2019-11-20

‹‹የመደመርና የውሕደት የፖለቲካ ሤራ››?

ከይኄይስ እውነቱ

የኢትዮጵያ ቆሻሻ ፖለቲካ ለሤራ፣ ለአሻጥር፣ ለሸፍጥ፣ ለተንኮል ያነሰበት ጊዜ የለም፡፡ አገዛዞች በየትኛውም ጊዜ ሕዝብን የሚያደናግሩባቸውና የሚያጃጅሉባቸው ፍሬ የሌላቸው የቃላት ኳኳታዎች አያጡም፡፡ ‹መደመርና ውሕደት› ከዚህ የሚደመሩ ይመስለኛል፡፡ አገር በጭንቀት በጥበት ባላችበት በዚህ ቀውጢ ወቅት እነዚህን ‹ባዶ ቃላት› የሚሰማ ጆሮ፣ የሚናገር አንደበት፣ የሚያሰላስል ኅሊና የለንም፡፡ አገዛዞች ግን የፖለቲካ ትርፍ እንደሚያገኙበት አልጠራጠርም፡፡

አንዳንዶች (የውስጥ ዐዋቂ እንደሆኑ የሚነገርላቸው) የወያኔን የሰሞኑን ‹ውሕደት› የሚል ማደናገሪያ በመተንተን ሲደክሙ ይስተዋላል፡፡ ሥራቸው ነውና (መረጃና ማስጠንቀቂያ በመስጠት ረገድ) ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ 

ይሁን እንጂ ቁም ነገሩ ያለው ነባሩም ሆነ አዲሱ ወያኔ በርእዮተ ዓለም/ በፍልስፍና (ከነበራቸው/ካላቸው)፣ በፖሊሲ ደረጃ በተግባር ምድር ላይ ላለፉት 28 ዓመታት ለሥልጣንና ለዝርፊያ ሲሉ ያዋሉት የአገዛዝ ዘይቤ ላይ እንጂ ስያሜው ላይ ትኩረት ሰጥተን ባንነታረክ መልካም ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ምድር ላይ ያለው ጽድቅና እነዚህ በተውሶ የመጡ ስያሜዎች አንዳች ኅብረት እንደሌላቸው አስተዋይ ኅሊናና አእምሮ ያለው ሁሉ ገና ከማለዳው የተገነዘበ ይመስለኛል፡፡ እውን ወያኔ ትግሬ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ› ‹ልማታዊ መንግሥት› ወዘተ ለሚባሉ አሳቦች ገብቶትና ተጨንቆ ይመስላችኋል? በነዚህ ማደናገሪያዎች ሽፋን ኢትዮጵያን በእጁ ጨብጦ በግሩ ረግጦ ለመግዛት፣ ሥልጣኑን ለማደላደልና ያለማንም ሀይ ባይ ለማይጠረቃ ዝርፊያው ከለላ ስላደረገው እንጂ፡፡ ቁም ነገሩ ያለው የጐሣ ፖለቲካው፣ የጐሣ ፌዴራላዊነቱ፣ ‹‹ክልል›› በሚል ያደራጀው መዋቅር፣ እነዚህንም ሕጋዊ ቅርፅ ለመስጠት ድርጅታዊ ዓላማውንና ፕሮግራሙን የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› አድርጎ ሥራ ላይ ማዋሉ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ በታሪኳ አገዛዝ እንጂ ሥርዓት ያለው መንግሥት ኖሯት ስለማያውቅ፣ ፖለቲካ ዕውቀትን (ሳይንስንና ፍልስፍናን) መሠረት አድርጎ የምንመራበት አገር ውስጥ ባለመሆናችን፣ ሕዝብን ለማታለል ወይም በጥራዝ ነጠቅነት የአገዛዝ ቁንጮ የሆኑ ካድሬዎች የሚያመቻቸውን ስያሜ በጽሑፍ ስለተጠቀሙ ብቻ የአገዛዛቸው ይዘት መገለጫ ማድረግ ስህተት ይመስለኛል፡፡ ለማወናበጃ የሚጠቀሙበትን ሁሉ በቁም ነገር ወስደን ጊዜአችንን ማባከን ተገቢ አይደለም፡፡ ስለሆነም አገዛዞች ለማጭበርበር ካልሆነ በቀር ልማታዊ መንግሥት (የወያኔ አገዛዝ ሆኖም አያውቅ) አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ሊበራል ዴሞክራሲ፣ ሶሻል ዴሞክራሲ፣ ካፒታሊዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝም ባጠቃላይ የትኛውም ‹ኢዝም› ገብቷቸው አይደለም የቃሉን ኳኳታ የሚያሰሙት፡፡ በርጕም ወያኔ ዘመን (የአሁኑን ጨምሮ) የነገሠውን አገዛዝ ርእዮተ ዓለምም ሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት መለያ ጠባዩን/ገፅታውን ማስቀመጥ (characterize ማድረግ) ካስፈለገ ለባለሙያዎቹ ብንተውላቸው ይሻላል፡፡ ተግባራዊ ጉዳይ ከመሆኑ ይልቅ አካዳሚያዊነቱ ያመዝናል፡፡ 

በመሆኑም ትኩረታችንን አገርና ወገንን የማዳን ተግባር ላይ ብናደርግ ይሻላል፡፡ ለዚህም ሁላችንን የሚመለከቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ማንሳትና በጋራ መፍትሄ መፈለግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

እነዚህ ሁሉ ተደምረው ባለአእምሮ ለሆነ ሰው የሚሰጡት አገራዊ ሥዕል ምንድን ነው? የአገር መፈታት ሁነኛ ምልክት አይደለም? ኢትዮጵያን ለመታደግ የሚደረግ ትዕግሥትና ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ይመስላችኋል? በጭራሽ!!! ስለሆነም፣

በጭራሽ ወደማይቀለበስ ሁኔታ ውስጥ ከመግባታችን በፊት በጋራ የጋራ መኖሪያችንን የምናተርፈው መቼ ይሆን? 

የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያንገበግባችሁ እውነተኛ ምሁራንና ሌሎች በተለያየ የሕይወት መስክ ዕውቀትና ልምድ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን፤ ያልተደራጀ የሕዝብ ዓመፃ እንዴት ለመሠሪዎችና ጮሌዎች ሲሳይ እንደሆነና ያስከተለውንም ውጤት በዚህ የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ በቅጡ የታዘባችሁ ይመስለኛል፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ዝንባሌ ያላችሁ የፖለቲካ ማኅበር በማቋቋም፣ ሌሎቻችንም ሲቪክ በሆነ ማኅበረሰብ አቀፍ እንቅስቃሴ ሕዝብን አደራጅተን በቅድሚያ ኢትዮጵያን በማዳን፣ ቀጥሎም አገዛዝን በማስወገድ ለልጅ ልጆቻችን የሚሸጋገር ሥልጡንና የተሻለ መንግሥተ ሕዝብና ሥርዓት የምናቆምበት ጊዜ አሁን አይደለም ወይ?

አምላከ ኢትዮጵያ ሁላችን የየድርሻችንን በቅንነት እንድንወጣ ኃይሉን፣ ጽንዑን፣ ብርታቱን ማስተዋሉን ያድለን፡፡ የመሠሪዎችን ወጥመድ ይበጣጥስልን፡፡ አሜን፡፡