https://l.facebook.com/l.php?u=https%3A%2F%2Fbuff.ly%2F2qPr103%3Ffbclid%3DIwAR045xmCuFxka0hCbChIY7hKUzmXl0rRkgRLinwgFEzzADgNYXBkrd7y_yA&h=AT13uFMdoCpcFw9PWs61Mx0TdPfQPGjjXsyI7y5wKpCrPdILwEAzxI2rWxXw_DkKDxDR1dfYfu0wWwl9Q9sdliw_J7MDMQcaVWp49e0ailEoyzdOsR94mmsnrXh59mcjxtso8MEEHhC-Js8j3K9yVOVfhkhRlD8GioD6Wq7NeRMSpbSk4RCyEiUBDigPoiPol2KcchAMKwV1hXRx4wZnnWgpCFYUzyhBtMZtMaLZxEkMJSRIvgPUf2c6hoi5PsswKc93pJgU5OXSMrjdN3ws7DuGv-M2wyoamMn1XOvOANiijF-Vv1Qf3XjbY2NiqyunuafJvnpLTT8C8_LMjnmPzDXvDUYzdvBtZzm946Kx6UUTk3hbksa7dSb_ry-z-ELRRrjNUs6P4Av3AYTzSfZZ7Zixz-QjSK0DV3XKTL4t1cxn32iwW_dU8tHenYQG3E3grPKAG2lVfo5-1RtA5m9AOjr-XF4GXeIXiLXyOM3YLz_rlHjK5COf_3ZToOTGAS7l72rKhbqamt22KVpv5HzvTIAQMVjQc1Y1v9AyLZiivUuUGoFw_PN4QSg4eBsTJitxGG0hP2S9vOfJSeHH4cy7Trw_Q3FZtWSPeISnF8QJtRYgvn2vBnWB_X23wkEUS4ATuhvTlLhIrjAa34w5G0J7HwTWMe9Utjx9ZYlVbLOrmfcrIQI

ስለ ወቅታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ፣
ኢትዮጵያ በታሪክ ሂደት ውስጥ እጅግ በጣም አሳሳቢ በሆነ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ትገኛለች፡፡ በሀገራችን ወስጥ በአሁኑ ጊዜ ያለው የኃይል አሰላለፍ የዜግነት(የአንድነት) የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ጽንፈኛ የብሄር ሰብ ፖለቲካ አስተሳሰብ መካከል ያለው ቅራኔ ነው፡፡ የዜግነት(የአንድነት) የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖች(ኢሕአፓን ጨምሮ) የኢትዮጵያ ህልውና ተጠብቆ ዲሞክራሲያዊ ሥርአትን ለማየት ሲታገሉ፣ ጽንፈኛ የብሄር ሰብ ፖለቲካ አራማጆች ደግሞ ሀገሪቱን በብሄር ከፋፍለው ለመበተን እየሠሩ ነው፡፡
በዚህ ዋነኛ በሆነው የዜግነት እና የጽንፈኝነት ፖለቲካ አስተሳሰብ ትግል ውስጥ፣ ጽንፈኛ የብሄር ሰብ ፖለቲካ አራማጆች ያለማቋረጥ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተንኳሽና ጠብ አጫሪ ተግባራትን በማድረግ፣ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመክተት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡
ጽንፈኞች በቃላት ከሚያደርጉት መስፈራራት አንስቶ፣ እስከ ግጭት መቀስቀስ፣ መንገድ መዝጋት፣ ዝርፊያና ግድያ ድረስ ወንጀል እፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ በፍጹም ወደ ለየለት የፖለቲካ እብደት ውስጥ እየገቡ ከሀገራችን አልፎ ለቀጠናችን ሊተርፍ የሚችል የጦርነት ድግስ እየደገሱ ነው፡፡ ራሳቸውንም እንደ ሁለተኛ መንግሥት ቆጥረው ህገወጥ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡
በዚህ ረገድ ሰሞኑን የኦሮሞ ጽንፈኞች በአዲስ አበባ እና በተወሰኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች መንገድ በመዝጋት የህዝቡ የዕለት ተዕለት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲገታ እያደረጉ ነው፡፡ ሽብር በህዝቡ ላይ እየነዙ ነው፡፡ ዝርፊያ እየካሄዱ ነው፡፡ በንጹሀን ዜጎች(ሴቶችንና ህጻናትን ጨምሮ) ግድያ እየፈጸሙ ነው፡፡ የሀይማኖን እና የዘር ግጭት ለመቀስቃስ በክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች እና በሌሎች ብሄር ተወላጆች ላይ ጥቃት በመፈጸም ላይ ናቸው፡፡ በዚህ ጥቃት ቆሜለታለኁ የሚሉትን የኦሮሞ ተወላጆችን ጭምር በማካተት እጅግ አደገኛነታቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቅ ትዕግሥት ጽንፈኞቹን ወደ አዕምሮአቸው እንዲመለሱ ከሚያደርገው ምክር በተጨማሪ እራሱን ከነዚህ ወንጀለኞች ለመከላከል እያደረገ ያለውን ጥረት ፓርቲያችን ያደንቃል፡፡ ተደራጅተው ጥቃቱን እንዲከላከሉ ያበረታታል፡፡ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የህዝቡን ደህንነት መጠበቅ አለባቸው፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ እና ክልል ፖሊሶች ግን ኅዝቡን ለመታደግ ያሳዩት ቸልተንነት ብሎም ከወንጀለኞቹ ጋር ያሳዩት ህብረት በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ እነዚህ ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ለተፈጠረው ጥፋት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ዘረፋ፣ ድብደባ ግድያና መፈናቀል በተመለከተ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) የሚከተለውን አቋሙን ይገልጻል፣
1. በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ቀስቃሽነት የተደረገውን ጥቃት ኢሕአፓ እያወገዘ፣ ለሞቱ፣ ለቆሰሉ፣ እና ለተፈናቀሉ ዜጎች ፓርቲያችን ልባዊ ሀዘኑን ይገልጻል፣
2. የተፈጸመው ጥቃት በሰዎች ላይ የተደረገ ወንጀል (Crime Against Humanity)ስለሆነ መንግሥት ገለልተኛ አጣሪ አካል ሰይሞ ጉዳዩ እንዲጣራ፣ ወንጀለኞቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ተጠቂዎቹም እንዲካሱ ፓርቲያችን ይጠይቃል፣
3. ዜጎች የህይወት የመኖር፣ ተዘዋውሮ የመሥራትና ፣ በሰላም ወጥቶ የመግባት መብቱታቸው አንዲከበርላቸው እንጠይቃለን፣
4. መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን በአግባቡ ያልተወጣ በመሆኑ እያወገዝነው፣ ለወደፈቱ ከዚህ ዓይነት ደካማነት ራሱን እንዲያስተካክል እናሳስባለን፣
5. በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች እየተሰፋፋ ያለው ኢ-መደበኛ አደረጃጀት እንዲታገድና በህጋዊ አደረጃጀት እንዲተካ እንተይቃለን፣
6. የኢትዮጵያ ሕዝብ በጽንፈኛ የብሄር ፖለቲከኞችና (አክቲቪስቶች) እየተደረገበት ያለውን የጥቃት ሁኔታ በአግባቡ ተገንዝቦ የቆየ የመከባባርና የመዋደድ ባህሉን አጠንክሮ ወንጀለኞቸን በመከላከል ሥፍራ እንዳይኖራቸው እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን፣
7. ህዝብና ህዝብን የሚያገጩና የርስ በርስ ጦርነት ጥሪ የሚያደርጉ የጽንፈኛ አክቲቪሰት ሚዲያዎች በህግ መሠረት እንዲጠየቁ፣ ሕዝቡም ለከንቱ ፕሮፓጋንዳቸው ጆሮ እንዳይሰጣቸው እናሳስባለን፣
8. በኢትዮጵያ ያሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ በዚህ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ወቅት ላይ ከህዝቡ ጎን በመሆን ለሰላም እንዲታገሉ ጥሪ እናደርጋለን፣
ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቃት
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ)
ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም.