SourceURL:https://www.bbc.com/amharic/50513606 እቴጌ፡ የጡት ካንሰርን በቀላሉ በስልክዎ መለየት እንደሚችሉ ያውቃሉ? – BBC News አማርኛ
- 26 ኖቬምበር 2019

ቤተል ሳምሶን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጥቁር አንበሳ የሕክምና ትምህርት ቤት የአምስተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪ ናት። ቤተል፣ የሕክምና ተማሪዎች ማህበር ውስጥ በአባልነት የምትሳተፍ ሲሆን በስነ ተዋልዶና ኤች አይ ቪ ላይ የሚሰራን አንድ ኮሚቴ በዳይሬክተርነት ትመራለች።
የሕክምና ባለሙያ ከሆኑት አባቷና ከሥነ-ሕንፃ ባለሙያ እናቷ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልዳ ያደገችው ቤተል የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ናዝሬት ስኩል ነው የተከታተለችው።
ለኔም ሆነ ለወንድሜ ሕክምና ማጥናት የቤተሰቦቼ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም የምትለው ቤተል፣ በናዝሬት ስኩል ስትማር በሴቶች ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ላይ እንዳታተኩር የሚያስችላትን ምክር ከመምህራኖቿ ተቀብላለች።
“ሴቶች ትምህርት ቤት መማሬ…” ትላለች ቤተል፣ “…ሁል ጊዜ የሚነገረን እኛ ዕድለኛ መሆናችንና በርካታ ሴቶች እኛ ያገኘነውን እድል ስለማያገኙ የሴቶችን ሕይወት ለመለወጥና ለማሻሻል መሥራት እንዳለብን ነበር።”
የሕክምና ተማሪዎች ማሕበር ውስጥ ከገባች በኋላ የበጎ አድራጎት ሥራ አልያም የሕክምና ትምህርቱን ለማዘመን፣ ካልሆነ ደግሞ የማሕበረሰብ ጤና ላይ መሥራት እንደምትችል አማራጮች ቀረቡላት።
• ከማህጸን ስለሚወጣ ፈሳሽ ምን ያህል ያውቃሉ?
• የወንድሙን ገዳይ ለመበቀል ወደ ፈጠራ ሥራ የገባው ኢትዮጵያዊ
ያኔ ነው እናቶችና ሕፃናት ላይ ከስነ ተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዙ ነገሮችን ለመሥራት የወሰነችው።
ሴቶች ላይ ለመሥራት ስትወስን ሃሳቡ ከባህር በላይ ሰፊ እንደሆነባት ታስታውሳለች፤ ስለዚህ ከሴቶች መብት ጋር በተያያዘ፣ የሴቶች ጥቃትን ለማስቆም የስነተዋልዶ ትምህርት ለመስጠት እንዲሁም የጡትና የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ላይ ብትሠራ እንደምትወጣው ተረዳች።
ይህንን ፍንጭ ለማግኘት የረዳትን ስታብራራም በማሕበር ውስጥ ‘ደብል ኢምፓክት’ የተባለ ፕሮጀክት መኖሩ ነው ትላለች። ደብል ኢምፓክት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደማለት ነው።
ስለ ካንሰር ሲያስተምሩ የጡትና የማሕፀን ጫፍን በጋራ ማስተማር እንደማለት።
በተለያዩ ተቋማት እየሄደች ስለጡትና ስለ ማህፀን ጫፍ ካንሰር ታስተምራለች፣ ጡታቸውን ራሳቸው እንዲፈትሹ፣ አልትራ ሳውንድና የማሞግራፊ ምርመራ እንዲያደርጉ መልዕክት ታስተላልፋለች።
የማህፀን ጫፍ ካንሰርንም ቢሆን በአቅራቢያቸው በሚገኝ የጤና ጣቢያ ጎራ በማለት እንዲመረመሩ ታበረታታለች። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ለማስተማሪያነት አልያም ለመርጃ መሣሪያነት የሚያገለግል በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተዘጋጀ መርጃ ልታገኝ አልቻለችም።
ያኔ እቴጌ ተፀነሰች።
እቴጌ ስትፀነስ ግን ከእርሷ ጋር አብረውት የሚማሩት፤ ሜሪ መሬሳ፣ መህቡባ በጊቾ፣ ቅድስት ዓለም ሰገድ አብረውኝ ነበሩ ትላለች።

በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ
ካንሰር ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው። በዓለማችን ላይ ካንሰር ብቻውን በየዓመቱ 7.9 ሚሊየን ሰው እንደሚገድል ጥናቶች ያሳያሉ። ምንም እንኳ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ውስጥ አሁንም በገዳይነት ግንባር ቀደምነቱን የያዙት ተላላፊ በሽታዎች ቢሆንም እንደ ካንሰር ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችም እያደጉ ይገኛሉ።
ከሁሉም የካንሰር ዓይነቶች የጡት ካንሰር የከፋ መሆኑን የሚያሳየው እ.ኤ.አ. በ2018 የተደረገ ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመዘገቡ የካንሰር ሕሙማን ቁጥር 25.5 በመቶው የጡት ካንሰር የተያዙ መሆናቸውን ያሳያል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳው በመላ ሀገሪቱ ከሚከሰቱ ሞቶች ካንሰር 5.8 በመቶውን ድርሻ ይይዛል። በኢትዮጵያ በካንሰር ታምመው ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች አብዛኛዎቹ በሽታው ከተሰራጨና ደረጃው ከፍ ካለ በኋላ እንደሚመጡ ቤተል ትናገራለች።
• አመጋገባችን ማረጥን ሊያፋጥን ወይም ሊያዘገይ ይችላል
• “ዓላማችን ችግሮችን ፈተን ገንዘብ ማግኘት ነው ” የጠብታ አምቡላንስ ባለቤት
• የሃምዛ ሃሚድ ገመድ አልባ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ
በዓለማችን ላይ በስፋት ከሚታዩት የካንሰር ዓይነቶች መካከል የሳንባና የጡት ካንሰር ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ በኢትዮጵያም የጡትና የማህፀን በር ካንሰር ቀዳሚውን ተርታ ይይዛሉ።
በሀገሪቱ ውስጥ በካንሰር ተይዘው ከሚሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸውንም ጥናቶች ያሳያሉ።
ቤተል የጡትና የማህፀን ጫፍ ካንሰርን ስታስተምር ባገኘችው መርጃ መሣሪያ ተነሳስታ የእቴጌ መተግበሪያን ለመሥራት መወሰኗን ለቢቢሲ ትናግራለች።
ቤተልና ጓደኞቿ፣ የጡትና የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ማስተማሪያ መሣሪያዎችን ማዘጋጀት ሲያስቡ የተለያዩ አማራጮች በቅድሚያ ተነስተው እንደነበር አትዘነጋም።
ስለ በሽታው የተንቀሳቃሽ ምስል ብናዘጋጅ ሴቶች ስልካቸው ላይ ጭነውት ምን ያህል ጊዜ ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚለውን ከግምት አስገብተዋል።
ከዚህም ተነስተው የስልክ መተግበሪያ ቢሆን፣ የቀን መቁጠሪያ በማካተትም በየወሩ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ለማድረግ እንዲያስታውሳቸው ተደርጎ ሊሰራ እንደሚችል በመረዳታቸው መተግበሪያውን ለመሥራት ወሰኑ።
ይህ መተግበሪያ ስልክ ላይ ተጭኖ በየወሩ የሚያስታውስ ከሆነ፣ አንዲት ሴት ራሷን በየወሩ በመፈተሽ ጤናዋን መጠበቅ፣ ካንሰር ከተከሰተም ሳይባባስ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደምትችል ታስረዳለች።

አሰሳ ማህበራዊ ሚዲያ
ቤተል የሕክምና ተማሪ እንደመሆኗ ሀሳቡ እንጂ መተግበሪያውን የመሥራት አቅሙም ሆነ ችሎታው አልነበራትም። ስለዚህ አንዳንድ ድርጅቶችን በር ለማንኳኳት የማህበራዊ ድረገ ጾችን ማሰስ ጀመረች።
ሊንክድኢን ላይ ዞካ አይቲ ሶሊውሺንስ፣ ቴሌግራም ላይ ደግሞ እዝራ ደሜን አገኘቻቸው። ያሰበችውን ስታካፍላቸውም ተገናኝተው ቁጭ ብሎ ለማውራት ቀጠሮ ያዙ።
እነዚህ አካላት ስለቤቲ ፕሮጀክት ሲሰሙ ደስተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ሥራውን ወዲያው ለመጀመር ዓይናቸውን አላሹም።
የዞካ አይቲ ሶሊውሺንስ መስራችና ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ብርሃኔ፣ በነፃ ለመስራት ፈቃደኛ ሆነ። ዞካ አይቲ ሶሊውሺንስ ሶፍትዌርን መስራትና የመረጃ ደህንንት ላይ ስልጠና የሚሰጥ በመሆኑ መተግበሪያውን ሰርተዋል።
• “ወንዶች በጡት ካንሠር እንደሚያዙ አላውቅም ነበር”

አቶ ብሩክ ብርሃኔ ቤተል ወደ ድርጅታቸው ስትመጣና ስትነግራቸው ለምን መተግበሪያውን ለመሥራት እንደተስማሙ ሲናገሩ፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት 64 ሚሊየን የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ መኖሩን በማንሳት ነው።
ከእነዚህ መካከል 18 ሚሊየኑ የኢንተርኔት ዳታን የሚጠቀም መሆኑን በማከል እንዲህ ዓይነት የጤና መልዕክቶች በቀላሉ በስልክ ላይ እንዲሠሩ መሆናቸው፣ ለተጠቃሚ በቀላሉ ተደራሽ ያደርጋቸዋል ሲሉ ይናገራሉ።
ከ18 ሚሊየኑ የሴቶች ቁጥርም ቀላል አይሆንም የሚሉት አቶ ብሩክ፣ በአንድሮይድ ስልኮች ላይ የሚሠራ መተግበሪያ መስራታቸውን ያስራሉ።
በሀገራችን አብዛኛው ሰው የሚጠቀመው አንድሮይድ ስልክ ነው የሚሉት አቶ ብሩክ፣ ለዚህም ቅድሚያ በመስጠት መስራታቸውን ይናገራሉ።
ድርጅታቸው ይህንን መተግበሪያ ለመሥራት ከካዝናው፣ በጥሬ ገንዘብ ብቻ ከ50 ሺህ ብር በላይ ማውጣቱን ተናግረው ከዚህ መተግበሪያ የሚያገኙት ምንም ክፍያ እንደሌለ ይጠቅሳሉ።
እዝራ ደሜ በበኩሉ በሥነ-ሕንፃ የተመረቀ ቢሆንም በግሉ የተለያዩ የአኒሜሽኖችን ሥራዎችን ይሠራ ስለነበር እቴጌን፣ መተግበሪያው ላይ እንደሚታየው መልዕክቱ ሴቶች እንዴት ጡታቸውን በመንካት ለካንሰር ተጋልጠው መሆን አለመሆኑን እንደሚፈትሹ የሚያሳየውን በአኒሜሽን መታየት በሚችል መልኩ የመሥራት ኃላፊነቱን በመውሰድ ሠራ።
ቤተል ከዞካዎችም ሆነ ከእዝራ ጋር መተግበሪያው ላይ ምን ምን ነገሮች መግባት እንዳለባቸው የሚለውን በዝርዝር ቁጭ ብላ መሥራቷን፣ እነርሱ በበኩላቸው ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ሁሉ መወጣታቸውን ትናገራለች።
መተግበሪያው በአሁኑ ሰዓት በጉግል ፕሌይ ስቶር ላይ ተጭኖ እንደሚገኝ የምትናገረው ቤተል፣ ወደ ፊት መሻሻል ያለባቸውን ለማሻሻል ሀሳብ መኖሩን አልሸሸገችም።

እቴጌ ለምን?
በመተግበሪያው ላይ ተቀርጻ መልዕክት የምታስተላልፈው ሴት፣ በተቻለ አቅም ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖራት እና ኢትዮጵያዊ ባህል እንድታንፀባርቅ ማድረጋቸውን ቤተል ትጠቅሳለች። በዚያ ላይ ይህንን መተግበሪያ ለመስራት ከመነሻው ጀምሮ አብረዋት የነበሩ፣ ጓደኞቿ፣ ሀሳቡን ስጋ በማልበስ፣ ነፍስ በመዝራት አብረዋት በመሆናቸው እቴጌ የሚለውን ስም መርጠናል ስትል ታስረዳለች።
ሴቶች በተለያየ ማህበራዊ ግንኙነታቸው ጤናንም አንስተው ስለሚወያዩ፣ ሴቶች ለሌላ ሴቶች የጤና ምክር እንዲሰጡ ለማድረግ በማሰብ አኒሜሽኗ ከሕክምና ባለሙያ ይልቅ በዕለት ተዕለት የምናገኛት ዓይነት ሴት የምትመስል ገፀባህሪን መጠቀማቸውን ታብራራለች።
የስሟም እቴጌ መሆን ተጠቃሚው ሲሰማም በቀላሉ ለመረዳትና ለመቀበል እንደሚያደርገው በማሰብ መሆኑንም ትገልጻለች።
እዝራ ደሜ፣ እቴጌን መጀመሪያ ሥሠራት ወጣት ነበረች ሲል ያስታውሳል፤ ነገር ግን ቤቲ እድሜዋ ሰላሳዎቹ ውስጥ ቢሆን የተሻለ እንደሚሆን ሀሳብ በማቅረቧ አሁን ያለውን መልክና ዕድሜ መያዟን ይናገራል።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የጡት ካንሰር አብዛኛው የሚያጠቃቸው ሴቶች ዕድሜያቸው በሰላሳዎቹ ውስጥ ያሉትን በመሆኑ እንደሆነ መናገሯን ይገልጻል።
እቴጌ መጀመሪያ ሥትሠራ የገጠሩ ማህበረሰብ የሚለብሰው አረንጓዴ ሸማ ቀሚስ፣ ኮንጎ ጫማ አድርጋ እንደነበር በመግለጽም፣ በኋላ ግን አስተያየቶችን በመቀበል የጥበብ ልብስ እንድትለብስ መደረጉን ይናገራል።
መተግበሪያው በአሁኑ ሰዓት በአማርኛ ብቻ እንደሚሠራ የምትናገረው ቤተል፣ በቀጣይ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ለመጨመር ማሰባቸውን ታስረዳለች።
አቶ ብሩክ ዋናው ሀሳባችን ሰዎች ጭነውት ጤናቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ብቻ ነው በማለት ድጋፍ ቢገኝ በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መሥራት እንደሚቻል ይናገራሉ።
ይህንን መተግበሪያ የሰራነው የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት ብቻ ነው የሚሉት አቶ ብሩክ፣ በሽታውን ቀድሞ ማወቅ የመከላከሉ ግማሽ አካል በመሆኑ መረጃውን ለማዳረስና የበርካታ ሴቶች ህይወትን መታደግ አላማቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
እዝራ በበኩሉ ይህንን መተግበሪያ ከካንሰር ውጪም ወደ ሌላ የተለያዩ በሽታዎችን ለማስተማር መጠቀም እንደሚቻል ያስባል።