SourceURL:https://www.bbc.com/amharic/news-50583016 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለማህጸን ለካንሰር መከላከያ ክትባት ከሚሰጡ ጥቂት አገራት አንዷ ናት – BBC News አማርኛ
- 28 ኖቬምበር 2019

የማህጻን በር ጫፍ ካንሰር በመላው ዓለም ለሴቶች ሞት ምክንያት ከሆኑት የካንሰር አይነቶች መካከል አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በአፍሪካ ግን ይህ በሽታ ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል በተለየ መልኩ በከፍተኛ ደረጃ ገዳይ ነው፤ ምንም እንኳ ቀድሞ መከላከል ቢቻልም።
በሩዋንዳ የተጀመረው በሽታውን የመከላከል እንቅስቃሴ ውጤትማ መሆኑን ተከትሎ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የሩዋንዳን ተመሳሌት መከተል ጀምረዋል።
አንጀሊን ኡሳናሴ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ትኖራለች። የ67 ዓመት አዛውንቷ አንጀሊን በማህጻን በር ጫፍ ካንሰር ህይወቷ እንዴት እንደተቀየረ ታስታውሳለች።
ስለኤችፒቪ ማወቅ ያለብዎ ነገሮች
የበለጠ ለማወቅ ጥያቄዎቹን ይጫኑ 1. ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ (ኤችፒቪ) ምንድን ነው?
ልክ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ነበር ድንገት በሙታንታዋ ላይ ደም የተመለከተችው። የ67 ዓመት ሴት መቼም የወር አበባ ልታይ አትችልም። እንዲህ አይነት ምልክት በእራሷ ላይ ካየች ዓመታት አልፈዋል።
“በአቅራቢያዬ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሄድኩኝ። ከዚያም ሃኪሞች የማህጻን በር ጫፍ ካንሰር ምረመራ እንዳደርግ ነገሩኝ። የምረመራ ውጤቱ ሲመጣ በሽታው እንዳለብኝ አሳየ። በጣም ተደናገጥኩ። ልቀበለው አልቻልኩም። የምሞት መሰለኝ” በማለት የነበረውን ሁኔታ ታስታውሳለች።
አንጀሊን በሽታውን በጊዜ ማወቋ እና የህክምና ዕርዳታ ማግኘቷ ህይወቷን እንደታደረገው ታምናለች።
ስለኤችፒቪ ማወቅ ያለብዎ ነገሮች የበለጠ ለማወቅ ጥያቄዎቹን ይጫኑ 1. ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ (ኤችፒቪ) ምንድን ነው?
ዛሬ ላይ ቢሆን ግን አንጀሊን ይህ በሽታ ባልያዘት ነበር። ምክንያቱም በመላው ሩዋንዳ የተጀመረው የቅድመ ማህጻን በር ጫፍ ካንሰር ምረመራ እና ክትባት በታደጋት ነበር።
ለማህጻን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ መከሰት በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፈው ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ (ኤችፒቪ) አብዛኛውን ጊዜ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።
ምንም እንኳ በአፍሪካ ይህ በሽታ ከፍተኛ ሞት የሚያስከትል ቢሆንም 10 አገራት ብቻ ናቸው የማህጻን በር ጫፍ ካንሰር ክትባትን ለዜጎቻቸው የሚሰጡት።
ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ተጠቃሽ አገር ናት።

በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ አገራት ለዜጎቿ ክትባቱን በብቸኝነት የምታቀርበው ሴኔጋል ናት።
በምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ ለዜጎች ክትባቱን ስለሚያቀርቡ በማህጻን በር ጫፍ ካንሰር የሚከሰተው ሞት ከሌሎች የአህጉሪቱ ቀጠና ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ ነው።
ሩዋንዳ ከስምንት ዓመታት በፊት የጀመረችው ዘመቻ አዎንታዊ ውጤት አስገኝቶላታል። ከ10 ሴቶች 9 ሴቶች ክትባቱን ማግኘት ችለዋል።
ይህ ውጤት ግን ያለፈተና አልነበረም የመጣው።
ክትባቱ የሚያስወጣው ከፍተኛ ገንዘብ እስከ ለክትባቱ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች ሩዋንዳዊያን የተሻገሯቸው ጋሬጣዎች ናቸው።
“አሁንም ቢሆን የማህጻን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ እርግማን ነው በማለት ወደ ሃኪም ከማቅናት ይልቅ ወደ ጠንቋዮች ጋር የሚሄዱ ሴቶች አሉ” በማለት አንጀሊን ትናገራለች።
ከዚህ በተጨማሪ በበሽታው ምክያት ‘ማህጸናችን እንዲወጣ ሊደረግ ይችላል’ የሚለው ስጋት በርካታ ሴቶች ወደ ህክምና እንዳይሄዱ ይገድባቸዋል።
የኤችፒቪ ክትባት በሽታው በወጣቶች መካከል እንዳይስፋፋ በከፍተኛ ደረጃ ያደርጋል
መንግሥት የማኅበረሰብ መሪዎችን፣ አብያተ ክርስቲያናትን፣ የመንደር መሪዎችን፣ የጤና ሰራተኞችን፣ ትምህርት ቤቶችንና የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም በክትባቱ ዙሪያ የሚነዙ አፈታሪኮችን ለማስወገድ ዘመቻ አካሂዷል።
ተማሪ ለሆኑት ልጃገረዶች በትምህርት ቤት ለማይማሩት ደግሞ በየቤታቸው ክትባቱን እንዲያገኙ ተደርጓል።
የጤና ባለስልጣናትም ክትባቱ በተፈለገበት ቦታና ጊዜ ሁሉ በበቂ ሁኔታ በፍጥነት እንዲገኝ አድርገዋል።

ኅብረተሰቡ በስፋት እንዲከተብ የሚያስችለው የመጀመሪያው የክትባት ዘመቻ ከተጀመረ ከስምንት ዓመታት በኋላ ክትባቱ የሩዋንዳ መደበኛ የክትባቶች ዝርዝር ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል።
ምንም እንኳን ሩዋንዳ ያገኘችውን ውጤት የሚያሳይ መረጃ ባይኖርም ተመሳሳይ ዘዴን የተጠቀሙ አገራት ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ላይ የኤችፒቪ በሽታ መስፋፋት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
• “እዚህ ደረጃ የደረስኩት በእርሷ ብርታት ነው” አርቲስት ደመረ ለገሰ
አውስትራሊያ ከ1991 (እአአ) ጀምሮ ሴቶች የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ ማደረግ የተጀመረ ሲሆን ከ12 ዓመት በፊት ደግሞ ክትባቱ መስጠት ተጀምሯል።
የአውስትራሊያ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ክስተት መጠን ከአንድ መቶ ሺህ ሴቶች ሰባት ብቻ ነው፤ ይህም በዓለም ላይ ከሚታየው አማካይ ቁጥር በግማሽ ያመነሰ ነው።
በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ደግሞ ዓመታዊው የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር አዲስ ክስተት በአንድ መቶ ሺህ ሴቶች ወደ ስድስት ዝቅ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።
‘በየቀኑ ዘጠኝ ሴቶች ይሞታሉ’
የሩዋንዳን እርምጃ በመከተል ሌሎች የአፍሪካ አገራት በአሁኑ ጊዜ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ነው።
በጥቅምት ወር የኬንያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ጋር በመተባበር የኤችፒቪ ክትባትን ከመደበኛ የክትባት አይነቶች ጋር እንዲሰጥ ማድረግ ጀምሯል።
በዚህም ዘመቻ እድሜያቸው 10 ዓመት የሆናቸው 800 ሺህ ታዳጊ ሴቶችን በየዓመቱ ለመከተብ ፍላጎት አለው።
“ኬንያ ውስጥ በየቀኑ በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምክንያት ዘጠን ሴቶች ይሞታሉ። ይህንንም ለመከላከል ነው ለልጃገረዶች ክትባት ለአዋቂ ሴቶች ደግሞ ምርመራ የሚደረገው” ሲሉ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኘው የአጋ ካን ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ውስጥ የጽንስና የማህጸን ፕሮፌሰር የሆኑት ማርሊን ተመርማን ይናገራሉ።

ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ የጤና ባለስልጣናት ክትባቱ ካለበት ቀላል የጎንዮሽ ችግር በስተቀር ደህንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ እንደሆነ ቢገልጹም አንዳንዶች አሁንም ጥርጣሬ አላቸው።
“ስለክትባቱ የምሰማው ነገር ስላስፈራኝ የአስር ዓመቷ ልጄን እንድትከተብ አላደረግኩም። ሲከተቡ ሽባ ሊሆኑ ወይም የደም መርጋት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የሚገልጹ ወሬዎች አሉ። ስለክትባቱ ምንም አይነት ትምህርት አልተሰጠንም” የምትለው በኬንያዋ የባሕር ዳርቻ ከተማ ሞምባሳ ነዋሪ የሆነችው እናት ቦንጄ አትማን ናት።
ሃይማኖታዊ ስብስብ የሆነው የኬንያ የካቶሊክ ዶክተሮች ማህበር ግን ክትባቱን ለታዳጊ ልጃገረዶች መስጠት አስፈላጊ አይደለም በማለት ሴቶች ክትባቱን እንዳይወስዱ ጥሪ አቅርቧል። ኤችፒቪንም ለመከላከል ከወሲብ መታቀብ ወይም በአንድ የትዳር አጋር መወሰንን እንደመፍትሄ አቅርቧል።
ሩዋንዳ ውስጥ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰርን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
• የዘር ከረጢት ካንሰር ከአባት ጅን ጋር የተያያዘ ነው
“ዘመቻውን በጀመርንበት ወቅት ከፍ ባለ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ክትባቱን አላገኙም ነበር። አሁን ትኩረታችን በ30 እና በ49 እድሜ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን መመርመር ነው” ይላሉ ዶክተር ኡዊንክዊነዲ።
አንጀሊን ሌሎች ስለበሽታው ያለቸውን ግንዛቤ ለማስፋትና ማግኘት የሚገባቸውን ህክምና እንዲወስዱ ለማበረታታት የራሷን የካንሰር ታሪክ በመንገር ጥረት እያደረገች ነው።
“የምችል ቢሆን ኖሮ፤ ሁሉንም አሰልፌ ምርመራ እንዲያደርጉ ሃኪም ጋር እወስዳቸው ነበር” ትላለች።