2019-11-15

የዳንኤል ክብረት ኢወቅታዊ እውነታ

መስፍን አረጋ 

ይህችን አጭር ጽሑፍ ለመጻፍ የተነሳሳሁት ሙሃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ‹‹ከዲሞክራሲ በፊት ፍትህ›› በሚል ርዕስ ያደረገውን ግሩም ንግግር ካዳመጥኩ በኋላ ነው፡፡  ዳንኤል በትክክል እንዳስቀመጠው የጦቢያ አንገብጋቢ ችግር የዲሞክራሲ እጦት ሳይሆን የጦቢያ የፍትሕ እመቤት (lady justice) በብሔር በሽታ መታወር ነው፡፡  ዳንኤል ለመናገር ያልፈለገው ወይም ደግሞ የፈራው ግን የፍትሕ እመቤታችንን ያሳወራት የየትኛው ብሔር በሽታ መሆኑን ነው፡፡  ቢፈራም ደግሞ አይፈረድበትም፡፡ ራሱን ዳኛ አድርጎ ልጁን ቀማኛ ያደረገው ማነው? የኦነጉ ጌታቸው አሰፋ (ብርሃኑ ፀጋየ) ዐቃቤ ሕግ በሆነበት አገር አቤት የሚባለው ለማን ነው?

የዳንኤል ሐሳብ ምንም የማይነቀስለት እንከን የለሽ እውነታ ነው፡፡  ችግሩ ግን ወቅቱን የጠበቀ እውነታ አለመሆኑ (ኢወቅታዊ እውነታ መሆኑ) ነው፡፡  ማናቸውም ነገር እሴት የሚኖረው በተገቢው መቸት (መቸና የት) ላይ ሲመቸት ብቻ ነው፡፡  ጥድ አለቦታው ብሳና ይሆናል፡፡ የዳንኤል ሐሳብ ላገራችን ችግር ዘላቅ መፍትሔ ቢጠቁምም፣ አንድ ሐሙስ ለቀራት አገራችን ግን ነፍስ አድን አይደለም፡፡

አንበስና ሌንጮ የሚባሉ ሁለት ሰወች አሉ እንበል፡፡  ሌንጮ መቸም የማላገኘው ምቹ አጋጣሚ ተፈጠረለኝ ብሎ አንበስንና የአንበስን ዘር ማንዘሮች በሜንጫ በመቆራረጥ፣ የተረፉትን ጥቂቶቹን ደግሞ በሞጋሳና በጉዲፈቻ የሱ የራሱ በማድረግ የአንበስን ቴሳ (ድራሽ) ለማጥፋት ቆርጦ ተነሳ እንበል፡፡  በዚህ ወሳኝ ሰዓት ላይ አንበስ መጨነቅ ያለበት ራሱንና ወገኖቹን ከጥፋት ስለማዳን ብቻና ብቻ ነው፡፡ ቀጥሎ መጨነቅ ያለበት ደግሞ ለሌንጮ የተፈጠረለት ምቹ የጥፋት አጋጣሚ ዳግመኛ እንዳይፈጠር ስለሚያረጋግጥበት መንገድ ነው፡፡ ከዚህ እፎይታ በኋላ ነው አንበስ ስለ ፍትሕና ርትዕ በተረጋጋ መንፈስ እያሰበ ሌንጮንም እንዲያሰብ ለማድረግ የሚሞክረው፡፡

እየየም ሲደላ ስለሆነ የመኖር ያለመኖር ጥያቄ ከፊቱ ለፊቱ ለተደቀነበት የአማራ ሕዝብ የፍትሕ ጥያቄ የቅንጦት ጥያቄ ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል አሕግ (የአሜርቃ ሕቡር ግዛቶች፣ USA) ባንጻራዊ ደረጃ ፍትሕ የሰፈነባት አገር ናት፡፡ ይህ ፍትሕ የሰፈነው ግን እልፍ አእላፍ ፈጅሬ አሜሪቃውያን (native americans) ያለ ርህራሄ ተጨፍጭፈው ዘር ማንዘራቸው ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ከጠፋና የተረፉት ጥቂቶች ደግሞ በግዴታ ግድፈቻ (በግዴታ ጉዲፈቻ በማድረግ፣ forced adoption) ማንነታቸውን እንዲለውጡ፣ ወይም ደግሞ የመጠጥና የእጽ ሰለባ እንዲሆኑ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡  

በተመሳሳይ ሁኔታ የአማራው ሕዝብ ከኦነግ ሜንጫ ራሱን በራሱ ታድጎ ቀጣይነቱን ካላረጋገጠ በስተቀር፣ ዳንኤል የሚመኘውን ፍትህ፣ ርተዕና፣ ዲሞክራሲ ሊያጣጥሙ የሚችሉት ኦሮሙሜወች ብቻ ናቸው፡፡  ያማራ ብሔርተኛ ድርጅቶች ሊደገፉ የሚገባቸውም አማራውን ከኦነግ ጅብ ለመከላከል የግድ ስለሚያስፈልጉ ነው፡፡ ስግብግቡ የኦነግ ጅብ አብንን መደገፍን አማራጭ የሌለው ምርጫ አድርጎታል፡፡  

ስለዚህም ዳንኤል በእኩል ዓይን ቢመለከታቸውም፣ ሳይወድ በግድ በቅርብ ጊዜ ያቆጠቆጠው ያማራ ብሔርተኝነትና አሠርት ዓመታትን ያስቆጠረው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዱባና ቅል ናቸው፡፡  ዐብይ አህመድን የኦሮሞ ብሔርተኝነት ቅንጣት ሳያሳስበው ያማራ ብሔርተኝነት እንቅልፍ የነሳው ሁለቱ ብሔርተኝነቶች እየቅል መሆናቸውን በደንብ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ያማራ ብሔርተኝነት ዓላማ አልኦሮሞ ጦቢያውያንን ከኦነግ ጽንፈኞች በመታደግ የጦቢያን ቀጣይነት ማረጋገጥ ሲሆን፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዓላማ ግን በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ የኦሮሞን አጼጌ (empire) መመሥረት ነው፡፡   

ጠላት ምንግዜም ጠላት ስለሆነ፣ አስቀድሞ መወገድ ያለበት የጠላት አሾክሿኪ ነው፡፡   ከፀራማራ ኦነጋውያን ጋር የሚደረገው የሞት ሽረት ትግል ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ደግሞ አማራ የለም የሚለውን ግንቦት ሰባትን ካማሮች መኻል በመመንጠር ነው፡፡  ባሁኑ ጊዜ ከኦነጋውያን ይልቅ አማራውን ይበልጥ የሚጨፈጭፉትና የሚያስጨፈጭፉት ይህ መሠሪ ድርጅት በአዴፓ (ብአዴን) አመራር ውስጥ የሰገሰጋቸው ፀራማሮች ናቸው፡፡

ስለዚህ ክቡር ዳንኤል ክብረት፣ ስለ ፍትሕ ለመወያየት መቀመጥ ስለሚያስፈልገን፣ በመጀመርያ የመቀመጫችንን እሾህ እንንቀል፡፡    

    መስፍን አረጋ 

    mesfin.arega@gmail.com