የኢትዮጵያ ብር

ኢትዮጵያ የባንክና የኢንሹራንስ ተቋማትን ለውጪ ባለሃብቶች ተሳትፎ ክፍት እንደማታደርግ ሮይተርስ ጉዳዩን በሚመለከት የተዘጋጀን ረቂቅ ሕግን ዋቢ አድረጎ ዘገበ።

ኢትዮጵያ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለውጪ ባለሃብቶች ክፍት ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ቢሆንም የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፎች ግን አሁንም ዜጎቿ ብቻ የሚሳተፉባቸው መስኮች ሆነው እንዲቆዩ ልታደርግ መሆኑን ሮይተርስ አየሁት ባለው ረቂቅ ሕግ ላይ ሰፍሯል ብሏል።

የተለያዩ የውጪ ባለሃብቶችና ተቋማት ኢትዮጵያ ክፍት ታደርጋቸዋለች ተብለው የሚጠበቁ ተቋማትን ለመግዛትና በመንግሥት እጅ ስር ብቻ ተይዘው በነበሩ ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት እየገለጹ ነው።

እየበረታ በመሄድ ላይ ያለው የዋጋ ንረት አዙሪት

“ኢስላማዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዳል?”

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግና ኢትዮጵያን ወደ መካከለኛ ገቢ ለማሳደግ በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበሩ ዘርፎች ላይ የውጪ ባለሃብቶች ክፍት እንደሚሆኑ ተገልጾ ነበር።

ሮይተርስ የጠቀሰው ረቂቅ የኢንቨስትመንት ሕግ ላይ እንዳመለከተው የባንክ፣ የኢንሹራንስ፣ አነስተኛ የቁጠባና የብድር የገንዘብ ተቋማት ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ የተተዉ ዘርፎች ይሆናሉ።

የአገሪቱ የባንክ ዘርፍ በአፍሪካ በመንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግ ነው።

ባለፈው ሐምሌ የአገሪቱ ምክር ቤት አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የባንኮችን አክሲዮን ለመግዛት እንዲችሉ የሚፈቅድ ሕግ ሲያወጣ፤ በበርካቶች ዘንድ ቀስ በቀስ ዘርፉ ለውጪ ባለሃብቶችም ክፍት ሊደረግ ይችላል የሚል ተስፋን ፈጥሮ ነበር።

በስህተት የተሰጣቸውን 1 ሚሊየን ብር የመለሱት መምህር

እውን ድህነትን እየቀነስን ነው?

በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተወሰዱ ካሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች መካከል ትላልቆቹን የስኳር ማምረቻ ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዞታነት የማዘዋወሩ እርምጃ ከወራት በኋላ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም መንግሥት ለሁለት የሞባይል ስልክ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ፈቃድ ለመስጠትና የመንግሥት ንብረት ከሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ላይ ደግሞ የተወሰነ ድርሻን ለባለሃብቶች ለመሸጥ ዕቅድ አለው።

በሮይተርስ የተጠቀሰው ረቂቅ የኢንቨስትመንት ሕግ በቀጣዮቹ ሁለት ወይም ሦስት ሳምንታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት እየጨመረ የሚሄድና ወጣት ሕዝብ ያላት ሲሆን ኢኮኖሚዋም ከአስር ዓመታት በላይ በሁለት አሃዞች ሲያድግ ቆይቷል። ነገር ግን በአገሪቱ የሚስተዋለው ብሔርን መሰረት ያደረገ ውጥረትና ግጭት ኢኮኖሚው ላይ ስጋትን ፈጥሯል።