- 26 ኖቬምበር 2019

ባለፈው ሳምንት አርብ ጃዋር በዋሽንግተን ዲሲ አንድ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከህዝብ ጋር ለመወያየት ባዘጋጀው መድረክ ላይ ላይ ተገኝተው የነበሩት ቀሲስ ሳሙኤል ብርኃኑ ጃዋርን ለመቀበል በመውጣቴ ከስራ ታግጃለሁ ማለታቸው መነጋገሪያ ሆኗል።
በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የምትገኘው የደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ክፍል አስተባባሪ የሆኑት ቀሲስ ሳሙኤል ብርኃኑ ከቤተክርስቲያኗ ኃላፊ መልዕክት እንደደረሳቸውም ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ የሆኑት ዶ/ር አማረ ካሳዬ በበኩላቸው “አባ ሳሙዔል አልተባረሩም” ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አባ ሳሙዔል ስብሰባው ላይ የተገኙት በኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት ተጋብዘው እንደሆነ በመግለጽ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ ራሳቸው በወቅቱ ጃዋርን በሚቃወመው ሠልፍ ላይ ታድመው ነበር ብለዋል።
ዶ/ር አማረ በበኩላቸው አባ ሳሙዔል የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በትርፍ ሰዓታቸው አነስተኛ ክፍያ እየተከፈላቸው የሚያገለግሉ ካህን ናቸው እንጂ የእኛ ቋሚ ተቀጣሪ አይደሉም ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ።
• ታዳጊዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረጋቸው ሊያስጨንቀን ይገባል?
• እቴጌ፡ የጡት ካንሰርን በቀላሉ በስልክዎ መለየት እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አባ ሳሙዔል እኔ ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም አይደለም የወጣሁት በማለት “ፀሎት በኦሮምኛ እንዳደርግ በማህበረሰቡ ተጋብዤ ስብሰባውንም ተካፍያለሁ” ካሉ በኋላ ስብሰባውን ጨርሰው ከወጡ በኋላ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ ቀሲስ አማረ ካሳዬ መልዕክት እንደደረሳቸው ይናገራሉ።
ቀሲስ አማረ እንዲሁ የኦሮሞ ማህበረሰብ ለአባ ሳሙዔል ያቀረበላቸውን ጥሪ አንደነገሯቸው አስታውሰው እንዲሄዱ እንደፈቀዱላቸው፣ የጃዋርን መገኘት ግን እንዳላነሱላቸው ያስታውሳሉ።
የጃዋርን መገኘት ቢነግሯቸውም ኖሮ “ሃሳብ እሰጠዋለሁ እንጂ አልከለክለውም… መገኘት መብቱ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።
አባ ሳሙዔል በበኩላቸው የጃዋር መሐመድ አቀባበል ላይ ዋና ተዋናይ ነበርክ፤ በማለት ድርጊታቸው ሥራ አስኪያጁንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ምዕመናንን ማስቆጣቱን በመግለጽ “የእኔ ልጅ፣ ላንተም ለቤተ ክርስቲያኒቷም ደህንነት ሁኔታውን እስክናጣራ ድረስ አገልግሎት ላይ እንዳትገኝ ታግደሃል” የሚል ደብዳቤ እንደደረሳቸው ነግረውናል።
እኔ የተገኘሁት ጸሎት ለማድረግ ነው ያሉት አባ ሳሙዔል ደብዳቤውን የጻፉት ቀሲስ አማረ ራሳቸው በስብሰባው ላይ ተገኝተው እንደነበር ተናግረዋል።
ቀሲስ አማረ በበኩላቸው ሰልፉ ላይ መገኘታቸውን አረጋግጠው፤ ከሠልፉ በኋላ በርካታ ምዕመናን እየደወሉ ቅሬታ ማቅረባቸውን ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ሊያነጋግሯቸው ፈልገው ወደ ግል ስልካቸው ደጋግመው የደወሉ ቢሆንም ሊያገኟቸው አለመቻላቸውን በመጥቀስ ይህ የተፈፀመው ቅዳሜ በመሆኑ እሁድ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቷ ቢመጣ ሊፈጠር የሚችለውን ግርግር ለማስቀረት በሚል “የእኔ ልጅ ጃዋር ስብሰባ ላይ መገኘትህ እኔንም ሕብረተሰቡንም አሳዝኗል፤ በዚህ ምክንያት ላንተም ደህንነት ለቤተ ክርስቲያኒቷም ሲባል በነገው ዕለት እንዳትመጣ ወደፊት የሚደረገውን እንወስናለን” ብለው በስልክ መልዕክት መላካቸውን ያስረዳሉ።
ሕዝቡ በጃዋር ላይ ተቃውሞውን ያሰማው “ኦሮሞ ስለሆነ ወይንም ሙስሊም ስለሆነ ሳይሆን በድርጊቱ ነው” የሚሉት ቀሲስ አማረ እርሳቸውም ማዘናቸውን ይናገራሉ።
አባ ሳሙዔል፤ የቤተክርስቲያኒቷ ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ አማረ ‘ጃዋር ቤተ ክርስቲያን እንዲቃጠል ሲያደርግ ነበር፤ የቤተ እምነቱ ተከታዮችንም ሲያስገድላቸው ነበር’ በማለት ተቃውሞ ለማሰማት ከወጡ ሰዎች ጋር ነበሩ ያሉ ሲሆን ቀሲስ አማረ ይህንን ማድረጋቸውን አምነዋል።
ይህንን ያደረግኩት ግን “ነገሩ በጣም ስለከነከነኝና ስላሳዘነኝ እንጂ” መውጣትም አልነበረብኝም፤ መውጣትም አልፈልግም ነበር ሲሉ ያብራራሉ።
ቀሲስ አማረ አክለውም ይህ የቤተ ክርስቲያናችን አቋምም ነው በማለት “ክርስቲያን በመሆን ብቻ መገደልን መገፋትን” እንደሚቃወሙ ይናገራሉ።
አባ ሳሙዔል በበኩላቸው ጃዋር በሚመራው ስብሰባ ላይ ተገኝተው የሚቀርብበትን ክስና ወቀሳ በመጠየቅ መልስ ለማግኘት መሄዳቸውን ይናገራሉ።
ቀሲስ አማረ በበኩላቸው “አባ ሳሙዔልን ያስመጣኋቸው እኔ ራሴ ነኝ፤ የተቀበልኳቸውምና አገልግል ያልኩት እኔ ራሴ ነኝ። ኦሮሞ በመሆናቸው ምንም የተፈጠረ ነገር የለም” ሲሉ ያስረዳሉ።
እንዲህ አይነት ስብሰባ ለእኔ አዲስ አይደለም የሚሉት አባ ሳሙዔል በበኩላቸው ከዚህ በፊትም አንዱዓለም አራጌ ወደ አሜሪካ በሄደበት ወቅት በቤተ ክርስቲያን ተጋብዞ ፀሎት ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ።
• “ክስተቱ ‘የግድያ ሙከራ’ እንደሆነ ነው የምረዳው” ጀዋር መሐመድ
• ወደ ኦሮሚያ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት መሰማራቱ ተገለፀ
“ከጃዋር ጋርም የተለየ ነገር አላደረግንም” የሚሉት አባ ሳሙዔል፤ “በተመሳሳይ የሀገሪቷን ሁኔታ ተነጋግረን እኛም በአገራችን ጉዳይ ለመወያየትና ለመካፈል መብት ስላለን ገብተን ተወያይተን ወጣን” ብለዋል።
የትላንትናው ደብዳቤ እንዴት እንደተጻፈ ባላውቅም ከዚህ በፊት ግን በተመሳሳይ መድረክ ላይ ተገኝቼ ፀሎት አድርጌ አውቃለሁ የሚሉት አባ ሳሙዔል፤ ከስብሰባው በኋላ ጃዋር ‘ፀልዩልን ቤተክርስቲያንም ይሁን መስጂድ የሚጠብቁት ቄሮና ቀሬ ናቸው፤ ስለዚህ እናንተም በፀሎት ከጎናችን እንዳትለዩን’ በማለት ተነጋግረን በሰላም ተለያየን ይላሉ።
አክለውም ከስብሰባው እንደወጡ ከሥራ መታገዳቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ሲደርሳቸው ሀዘን እንደተሰማቸው ይናገራሉ።
ቀሲስ አማረ በበኩላቸው “የማከብረው የምወደው ልጄ ነው፤ መልዕክቱንም ስልክለት ልጄ ብዬ ነው የላኩት። አሁንም ልጄ ነው የምለው እርሱ እንደዚህ ሆኖ በመጥፋቱ በጣም ነው ያዘንኩት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።