November 12, 2019

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ 16 ወረዳዎች ውስጥ አንዱ ነው፤ የደራ ወረዳ፡፡ በወረዳው 39 ቀበሌዎች ከ 400 ሺህ በላይ ሕዝብ እንደሚኖርም ይገመታል፡፡

በዚህ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ ቀበሌዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ነዋሪዎች የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች፤ ቀሪዎቹ ደግሞ የአማርኛና ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዚህ ወረዳ ውስጥ የሚኖሩ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ‹‹ባሕልና ወጋችን በራሳችን ቋንቋ እንዳናሳድግ፣ በቋንቋችን እንዳንዳኝ፣ ይባስ ብሎ ለልጆቻችን የሚመደቡት መምህራን በቋንቋ ስለማይግባቡ የትምህርቱ ጉዳይ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡ በራሳችን ጥረት እንኳ ተምረን ብንመረቅ በአካባቢው ተቀጥረን መሥራት ባለመቻላችን ለስደትና ሌሎች እንግልቶችም እየተዳረግን ነው›› ብለዋል፡፡ በሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም ተመሣሣይ ችግሮች እየደረሱባቸው እንደሆነ የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል፡፡

ከቀበሌ እስከ ፌዴራል የራሳቸው ተወካይ እንደሌላቸው፣ በቋንቋ ምክንያት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተሳትፎ ማድረግ ስለማይችሉ በደል እየደረሰባቸው እንደሆነም ቅሬታቸውን ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

የኮሚቴው አባላት እንዳስረዱት አስተዳደራዊ በደሉን መንግሥት እንዲፈታው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለበርካታ ዓመታት ብዙ ደክመዋል፤ የሚሰማ አካል ግን አላገኙም፡፡ ‹‹አሁንም መንግሥት ጩኸታችን ሊያዳምጥና ችግራችን ሊፈታልን ይገባል›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ስለጎዳዩ በአብመድ ተጠይቀው ‹‹መጀመሪያ ማዬት ያለበት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ነው›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አብመድ ጉዳዩን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶኦን ጠይቋል፡፡ አፈ ጉባኤዋ ጉዳዩ ከዚህ በፊት ለምክር ቤት እንዳልቀረበ ተናግረዋል፤ ነገር ግን መስከረም 25 ቀን 2004 ዓ.ም እና ሕዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈ ቤት እንዲሁም ሕዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም ለኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኮሚቴዎቹ ጥያቄያቸውን በጽሑፍ ማቅረባቸውን የኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል፤ ደብዳቤው ለመድረሱም ለፊርማ ማረጋገጫ በያዧቸው ቀሪ ደብዳቤዎች እንደሚገኙ ለአብመድ አሳይተዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ አዳሙ ‹‹ኮሚቴዎቹ ከዚህ በፊት በ2006 ዓ.ም ለምክር ቤቱ ጥያቄያቸውን ያቀረቡበትን መረጃ ማግኘት አልቻልንም፤ በ2011 ዓ.ም ያቀረቡትን አቤቱታ ግን አግባብ ባለው መንገድ እንዲስተናገድ ተቀብለን አስቀምጠናል›› ብለዋል፡፡ የኮሚቴው አባላት ግን ሕዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረባቸውን አመልክተዋል፤ ለመድረሱም የፊርማ ማረጋገጫ የሚያሳይ ቀሪ ደብዳቤ ይዘዋል፡፡

የኮሚቴ አባላቱ ለኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕጋዊ ደብዳቤዎችን አስገብተው ‹‹አላስገቡም›› በመባላቸው ቅር መሠኘታቸውንና በእጃቸውም ማረጋገጫ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ -ከአዲስ አበባ/ አብመድ