SourceURL:https://www.bbc.com/amharic/50673671 ከ20 ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? – BBC News አማ

ሃምሳ የሚሆኑ ከተለያዩ ከማኅበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡና በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ሚና ይኖራቸዋል የተባሉ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለ11 ቀን አብረው ውለው፣ 8 ቀን አብረው አድረው ስለኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ መክረዋል።
እነዚህ በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ቁልፍ ሚና አላቸው የተባሉ አካላት ምክክራቸውን ሲያደርጉ መገናኛ ብዙኀን እንዳይገኙ፣ ታዛቢ እንዳይኖር ተደርጎ አንደነበርም ሰምተናል።
50 የሚሆኑትን ተሳታፊዎች ለመምረጥም ስድስት ወር ፈጅቷል ያሉት አዘጋጆቹ፤ 150 ሰዎችን ማነጋገር አስፈልጎ እንደነበርም ጨምረው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እነዚህ የምክክሩ ተሳታፊዎች በመጨረሻም ኢትዮጵያ የዛሬ 20 ዓመት ሊገጥማት ይችላል ያሏቸውን አራት እጣ ፈንታዎች ማስቀመጣቸውንም ተነግሯል።
የተለዩት ዕጣ ፈንታዎች ምንድን ናቸው?
በዚህ ወርክሾፕ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ ምን ምን ዓይነት ዕጣ ፈንታዎች ይጠብቋታል የሚለው ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል ያሉት የወርክሾፑ አዘጋጆች ከሆኑት መካከል አንዱ አቶ ንጉሡ አክሊሉ ናቸው።
ዝም ብለን ብንቀጥል ምንድን ነው የምንሆነው? ዝም ብለን ጊዜ የሚያመጣውን ከምንጠብቅ እየገነባን ብንሄድ የት ጋ ልንደርስ እንችላለን? የሚለውን 50ዎቹ ተሳታፊዎች ከተነጋገሩ በኋላ አራት እጣ ፈንታዎችን ለይተው አውጥተዋል ይላሉ አቶ ንጉሡ።
ይህንን በሚያደርጉበት ወቅት ግን የወርክሾፑ አዘጋጆች ሀሳብም ሆነ አስተያየት አይሰጡም ያሉት ደግሞ አቶ ሞኔኑስ ሁንደራ ናቸው። አቶ ሞኔኑስ ከወርክሾፑ አዘጋጆች መካከል ሲሆኑ ውይይቱም ሆነ ሀሳቡ ከራሳቸው ከፖለቲከኞቹ የሚመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ጨምረውም የአዘጋጆቹ ድርሻ የነበረው የስብሰባውን ሪፖርት መጻፍ፣ ለሁሉም ተሳታፊዎች መላክና እነርሱ በሚሰጡት አስተያየት መሰረት የተስማሙበት እየቀጠለ እንዲሄድ ማድረግ እንደነበር ያብራራሉ።
ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ በመጪዎቹ 20 ዓመታት ይገጥማታል በማለት የለይዋቸውን ዕጣ ፈንታዎችና መጨረሻ የሚሉት ነጥብ ላይ ለመድረስ መንገዱ ምን ይመስላል? ስያሜዎቹ መዳረሻዎቹና እዚያ የሚያደርሱት መንገዶችን የቀየሱት እራሳቸው መሆናቸውን ከአዘጋጆቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ንጉሡ ጠቅሰዋል።
• “ኢህአዴግ ተዳክሟል ብላችሁ እንዳትሳሳቱ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ
ይህ ሁሉም የተስማሙበት ሰነድ ከ20 ጊዜ በላይ አስተያየት በመስጠት መመላለሳቸውን፣ በስህተት የገቡ እንዲወጡ፣ የተዘነጉ እንዲገቡ እየተደረገ የሁሉም ሀሳብ ተካትቶ የመጨረሻው ሰነድ መውጣቱ ይናገራሉ።
በዚህም የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን የዛሬ 20 ዓመት ሊገጥማት ይችላል ያሏቸውን እጣ ፈንታዎች በሰባራ ወንበር፣ በአጼ በጉልበቱ፣ በየፉክክር ቤትና በንጋት መስለው አቅርበዋል ያሉት ደግሞ አቶ ሞኔኑስ ሁንደራ ናቸው።
የእነዚህ የእጣ ፈንታዎቹ ስያሜዎችን ሲያብረራሩም፤ ሰባራ ወንበር ተብሎ የተሰየመው ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለች የዛሬ 20 ዓመት የመንግሥት ሥልጣን ቢኖርም ሀገርን ወደ ሚፈልገው ጎዳና ለመምራት አስቸጋሪ ይሆናል በሚል መሆኑን ያስረዳሉ።
የፖለቲካ ኃይሎች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሀገርን ወደ ቀና ጎዳና መምራት የሚያስችል ፍላጎት ቢኖራቸውም አቅም ግን አይኖራቸውም ሲሉ ይተነብያሉ።
በዚህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማህበራዊና ደህንነት ሁሉ ይሽመደመዳል ሲሉ ይገልጻሉ።
አቶ ሞኔኑስ በመቀጠል፣ ‘አጼ በጉልበቱ’ ተብሎ የተሰየመውን እጣ ፈንታ ሲያብራሩ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት እየታየ እንዳለው ዜጎች የተለያየ ጥያቄ እያነሱ ነው ብለዋል።
መንግሥት እነዚህን ጥያቄዎች ለመፍታት የሚሠጠው ምላሽ ወሳኝ ነው በማለትም፤ አሁን ያለው ስጋት ጥያቄዎቹ እየበዙ ሲሄዱ መንግሥት ጥያቄዎቹን ለማፈን ጠመንጃ ቢጠቀም፣ ቢያስር ወደ የኃይል አገዛዝ የማምራት ዕጣ ፈንታ ይኖራል ሲሉ ማስቀመጣቸውን ያብራራል።
‘የፉክክር ቤት’ በሚል በተቀመጠው እጣ ፈንታ ሊከሰት የሚችለው ይላሉ አቶ ሞኔኑስ፤ ብሔር ብሔረሰቦች ከአጼ በጉልበቱ አገዛዝ ለመውጣት የሚያደርጉት እና መብታቸውን ለማስከበር በሚወስዱት ርምጃ ነው ይላሉ።

ብሔር ብሔረሰቦች በየግል የራሳቸውን አገር ለመመስረት ይንቀሳቀሳሉ። አገራዊ አስተሳሰብ እየቀረ ሁሉም በየብሔሩ እያሰበ የሚሄድበት ሁኔታ፤ በዚህም አተካሮና ፉክክር ውስጥ ተገብቶ የጋራ አገር ይረሳል፤ አገርም ወደ መፍረስ ትሄዳለች በማለት ማስቀመጣቸውን ያብራራል።
በመጨረሻ የተቀመጠው ዕጣ ፈንታ ‘ንጋት’ የሚል ሲሆን አሁን አገር ያለችበትን ሁኔታ ተሳታፊዎቹ በጨለማ መስለውታል ብለዋል። በዚህ ወቅት እስር፣ ግድያ፣ መከፋፈል፣ እርስ በርስ መጠራጠር እና ሌሎች ስጋቶች ተጋርጠው ይታያሉ ሲሉ የተቀመጠውን እጣ ፈንታ ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ እነዚህ ጥያቄዎች በሂደት እየተመለሱ መተማመን እየተፈጠረ መነጋገር ከተቻለ ፌደራሊዝምና እርሱን የሚያጠናክሩ ተቋማት እየዳበሩ ጨለማው ተገፍፎ ብርሃን ይወጣላታል ሲሉ ማስቀመጣቸውን ይናገራሉ።
ከእነዚህ ከአራት እጣ ፈንታዎች መካከል ሦስቱን ተሳታፊዎቹ እንደማይፈልጓቸው ማስቀመጣቸውን የሚናገሩት አቶ ንጉሡ፤ ‘ንጋት’ ግን ሁሉንም የሚያስማማ ነው በማለት በንጋት ውስጥ ሊያይዋት የሚፈልጓትን ኢትዮጵያ ለመስራት እና ለቀጣይ ትውልድ ለማውረስ እንደሚሰሩ በመግለጽ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸውን ገልጸዋል።
• “ኢህአዴግ ነፃ ገበያም፣ ነፃ ፖለቲካም አላካሄደም” ፀደቀ ይሁኔ (ኢንጂነር )
‘ንጋት’ የተሰኘው እጣ ፈንታ እንዲሁ በቀላሉ ማግኘት እንደማይቻል በመግለጽ መነጋገር፣ መደማመጥ ብሔራዊ መግባባት እንደሚያስፈልገው አቶ ንጉሡ ያስረዳሉ።
የትብብር መንፈስ መፍጠር፣ እየሰጡ መቀበልና ማመቻመች ስለሚያስፈልግ በቀጣይ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚኖሩ ድርድርና እርቆች እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የፓርቲ አመራሮች እዚህ የወሰኑትን የ’ንጋት’ እጣ ፈንታ ለአባላቶቻቸው በመንገር የማስረጽ ሥራ እንደሚሰሩ ይናገራሉ።
‘ንጋት’ን ወደ ሕዝቡ ለማስረጽ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሰሩ የሚናገሩት አቶ ንጉሡ፤ የስብሰባው 50 ተሳታፊዎችም ይህንኑ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን ይናገራሉ።

አዘጋጆቹ እነማን ናቸው?
ዘጠኝ ጓደኛሞች ናቸው። በተለያየ የህይወት አውድ ውስጥ የሚውሉ ቢሆንም ሲገናኙ ግን ስለ አገራቸው ዘወትር ያወራሉ። እነርሱም ሆኑ ሌሎች ስለኢትዮጵያ በሚያወሩት ጉዳይ ግን ደስተኞች አልሆኑም።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞና በነበረው ብሔር ተኮር ግጭት ምክንያት ብዙዎች የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ ከሊቢያና ከሶሪያ ጋር እያዛመዱ የሚያወሩ በረከቱ።
እነርሱ ግን የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ ከሶሪያና ከሊቢያ ከማመሳከር ይልቅ እንዲህ ዓይነት ሕዝባዊ ተቃውሞና ግጭት ገጥሟቸው በድል የተሻገሩ አገራትን ማሰስ ጀመሩ።
የገጠማቸውን ችግር አልፈው ወደ ተሻለ ጎዳና የሄዱ አገራት ያደረጓቸውን ነገሮች ሲመረምሩም አንድ ቁልፍ ነገር ማግኘታቸውን አቶ ንጉሡ ይናገራል።
• “ኢትዮጵያ የኢህአዴግ አባት እንጂ፤ ኢህአዴግ የኢትዮጵያ አባት አይደለም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ
አቶ ንጉሱ ራሳቸውን ከገጠማቸው ችግር ውስጥ ያወጡና ሕዝባቸውን ወደ ዲሞክራሲ ያሻገሩ አገራት ያደረጉ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሪዎች እንዲሁም የተወሰኑ የቁልፍ ተዋንያን የሚያደርጉት ዝግ ውይይትና ንግግር እንደሆነ ከንባባቸውና ከአሰሳቸው ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
እነዚህ ዝግ ውይይቶች ለመገናኛ ብዙኀንም ሆነ ለታዛቢዎች ዝግ እንደሚሆኑም ማስተዋላቸውን ይጠቅሳሉ።
እንዲህ አይነት ንግግሮች እርስ በእርስ መቀራረብ፣ መግባባትና መተማመንን እንደሚፈጥሩ መረዳታቸውን እንዲሁም በጋራ መነጋገር ከጀመሩ በኋላ አንድ የጋራ ሰነድ ይዘው ሊወጡ እንደሚችሉ ተረድተዋል።
እንዲህ አይነት ልምድ በደቡብ አፍሪካ፣ በኮሎምቢያ፣ በሜክሲኮ፣ በአየርላንድና በካናዳ ተሞክሮ ሸጋ ውጤት ማሳየቱንም ይገልጻሉ።
ድርድርም እርቅም ያልሆነ መርሃ ግብር
እነዚህ በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዋነኛ የፖለቲካ ተዋናዮችን አቀራርቦ ሀሳባቸውን እውን ለማድረግ ይበጃል ያሉትን ያወጡ ያወርዱ ጀመር።
በቅድሚያ ለዚህ ጥረታቸው “ዴስቲኒ ኢትዮጵያ 2040” የሚል ስያሜ ሰጥተዋል።
ሀሳባቸውን ይዘው በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጉምቱ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ደጃፍን ማንኳኳት ጀመሩ።
በመጀመሪያ እናንተ ማናችሁ የሚል ጥያቄ ከተሳታፊዎቹ መቅረቡን ያስታውሳሉ። ዘጠኙ ጓደኛሞች በተለያየ የሙያ መስክ የተሳካላቸው ቢሆኑም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን ስማቸው ተነስቶ ዳናቸው ተገኝቶም አያውቅም።
• ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ሊወያዩ ነው
ይህ እንደ ድክመት ቢነቀስባቸውም ነገር ግን ገለልተኛ ለመሆናቸው እንደ አስረጅ ሊቀርብ የሚችል መሆኑን አቶ ንጉሡ በኩራት ያስረዳሉ።
የወርክሾፑ ተሳታፊዎችን ለመመልመል በዙሪያቸው የሚገኙ በርካታ ሰዎችን ማነጋገር፣ ዓላማውን ማስረዳት እንደነበረባቸው ይናገራሉ።
በመጨረሻም ከተሳታፊው ጋር በቀጥታ ከመገናኘታቸው በፊት የተሳታፊው የቅርብ ወዳጆች ስለዚህ ወርክሾፕ አስቀድመው ነግረውት ስለሚጠብቃቸው እምነት ለማግኘት እንዳልከበዳቸው ያብራራሉ።
50 ሰው ለመመልመል ከ150 በላይ ሰዎችን ማነጋገር አስፈልጓቸው እንደነበር የሚገልጸው ንጉሡ፣ እነዚህ 150 ሰዎች ወደ ቁልፍ የፖለቲካ ሰዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አድራሽ እንጂ በራሳቸው መዳረሻ አልነበሩም ይላል።
እነዚህን ሰዎች ማነጋገር በራሱ ስድስት ወር መፍጀቱን በማስታወስም ወርክሾፑ መካሄድ ከመጀመሩና ደጋፊ አካላትን ገንዘብ ልገሳ ከመጠየቃቸው በፊት የተሳታፊዎቹን ይሁንታ ማግኘትን ማስቀደማቸውን ያስረዳሉ።
አንዳንድ ተሳታፊዎች በመካከል የሚወጡ፣ የሚጠራጠሩና እንዲህ ዓይነት ውይይት የተለመደ ነው በማለት ማጣጣል እንደነበር ያስታውሳሉ።
ተስፋ ባለመቁረጥ ይሁንታቸውን ከሰጡ በኋላ በሚወጡ ሰዎች ምትክ እየተኩ፣ ካልሆነ እንዲተኩ በማድረግ ወርክሾፑን ማስጀመራቸውን ይናገራሉ።
ወርክሾፑን መሳተፍ ከጀመሩ መውጣት አይታሰብም የሚሉት አቶ ንጉሡ፣ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ጉዳይ መሳተፋቸውን ይጠቅሳሉ።

“ይህ ፕሮግራም ድርድር አይደለም፤ እርቅ አይደለም። ይህንን በወርክሾፑ ላይ የተሳተፉ አካላትም ቀድመው እንዲያውቁ ተደርጓል” በማለትም ከተለያየ የፖለቲካ አመለካከት እና አስተሳሰብ የሚመጡ ፖለቲከኞች በታሪክ የማይግባቡባቸው ነጥቦች መኖራቸውን ያነሳሉ።
እነዚህ አለመግባባቶችና ልዩነቶች እየሰፉ ሄደው ስለዛሬና ስለነገ እንኳ እንዳናስብ እያደረጉን ነው በማለት፤ የዚህ ወርክሾፕ ዋነኛው ዓላማ ሰዎችን ከትናንትናና ከዛሬ አውጥቶ፣ በትናንትና በዛሬ ላይ በመመስረት ነገን እንዲያዩት ማድረግ መሆኑን ይገልጻሉ።
“ነገን አብረው እንዲገነቡት በነገይቱ ኢትዮጵያ ላይ እየተወያዩ የምንፈልጋት ኢትዮጵያ እንደዚች ዓይነት መሆን አለባት ብለው፤ የሚፈልጓትን ኢትዮጵያ በሀሳብ መገንባት ቢችሉ ከዚያ በኋላ በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እየተነጋገሩ መግባባት ይችላሉ” ይላሉ አቶ ንጉሡ።
የጉባዔው ተሳታፊዎች እነማን ናቸው?
እነዚህ ዘጠኝ ጓደኛሞች ይህንን ወርክሾፕ ለማካሄድ አንድ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰራ ድርጅት አግኝተው በማናገር ምክር ጠይቀዋል። ከድርጅቱ ጋር የኢትዮጵያን ተጨባች ሁኔታ ካወሩ በኋላ መልካም ምክር ማግኘታቸውን አቶ ንጉሡ ያስታውሳሉ።
ይህንን ዘዴ ከኢትዮጵያ ተጨባች ሁኔታ ጋር አንዴት እናላምደዋለን በሚል መወያየታቸውን አንስተው፤ በመቀጠል የወሰዱት እርምጃ የኢህአዴግ አራት አባል ድርጅቶችን፣ ዋና ዋና የፖቲካ አስተሳሰብን ይወክላሉ ያሏቸውን የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮችን፣ ክልሎችን፣ አክቲቪስቶችንና፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦችን፣ ነጋዴዎችን፣ ሲቪል ማህበረሰቡ ተወካዮችን፣ ጋዜጠኞችንና ምሁራንን በማሰባሰብ መስራት መጀመር መሆኑን ይናገራሉ።
ይህንን ሀሳብ ወደፊት ሊያራምድ የሚችል ተቋም እንደሚያስፈልግም ከተነጋገሩ በኋላ፤ ተቋም በገዢው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎች ሙሉ እምነት የሚጣልበት እንዲሆን በማለትም የካናዳውን “ፎረምስ ኦፍ ፌዴሬሽንስ” በመምረጥ ከስምምነት ላይ ደረሱ።
• “ለስልጣን ተብሎ የሚፈጠር ውህደትን ህወሓት ፈጽሞ አይቀበለውም” አቶ ጌታቸው ረዳ
በአጠቃላይ ሂደቱ ሦስት ወርክሾፖች ይካሄዱበታል የሚሉት አቶ ንጉሡ፤ እነዚህ ወርክሾፖች የመገናኛ ብዙኀን የማይገኙባቸው፣ ሶሻል ሚዲያ ላይ የማይጻፍበትና ታዛቢ የሌለባቸው መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ይህንን ደግሞ ተሳታፊዎችም ያከብራሉ በማለት፤ በዚሁ መሰረት በአርባምንጭና በቢሾፍቱ ወርክሾፖቹን ማካሄዳቸውን ያስረዳሉ።
እነዚህ ወርክሾፖች በአይነታቸው ለየት ይላሉ የሚሉት አቶ ንጉሡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወርክሾፖች፤ ወርክሾፖቹ አራት አራት ቀን ብቻ የሚካሄዱ ሲሆን ለሦስት ቀናት ተሳታፊዎች አብረው ያድራሉ ሲሉ ያስረዳሉ።
በሦስተኛው ወርክሾፕ ደግሞ ሁለት ቀን አብረው ያድራሉ ሦስት ቀን አብረው ይቆያሉ ይላሉ።
ፖለቲከኞች ከጉባኤው በኋላ
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ረዥም ዓመት እንደቆዩ የተናገሩት አቶ ፀጋዬ ማሞ አንዳንዶቻችን ከሌላው የበለጠ ስለኢትዮጵያ የሚያገባን የሚመስለን አለን በማለት በዚህ ሂደት በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ 50ዎቹ ተሳታፊዎችም እኩል ስለኢትዮጵያ እንደሚያገባቸው መማራቸውን ተናግረዋል።
አክለውም አንዳንዶቻችን አውሬ አድርገን ከሳልናቸው አካላት ጋር ቁጭ ብለን ስንወያይ በትክክልም ሰው መሆናቸውን ተረድተናል ብለዋል።
ከእኛ በላይ የተጣላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የለም በማለትም በመነጋገርም ሁሉንም ችግር መፍታት እንደሚቻል መማራቸውን መስክተዋል።
ዶ/ር በድሉ ዋቅጂራ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ችግር በጠመንጃ ሳይሆን በመነጋገር፣ በይቅርታና በፍቅር ብቻ የሚፈታ መሆኑን መረዳታቸውን ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ፖለቲካ ውስጥ ሁሌም ችግሩ ምክንያታዊነት መጥፋቱ ነው፤ በማለት በተካሄዱት የተለያዩ ወርክሾፕ የተረዱት ሰዎች በምክንያታዊነት ቁጭ ብለው ከተወያዩ መፍታት የማይችሉት ነገር እንደሌለ መረዳታቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ 50 የወርክሾፑ ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ እየተገናኙ ኢ መደበኛ የሆኑ ውይይት ለማድረግ መስማማታቸውንም ተገልጿል።
የአብን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ደግሞ በበኩላቸው የምንወዳት አገራችን ንጋት እንዲነጋላቸት የምችለውን አደርጋለሁ ብለዋል።