2019-11-15
ለኦሮሞ እና ለአማራ ልጆች (እንዲሁም ለክርስቲያኖች እና ለሙስሊሞች)
አፈንዲ ሙተቂ
ሀገሪቷ ሁላችሁንም ትፈልጋለች:: የፖለቲካው ጡዘት ነገሮችን በሰከነ አእምሮ የምንመለከትበትን ሃይል ስለነሳን የማንም ማጅራት መቺ መፈንጫ መሆናችን ያሳዝናል:: “ሶሻል ሚዲያው እንደ ነዳጅ ዘይት ነው: በጥንቃቄ ካልተጠቀምንበት ሀገር ያጠፋል” ብንባባልም አድማጭ አልተገኘም:: በጭቆናው ዘመን አብረን ኖረን: ጭቆናው ሲብስብን ደግሞ አብረን ታግለን ጨካኙን የወያኔ ጁንታ ካባረርን በኋላ እርስ በራሳችን መናቆራችንና መጋደላችን በእጅጉ ልብ የሚነካ ነገር ነው:: አቶ ጌታቸው ረዳ እና መሰሎቹ “ይህ ያልተቀደሰ ጋብቻ ነው: በቅርቡ እርስ በራሳቸው ይባላሉ” በማለት ያሟረቱብንን እውነት እያደረግነው ነውን? ወይንስ በውጪ ሀገራት የምንሰማው አይነት ፍጭት በሀገራችን እንዲከሰት ነው የናፈቀን? የነገሮች ውል ጠፍቶብናል:: አማራና ኦሮሞን እያጋደለ ያለው ሃይል ማንነት በውል አልታወቀም:: ሆኖም ይህ ሃይል ለየትኛውም ህዝብ ቀና አሳቢ አለመሆኑ እሙን ነው:: ህዝብን እያጋደሉ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርአት መመስረት አይቻልም:: ህዝቦችን ማጋደል ትርፉ ቂም በቀልን ማውረስ ነው:: የኦሮሞን መብት መጠየቅና አማራውን መግደል እንደ ሰማይና መሬት ይራራቃሉ:: የአማራውን መብት መጠየቅና ኦሮሞውን መግደል እጅግ በጣም ተቃራኒ የሆኑ አስተርዮዎች ናቸው:: — እኛ የገለምሶ ከተማ ሙስሊሞች ባለፈው እሁድ የመውሊድ በዓል አካባበርን ከጠናቀቅን በኋላ አንድ በሬ ለከተማችን ክርስቲያኖች ሰጠተን ነበር:: በሬውን ቤተ ክርስቲያን ወስደን ነበር ያስረከብነው::: በወቅቱ ክርስቲያን ወገኖቻችን እኛን አቅፈው ከመሳም አልፈው በደስታ አልቅሰውም ነበር:: ይህ የከተማችን የቆየ ባህል ነው:: ዘንድሮም ተተግብሯል:: ወደፊትም ይቀጥላል:: ኢንሻ አላህ!! ታዲያ በዛሬው እለት ቤተ ክርስቲያን እና መስጊድ መቃጠላቸውን ስሰማ ማመን ነው ያቃተኝ (ትናንት በራሪ ወሬ ስሰማ “በሀረርጌ እንዲህ የሚያደርግ የለም” በማለት በድፍረት ፅፌ ነበር:: የማይታመን ነገር ስለሆነብኝ ነው እንዲያ ያደረግኩት:: ሁለት ልጆች ማረሚያ ሲልኩብኝ ግን በአስር ደቂቃ ውስጥ ፅሁፌን አነሳሁት። አዝናለሁ)። በውኑ የሀገሬ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች እንዲህ ይጨካከኑ ነበርን? በሁለቱም ሃይማኖቶች ውስጥ “ቤተ እምነት ያቃጠለ ይፀድቃል” የሚል አስተምህሮ የለም:: ይህ የጋራ ጠላቶቻችን ሊያጨራርሱን ሲሉ የላኩብን ቅጥረኛ ሴራ ነው:: —- ወገን! በአንድ ሀገር ውስጥ ነው የምንኖረው:: በእምነትና በብሄር ብንለያይም በሌሎች ብዙ መንገዶች እንገናኛለን:: በእንደዚህ አይነቱ ጊዜ የሚያስፈልገን ፍቅራችን ማጠናከር ነው:: ውጥረትና ሁከት የሚረግበውም እንደዚያ ነው:: ስለዚህ ባለንበት አካባቢ ሁሉ ሊያባሉን የሚቀሰቅሱትን እያጋለጥንና ሰላምና ፍቅራችንን እያጎለበትን ሀገራችንን ከአደጋ እንድንታደጋት ጥሪዬን አቀርባለሁ:: Filed in:Amharic