደአ እውነትን በመናገሩ ምን ያህል ዛቻና የጥላቻ ዘመቻ እየተካሄደበት እንደሆነ እያስተዋልን ነው፡፡ በዚህ ክልል በተለይ ከሸዋ ለሚወጡ ፖለቲከኞች በከፍተኛ ደረጃ ቦታ እንዳይዙ ይደረጋል፡፡ ዛሬ ታዬን የገጠመው ይሄው ነው፡፡ ከዚህ በፊት በዶክተር አለሙ ላይ ተመሳሳይ ዘመቻ ሲደረግበት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
ለማንኛውም ሁሉም ምሁራን ሊጋፈጡት ግድ የሚል ታሪካዊ ወቅት አሁን ነው፡፡ አገርን ለወሮበሎች አስረክቦ ወገን በየቀኑ እየተገደለና፣ እያለቀሰ አላቃሽ ብቻ ከመሆን ያለፈ ሥራ አለመስራት አገርን እያፈረሰ ከአለ ዋናው አደጋ ነው፡፡ አገር የምትፈርሰው በወሮበሎች ጥፋት ሳይሆን በአዋቂዎች ግደሌሽነትና ዝም ባይነት አልፎም አድር ባይነት ነው!Current Events In Ethiopiax
ቅዱስ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን! አሜን!
ሰርፀ ደስታ