- 3 ዲሴምበር 2019

የወላይታ ዞን በክልል የመደራጀት ጥያቄን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከወላይታ ሕዝብ ተወካዮች ጋር ትናንት ሕዳር 21/2012 ዓ.ም በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ከውይይቱ በኋላ ያነጋገርናቸው የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የወጣቶች ክንፍ አመራር አቶ አሸናፊ ከበደ ፤ በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ካቀኑት አባላት መካከል ይገኙበታል።
• የወላይታ ዞን ተወካዮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ሊወያዩ ነው
• የሲዳማ ሕዝበ-ውሳኔ፡ አዲስ ክልል፤ አዲስ ፈተና?
አቶ አሸናፊ እንደገለፁልን ውይይቱ በአጠቃላይ የወላይታን ሕዝብ የክልል እንሁን ጥያቄን የተመለከተ ነበር።
ውይይቱ በዋናነት ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወላይታ ሶዶ በሔዱበት ወቅት “ተወያዩበት፤ ምከሩበት” ባሉት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በዚሁ መሠረት ውይይት ያደረጉበትን ሃሳብ ይዘው ወደ ውይይት መቅረባቸውን አቶ አሸናፊ ያስረዳሉ።
ከዚህ ቀደም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉትን ውይይት የሚያስታውሱት አቶ አሸናፊ፤ በወቅቱ የነበሩት አጀንዳዎች ሦስት እንደነበሩ ያወሳሉ።
“የወላይታ ሕዝብ ብቻውን ክልል መሆን ነው ወይ?፣ ሌሎችን ይዞ ከአጎራባች ዞኖች ጋር ክልል መሆን ነው ወይ? አጠቃላይ ሌሎች 55ቱን ይዞ ሠፊ ሕዝብና መሬት፣ ሰፊ የተማረ ሰው ያለበት በመሆኑ አንደ ዋና መቀመጫ እንዲያገለግል በሚል ዙሪያ ነበር የተወያየነው” ይላሉ።
በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ አቋማቸውን ማስቀመጣቸውን ይገልፃሉ።
በመሆኑም ክልል የመሆንን ጥያቄ የወላይታ ሕዝብ ብቻውን የሚወስነው ባለመሆኑ፤ ተጨባጭነቱም ሊረጋገጥ ስለማይችል በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር እንደማይችል እንዲሁም አጎራባች ያሉ ዞኖች ጋር አንድ ክልል መሆንንም አንደ አማራጭ የወላይታ ሕዝብ ተወያይቶበት፤ ሌሎች ከመጡ ማቀፍ እንደሚችል ከዚያ ውጭ ግን በሌሎች እጣ ፈንታና መብት ውስጥ ገብቶ መወሰን የወላይታ ሕዝብ ሥልጣን አለመሆኑን ተነጋግረውበታል።
እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ውይይት መነሻነት ወላይታ ራሱን ችሎ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፤ ወላይታ ሶዶን ደግሞ ማዕከል አድርጎ የራሱን ክልል እንዲመሠርት የሁሉም ሕዝብ ድምፅ በመሆኑና ሕገ መንግሥታዊ መብት ስለሆነ ሌሎች አማራጮች እንዳማይሠሩና እንደማያዋጡ ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን ያስታውሳሉ።
የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች ትናንት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት የደረሱባቸውን ሃሳቦች አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ ከሆነ ጥያቄውን እርሳቸው እንደማይመልሱት በመግለፅ፤ በሕጉ መሠረት እንዲሄድ ከምርጫ ቦርድ ጋር እንደሚነጋገሩ እዚያው ምላሽ በመስጠት ለቀሪ ጉዳዮች በተወካዮች በኩል ሰፋ ያለ ምላሽ እንደሚሰጡ እንደገለፁላቸው አቶ አሸናፊ ነግረውናል።
“የወላይታ ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ራሱን በክልል አደራጅቶ መምራት መሆኑን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀን ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሌሎች አማራጮችን አይታችኋል ወይ ተማክራችኋል ወይ?” የሚል ጥያቄ አቅረበውላቸው እንደነበር ይጠቅሳሉ።
ይሁን እንጅ የቀረቡት አማራጮች ሁሉ የሕዝብ ጥያቄ ባለመሆናቸው፤ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄም ባለመሆናቸው በሕገ መንግሥቱ መሠረት የወላይታ ሕዝብ የሚጠይቀው የራሱን በሕገ መንግሥት የተቀመጠውን መብት እንጅ የሌሎችን እጣ ፈንታ በሚወስን መልኩ መጠየቅ አይችልም በሚል ውሳኔ ላይ የተደረሰበትን የሕዝብ አቋም አንፀባርቀው መውጣታቸውን ይናገራሉ።
ወላይታ ክልል እሆንበታለሁ ያለውን ቀነ ገደብም ታህሳስ 10/2012 ዓ.ም አድርጎ አስቀምጧል።
ቀነ ገደብ ማስቀመጡ ምን ያህል ያስኬዳል? ያልናቸው ተወካዩ፤ “በሕገ መንግስቱ መሠረት አንቀፅ 47/42 በተቀመጠውና በሌሎች አንቀፆች የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የምርጫ ቦርድ በአንድ ዓመት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ያደራጃል ይላል” ሲሉ አንቀፅ ይመዛሉ።
በመሆኑም ሕዝበ ውሳኔውን እንዲያደራጁ ታህሳስ 10 አንድ ዓመት ይሞላል፤ ከዚህ በኋላ ጥያቄው መመለስ ካልተቻለ ሕዝቡ ቀኑን ጠብቆ የራሱን ሉዓላዊ ሥልጣን ይጠቀማል ብለዋል።
ይሁን እንጅ በሲዳማ የተፈጠረውን ስህተት ለመድገም እንዳማይፈለግ ገልፀዋል።
“ሰላማዊ በሆኑ መንገዶች በሙሉ ታህሳስ 10 ሕዝበ ውሳኔው የሚካሄድበት ቀን ካልታወቀ፤ የራሱን ውሳኔ አሳውቆ አቋሙን ገልፆ ፤ቀጣይ ሰላማዊ ትግሎች በሌሎች መንገዶች ይሄዳሉ” ብለዋል።
በዚህ ሒደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ካሉም የክልሉ መንግሥትና የፌደራል መንግሥት ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።