SourceURL:https://www.ethiopianreporter.com/article/17313 መኢአድ የቀድሞ ሊቃነ መናብርቱን አስጠነቀቀ | ሪፖርተር Ethiopian Reporter Amharic

መኢአድ የቀድሞ ሊቃነ መናብርቱን አስጠነቀቀ
17 November 2019 ነአምን አሸናፊ
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የቀድሞ ሊቀ መናብርቱ አቶ አበባው መሐሪና በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር)፣ ከኢዜማ ጋር ተዋህደናል በማለት ፓርቲውን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው በማለት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠነቀቀ፡፡
መኢአድ ይህን ያሳሰበው ሐሙስ ኅዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር) እና ኢዜማ ተዋህደናል ማለታቸውን አስመልክቶ በሰጠው የተቃውሞ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ሲሆን፣ መግለጫውን የሰጡት ደግሞ ሊቀመንበሩ አቶ ማሙሸት አማረና ምክትላቸው አቶ ሙሉጌታ አበበ ናቸው፡፡
ውዝግቡ የተከሰተው የመኢአድ የቀድሞ ሊቀመንበር በዛብህ (ዶ/ር) እና አቶ አበባው ማክሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢዜማ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው፣ ከፓርቲው ጋር ውህደት መፈጸማቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው፡፡
በዚህ ምክንያት የመኢአድ አመራሮች የቀድሞ ሊቃነ መናብርት ድርጊት ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቀጠቡ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከዚህ ድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ ግን በሕጋዊ መንገድ መኢአድ መብቱን እንደሚያስከብር አስታውቋል፡፡
ጉዳዩን ከኢዜማ አመራሮች ጋር በመወያየት ለመፍታት ሞክረው እንደሆን ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ፣ ‹‹በፓርቲያችን ላይ የማፍረስ ሴራ እየተካሄደ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያስፈልገን መወያየት ሳይሆን ፊት ለፊት መፋለም ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ተግባራቸውን እንዲያቆሙ እናደርጋለን እንጂ አንወያይም፤›› ሲሉ አቶ ማሙሸት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ተደረገ የተባለው ውህደት ከመኢአድ ጋር እንደማይገናኝና የግለሰቦች ጉዳይ ብቻ መሆኑን ተገንዝበው አጋርነታቸውን እንዲቀጥሉ ለአባላቱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የመኢአድ አመራሮች የፓርቲውን የቀድሞዎቹን ሊቃነ መናብርት በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር) እና አቶ አበባው መሐሪን የሕወሓት ተላላኪዎች በማለት ተችቷቸዋል፡፡
ሆኖም እነዚህን ግለሰቦች ሊቃነ መናብርት አድርጋችሁ ስትመርጡ ነበር፡፡ ይህን የምታውቁ ከሆነ ከመጀመርያ ለምን ዕርምጃ አልወሰዳችሁም ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ፣ ‹‹በወቅቱ ምንም ዓይነት ዕርምጃ ያልወሰድነው ፓርቲውን ከማፍረስ ለመታደግ ነው፤›› ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡