ሁሌ እናስታውሳቸው
ተቀብሮ እንዳይቀር
አኩሪ ታሪካቸው!!!!!!!
መኮንን ሐጎስ ማን ነው ??

በሠሎሞን ታምሩ ዓየለ እንደተናገረው………
“ይህንን የትውስታ ጽሑፍ እንድጽፍ አንዳች ነገር ሁልጊዜ ከውስጤ ይገፋፋኝ ነበር።……..
ይኸውም ስለ ቀድሞው የቀኃሥ ዪኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ መሪዎች ስለነ ጥላሁን ግዛው፧ ዋለልኝ መኮንን፤ ማርታ መብራህቱና ሌሎችም ውድና ክብሩን ሕይወታቸውን ለሕዝብ እኩልነትና ለዴሞክራሲያዊ መብት፤ ለፍትህና ርትዕ፤ ለነጻነት ሰጥተው ስላለፉት ታጋዮች ሲወሳ ከእነርሱ እኩል ተርታ ስሙ ሊነሳና መስዋእትነቱ በታሪክ ብዕር ተጽፎለትና ገኖ እንዲወጣ ብዙ ስላልተነገረለት የነጻነት አርበኛና የህዝብ ልጅ መኮንን ሐጎስን ለማስታወስ ነው።
እነሆ ! መኮንን ለነጻነት የሚከፈለውን ትልቁን ዋጋ መስዋእትነት ከፍሎ ከሚወደው ቤተሰቡና ዘመደ አዝማድ፤ አገሩና ለመብቱ የታገለለትን ሕዝብ ጥሎ በግፈኞችና በነፍሰ ገዳዮች ይህቺን ምድር ጥሎ ከሂደ ግማሽ ምእተ አመት ሊሞላ ትንሽ ቀርቶታል።”
ስለ መኮንን በጥልቀት የሚያውቁና ከጎኑ የነበሩ ግን በብዕራቸው ዛሬም ቢገልጹት ጊዜው አልረፈደም በማለት እያሳሰብኩኝ ፣ ካደረጉት ከወዲሁ ላቅ ያለ ምስገናዬን እገልጻለሁኝ።”
መኮንን ሐጎስ ገብሬ ከአባቱ መጋቢ ሃምሳ አለቃ ሐጎስ ገብሬና ከእናቱ ከወይዘሮ ጥሩነሽ እንደልቡ እአአ በየካቲት 29 1947 በቀድሞው የሐረር መምህራን ማሰልጠኛ ሰፊ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኘው የሰራዊቱ ክፍል መኖሪያ እንደተወለደና ዕድገቱ ግን ለሐረር ከተማ በቅርብ ዕርቀት በምተገኘው ሐማሬሣ በ፪ተኛው ጦር ሜዳ መድፈኛ ሻለቃ ቅጥር ግቢ ውስጥ በነበረው የሰራዊቱ መኖሪያ ሰፈር ነው።
የመጀመሪ ደረጃ ትምህርቱን በቀላድ አምባ በሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ት/ቤት የሁለተኛ ደረጃ ት/ቱን ደግሞ ሽንኮር በሚገኘው የመድሃኒዓለም መርሃ ሙያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ ቤትና በቀድሞው በዕደ ማሪያም እንደተማረና ከዚያም የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሶሺያል ሳይንስ ኮሌጅ ትምህርቱን በጂኦግራፊ ዴፓርትመንት እስከ ሦስተኛ ዓመት ድረስ ካጠናቀቀ በኋላ ከምረቃ ዓመት አስቀድሞ በጊዜው ለአንድ ዓመት ያህል በተለያዩ የመንግስት ተቋማት “ ሰርቪስ” በመባል በሚታወቀው መርሃ ግብር መሰረት እንደ ዕድል ሆኖ ቀድሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተከታተለበት ሐረር መድሃኔዓለም መርሃ ሙያ ሁለተኛ ደረጃ በአስተማሪነት አስከ እለተ ሞቱ ድረስ አገልግሏል።
ይህ ድንቅና ባለ ብሩህ አእምሮና ምጡቅ ወጣት ምንአልባትም ከዚያች ትንሽዬ የሰራዊት መንደር የዩኒቨርሲቲን በር ከረገጡት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘና ለሌሎችም የሰራዊቱ ልጆች ዓርዓያ በመሆን በሩን የከፈተ ተራማጅ ወጣት ነበረ።
ጊዜው የየካቲት ወር ( 21 ወይም 22 ) 1962 ዓም መገባደጃ የመጨረሻው ሳምንት ይመስለኛል። በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች የሁዳዴ ጾም መግቢያ ወይም መያዣ ዝግጅት በዕለተ ቅዳሜ ወላጆቹን ሊጎበኝና መልካም የጾም ወቅት እንዲሆን ለመመኘት ሐማሬሳ ብቅ ያለው መኮንን ወላጆቹን ጎብኝቶ ሲመለስ ፣ ዛሬ በህይወት የሌለችውን እናቴን ወ/ ሮ ደብሪቱ ጎንጥን ሰላምታ ለመስጠት እንዲሁ በቁሙ በራፋችንን የረገጠውን መኮንን በደንብ አድርጌ ተመለከትኩትና አስተዋልኩት ።
ይቺ ቀን ነች መኮንንን ደህና አድርጋ የዘገበችው አእምሮዬ ዛሬ በትንሹ ያንን ወጣት እንድመለከተውና እንዳስታውሰው ያደረገኝ። መኮንን የልጅነት ሰላምታውን ለእናቴ ከሰጠ በኋላ እንደሚቸኩል ገልፆ ወደ ቤታችንም ጎራ ሳይል በዚያ ቁመቱ እየተንደረደረ ግቢውን ለቆ ወጣ። መኮንን ሐጎስ ቁመታምና ለግላጋ መልካ መልካም ወጣት ፤ አለባበሱም ቄንጠኛ ስለነበር፤ በተለይ ሙሉ ልብስ ከቁመቱ ጋር ሰለሚሄድ ያምርበታል። መኮንንን ከዚያ በፊት ግን በአካል ለመግለፅ በሚያስችል መልኩ ስለማወቄ ምንም ማረጋገጫ የለኝም ።
በትምህርቱ በጣም ጎበዝ ፤ በአስተማሪነት ግልጋሎት ሲሰጥ በተማሪዎች በጣም ተወዳጅ የነበረው መኮንን ሐጎስ፤ ቀደም ሲልም ከተማሪነቱ ጀምሮ፤ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ውስጥ ንቁና የጎላ ሚና ስለነበረው የመንግስትን ኢፍትሃዊ አስተዳደር በሰላ አእምሮው ሲነቅፍና ሲተች ሲቀሰቅሳና ሲያቀጣጥል፤ ሲያደራጅና ሲመራ፤ ሲታገልና ሲያታግል የነበረ መሆኑ ይታወቃል።
የ ሃያ ሶስቱ አመት ወጣት አስተማሪ፤ በተማሪች የነበረው መወደድ፤ በትግሉ ላይ ያሳደረው ተፅእኖ፤ የመሪነት ችሎታውንና አቅሙን ለማሳየት በመቻሉና ይህም ተግባሩ በፖሊስና በደህንነት ሰዎች ያልተወደደለትና ያልተጨበጨበለት መኮንን እንደ ትግል ጓዶቹ ሁሉ ሞት ዕጣ ፈንታው እንዲሆን ተበየነበት። ዒላማቸው እስኪገባላቸው ድረስ ሲከታተሉት ከረሙና አመች ጊዜ ጠብቀው መኮንንን በ ሐረር ከተማ በወቅቱ ሕብረት ሆቴል ተብሎ በሚጠራው ስፍራ እራቱን ተመግቦ ከወጣ በኋላ በአልሞ ተኴሾች በተተኮሰበት ጥይት ጭንቅላቱን ከተመታ በኋላ፤ ተፈላጊው ህክምናም ተደርጎለት ህይወትም እንዳይዘራ ሰለተፈለገ ብቻ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታም እንዳያገኝም በከተማዋ በሚገኙ ሆስፒታሎች ደጃፍ እንደተንከራተተም ይነገራል። በዚህ በወጣትነት ዕድሜው ትልቅ ራዕይና ሩቅ ለመጓዝ ሃላፊነት የሰነቀው ወጣቱ ፖለቲከኛና የነጻነት ዐርበኛ ተገደለ። የእስትንፋሱም የህይወቱም ፍጻሜ ሆነ።
ያ ወጣቱ ታጋይ መኮንን ሐጎስ የህዝብ ልጅ ነውና መላው ቤተሰቡና በከተማው ዝናውንና ገናናነቱን አይፈሬነቱን ያውቁ የነበሩትና ሁኔታውን በስጋትና ለእርሱ ሲሉ ይፈሩለትና ይሳሱለትና ይከታተሉት የነበሩ ሁሉ የልቅሶውን ሥርዓትም በእጅጉ በቁጭትና በሚያሳዝን መልኩ ነበር ያጠናቀቀው። ወላጅ፤ ዘመድ አዝማድ፤ ጎረቤት፤ ልጄ፤ ወንድምዬ ፤ መኮንኔ ያላለ የለም። ተማሪም መምህሬ በማለት ለቅሶውንና ሃዘኑን ገለጸ።
የቀብር ሥርዓቱም በሐረር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እጅግ ቁጥሩ በበዛና በከተማዋ ከዚያም በፊት ሆነ ዛሬም ታይቶ በማይታወቅ ወደር በሌለው መልኩ የህዝብ ብዛት ታጅቦ ተፈጽሟል። ለመጥቀስም ያህል፦ መላው የሐማሬሳ ነዋሪና የሠራዊቱ አባላት፤ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች፤ የመድሃኔዓለምና የሐረር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፤ የሐረር ዕጩ መምህራን ተቋም ሠልጣኞችና መምህሮች፤ የሐረርጌ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ሰራተኞች፤ ከፍተኛ የፖሊስና የጦርሠራዊት መኮንኖችና የበታች ባለማዕረጎችና አባላቶች፤ በቅርብ እርቀት በዓለማያ እርሻ ኮሌጅ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎችና መምህራንና ሌሎች በጥቂቱ ናቸው።
በወጣቱ መኮንን ሐጎስ ድንገተኛ ግድያና ሞትም ያልተዋጠለት ነዋሪ ህዝብ የመንግሥት እጅ አለበት ብሎ ሰለ ጠረጠረ የቀብር ሥርዓቱም ላይ ዐመጽ እንዳይነሳ እጅግ ተፈርቶ ስለ ነበር በጸጥታ ኃይሎችና በነጭ ለባሾች ተወሮም እንደነበር ይወሳል።
ከቀብር ሥርዓትም በኋላም ቢሆን ውስጥ ውስጡን ነዋሪው ህዝብ ማጉረምረምና የዚያኑ ጊዜ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን ሰዎች መውቀስና መጥላት ጀመረ። በተለይም የሠራዊቱ ክፍል የበታች ሹማምንቶችና ውስጥ አዋቂዎች የተፈጸመውን ግድያ አወገዙት።
ግድያውም የተፈጸመው በሠራዊቱ አባል ልጅ ላይ በመሆኑና አባቱ የአገር ድንበር አጥር ሆኖ ወራሪዎችን የመለሰና የሰላም በር ዘብ ሆኖ ያሳደገውና የልጁንዓለም ለማየት በተስፋ ይጠብቀው የነበረ በመሆኑ ሰራዊቱ በድርጊቱ መከፋቱንና መቆጨቱን የተረዱት ነፍሰ ገዳዮች ሁኔታውን ለማለዘብ አዲስ ትርኢት ጀመሩ። ጥቂት ቆየት ብሎም የመኮንን ገዳይ በመባል፤ በወሬ ደረጃ ከመኮንን ጋር የግል ግጭት አለው ተብሎ የሚወሳ፤ ዘሪሁን ጆቴ የተባለ አንድ ሚስኪን መምህር ወጥመድ ውስጥ ገባና ተያዘ።
ብዙ እንግልትና ድብደባ እንደተፈጸመበት የሚገልጸው መምህር የደረሰበትን ሰቆቃ በዚያኑ ጊዜ “ፖሊስና እርምጃው” ጋዜጣ ላይ “ሳልገድል ገድለሃል ተብዬ የደረሰብኝ ስቃይ” በሚል የ1966 ዓም የየካቲት አብዮቱ የፈነዳ ሰሞን አስነብቦናል።
ክብር የህዝብን ጥያቄ አንግቦ ግንባሩን ለጥይት ለሰጠ ጀግና ትውልድ!!
ለህግ የበላይነት፤ ለሰላም ለዴሞክራሲና ለ እኩልነት..
ሁሉንም ያካተተ የሽግግር መንግስት!!!
የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!!