
- ለማሳየት የወጠኑ 50 ኢትዮጵያውያንና ግኝቶቻቸው

ኢትዮጵያን ከ20 ዓመታት በኋላ አጉልተው ለማሳየት የወጠኑ 50 ኢትዮጵያውያንና ግኝቶቻቸው
8 December 2019 ብሩክ አብዱ
ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንደምትገኝ በርካቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ ወጣም ወረደም አሁን ያለው ሁኔታ እንደ ተሰባሪ ብርጭቆ በጥንቃቄ ተይዞ ወደ ዴሞክራሲ መሸጋገር ካልተቻለ ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እንደ ሕዝብ ለመቀጠል አዳጋች እንደሚሆንባቸው ተንታኞችና ሐሳብ አመንጪዎች ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ጥሪዎች በቡድንም በተናጠልም ሲደረጉ ነበር፡፡ የተለያዩ ምልከታዎች፣ ፖለቲካዊና ሌላ ዓይነት ፍላጎቶችን ያዘሉ እንደሆኑም ትችቶች ይቀርቡባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ሙያዊና ሳይንሳዊ የሆኑ ትንታኔዎች፣ የአካታችነትና የግኝቶች ተግባራዊነት ላይ ጥያቄዎች ይነሱባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታዎችና የተሻለ አቅጣጫን ያሳያል በሚል ተስፋ ‹‹እውነታዎችን እንድንጋፈጥ፣ እንድንነጋገርና የጉዞ አቅጣጫዎቻችንን እንድንመርጥ አጋጣሚዎችን ይፈጥሩልናል›› የተባሉ መፍትሔዎችን ለመተለም የትራንስፎርማቲቭ ሴናሪዮ ትንተና (Transformative Scenario Planning) በተግባር ላይ በማዋል፣ ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በኋላ ምን ልትመስል እንደምትችል ያመለከቱ ቢሆኖች (ሴናሪዮዎች) ተለይተው፣ ማክሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስካይ ላይት ሆቴል ይፋ ተደርገዋል፡፡
በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ለጦርነት ዕቅድ ማውጫነት ጥቅም ላይ ውሎ እንደነበር በመጠቆም፣ እ.ኤ.አ. ከ1939 እስከ 1945 ባሉት ጊዜያት እንደተፈጠረ የሚነገርለት የቢሆኖች ዕቅድ በተለይ የአሜሪካ አየር ኃይል ጠላቶች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል ትንታኔ ዝግጅቶችን ለማድረግ የሚያስችሉ መላ ምቶችን በማስቀመጥ፣ በሰፊው እንደተጠቀመው የተለያዩ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡
ይኼ የዕቅድ አሠራር ከአየር ኃይሉ በወጡ ግለሰቦች ወደ ቢዝነስና ፖለቲካው መግባት የጀመረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1970 በለንደን ሮያል ደረጃ (ሼል) የዕቅድ ሠራተኛ በነበሩት ፒየር ዋክ አማካይነት ‹‹የቡድን ዕቅድ›› የሥራ ክፍል ምክንያትነት ከከፍታ መድረሱም በጥናቶች ይጠቀሳል፡፡ የፒየር ዋክ ቡድን ይኼንን ዘዴ ሲጠቀምበት የነበረውም፣ የነዳጅ ገበያን ምን ሊጎዳው እንደሚችል በመለየት መፍትሔ ለማግኘት በማሰብ ነበር፡፡
ሴናሪዮ (ቢሆን) በቅጡ ከመረዳት ያልተደረሰበት፣ እንዲሁም በርካታ ጊዜ ያላግባብ ጥቅም ላይ የሚውል ቃል መሆኑን እ.ኤ.አ. በ2000 የተጻፈውን የሩቤክለት መጽሐፍ በመጥቀስ የሚያብራሩት ‹‹የቢሆኖች ትንታኔ ስትራቴጂካዊ ለሆኑ ትንበያዎች ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች›› በሚል ርዕስ ጥናት የሠሩት ዳና ሜትዝነርና ጉዊዶ ሬጀር፣ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ቢሆኖች ወደ አንድ የወደፊት መድረክ የሚመሩ የተለያዩ ቅያሶች ቅንብር ናቸው በማለት፣ በተግባር ግን ሁነቶችን አልያም ተለዋዋጭ ክስተቶችን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላሉ ይላሉ፡፡
የተለያየ አረዳድና አካሄድ ቢኖርም ቅሉ፣ የቢሆኖች ትንታኔ መዳረሻው በውስጣቸው ወጥ ፍሰት ባላቸው ምሥሎች የወደፊትን አጉልቶ ማየት እንደሆነ ጸሐፊዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህም የአሁን ሒደቶችን ከማቀጣጠል ይልቅ አማራጭ ምሥሎችን የሚያቀርቡ፣ የዓይነታዊና ቁጥራዊ መረጃን ያጠናቀሩ፣ ፍፁማዊ የሆኑና ከአሁኑ ሒደት የማይቀጥሉ ጉዳዮች እንዲፈተሹ የሚፈቅዱ፣ ውሳኔ ሰጪዎችን መሠረታዊ ግጭቶችን እንዲቀይሩ የሚያደርጉ፣ ብሎም መሣሪያ የሆኑ ተቋማዊ ሒደቶችን የጋራ ቋንቋ በመፍጠር ውስብስብ ጉዳዮችን ለመነጋገር የሚያስችሉ ባህርያት ያሏቸው እንደሆኑም ያክላሉ፡፡
ስለዚህም ቢሆኖች የወደፊት ሥጋቶችንና ዕድሎችን ለመለየት፣ ያለፉ ሁነቶችን በመለጠጥ አዎንታዊና አሉታዊ የሆኑ የወደፊት የተለያዩ መልኮችን ምሥል መከሰት፣ ስትራቴጂካዊ አስተሳሰብና የመማር ሒደቶችን ማጎልበት፣ የስትራቴጂካዊ ተዋጽኦ ጥበብን ማቀላጠፍ፣ የወደፊቱን ሁኔታ ማለም፣ የተለመዱ የወደፊት መላምቶችን መገዳደርና ማስቀረት፣ እንዲሁም ለአዳዲስ አቅጣጫዎችና አስተሳሰቦች መመርያ መስጠት የሚሉት የቢሆኖች ትንተና ዓላማዎች እንደሆኑም ኔልሰንና ዋግነር የተባሉ ጸሐፍትን ጠቅሰው ሁለቱ አጥኚዎች ያብራራሉ፡፡
ይኼንን የትንታኔ መንገድ ተጠቅመው ዴስቲኒ ኢትዮጵያ በተሰኘ ተቋም አስተባባሪነት የተሰበሰቡ 50 ‹‹ተፅዕኖ ፈጣሪ›› ኢትዮጵያውያን ሦስት የምክክር መድረኮችን በአርባ ምንጭና በቢሾፍቱ ከተሞች ከሰኔ 2011 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2012 ዓ.ም. አካሂደዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን አሁን ከምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ለሚገጥሙን ተግዳሮቶች እንደምንሰጣቸው ምላሽ የተለያዩ አራት መዳረሻዎችን ያመላክቱናል፤›› ሲሉ አራት ቢሆኖች ኢትዮጵያን በ2020 ይጠብቋታል በማለት ለይተዋል፡፡ እነዚህም ቢሆኖች አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታና ይኼንን መነሻ በማድረግ ሊከሰቱ የሚችሉ ነገር ግን አይገመቴ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ የተተነተኑ፣ በቀጣይ ዓመታት ምን ሊከሰቱ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ታሪኮች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ሆኖም ወደፊት ምን እንደሚሆን የተነገሩ ትንቢቶችና ምን መከሰት እንዳለበት የሚደነግጉ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች አይደሉም ይላል፣ ከዚህ ሥራ የተገኘው የሪፖርት ሰነድ፡፡
በእነዚህ አጥኚዎች የተለዩት ቢሆኖች ንጋት፣ የፉክክር ቤት፣ አፄ በጉልበቱና ሰባራ ወንበር የሚሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ወደፊት ከዴሞክራሲ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከፀጥታና ሰላም፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከምግብ ዋስትና፣ ከዓለም አቀፍ ክስተቶች፣ እንዲሁም እንደ አገር የመቀጠል ጥያቄ አንስተው ይተነትናሉ፡፡
ንጋትን የኢትዮጵያ ዕድገት ደረጃ በደረጃ ዕውን የሚሆንበትን ተስፋ ያዘለ ነው በማለት የሙሉ ቀን ብርሃን አልሆነም፣ ነገር ግን የአዲሱ ቀን ወገግታ ጀምሯል ሲል ያስተዋውቃል፡፡
‹‹በቅርቡ የተካሄዱ ማሻሻያዎች በኢትዮጵያ ላይ የተስፋ ስማት ጭረዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማብቃት ተከትሎ የነፃነት መንፈስ ታይቷል፡፡ የኢንተርኔት ሳንሱር ቆሟል፡፡ ጨቋኝ ሕጎች ተሻሽለዋል፡፡ የፖለቲካ አመራሮች ከእስር ተፈትተው በምርጫ ላይ የመሳተፍ ነፃነት አግኝተዋል፡፡ ከአጎራባች አገሮች ጋር ያለው ግንኙነት የተረጋጋና ተስፋ ሰጪ ሆኗል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሽግግራችን መሠረት እየያዘ ነው፡፡ አዲስ በተቋቋመው የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አስተባባሪነት በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ደረጃ ያሉ ሥር የሰደዱ ማኅበረሰባዊ ቅራኔዎች ዕልባት ማግኘት ጀምረዋል፡፡ ከቅራኔና ከጥላቻ ይልቅ የይቅርታና ዕርቅ አስተሳሰቦች በማኅበረሰቡ ዘንድ፣ እንዲሁም በመደበኛና በማኅበራዊ መገናኛዎች በየዕለቱ ተቀባይነታቸው እየጨመረ መጥቷል፤›› በማለት፣ የዚህን ቢሆን መግቢያ የሚያስቀምጠው ሰነዱ፣ አሁንም ቢሆን ተግዳሮቶች መኖራቸውን ያስገነዝባል፡፡
እነዚህ ተግዳሮቶች በመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ አሁንም ቢሆን ተቃውሞዎች መነሳት መቀጠላቸውን፣ የተደራጁ ወጣቶች በመላው አገሪቱ ወከባዎችን እየፈጠሩ መገኘታቸው፣ የዜጎችን መፈናቀል ማስቆም አለመቻሉ፣ በፍጥነት እያደገ የሚገኘው የሕዝብ ብዛት፣ ወዘተ እንደሆኑ በመጠቆም ጠንካራ ሥራ የሚጠይቁ ጉዳዮች እንደሆኑም ያሳስባል፡፡
ስለዚህም የንጋት ቢሆን፣ ‹‹የ2012 ዓ.ም. ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ ነው፣ መንግሥት በፍጥነት እያሻቀበ ለመጣው የሕዝብ ቁጥር ብዛት መፍትሔ ለማምጣት እየሠራ ነው፣ በ2017 ዓ.ም. ትኩረታችን ጠንካራ ተቋማት ግንባታ ላይ ነው፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለማስተማርና ለማሠልጠን መጠነ ሰፊ ዘመቻ ይካሄዳል፣ ዜጎች በውጤታማ መንገድ እየተደራጁ ይገኛሉ፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመሥራት ይነቃቃል፣ ኢኮኖሚያችን እያደገ ነው፣ መንግሥት በኢኮኖሚው ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ያለውን ባለቤትነት ይለቃል፣ በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የምንከተለው አቀራረብ ተቀይሯል፣ መንግሥት በመላው አገሪቱ ሕግና ሥርዓትን ለማስፈን የሚችልበት የተሻለ አቋም ይዟል፣ በ2020 ዓ.ም. ምርጫዎች የበለጠ ተዓማኒ እየሆኑ መጥተዋል፣ በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ትክክለኛና የተሻለ ቁርጠኝነት ይታያል፣ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን አረጋግጣለች፣ በ2027 ዳታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ተችሏል፣ ማኅበራዊ ዕድገቱ ተሻሽሏል፣ በ2032 ዓ.ም. የተሳካ ዴሞክራሲያዎ ሽግግር ዕውን ይሆናል፣ ይነጋል፤›› በማለት ምሥልን ይከስታል፡፡
በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ባህልና ጠንካራ መሪዎች ስላሏት፣ በክፍለ አኅጉሩና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚናን እየጫወተች እንደምትገኝ ይተነብያል፡፡
በሁለተኛው ቢሆን የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል በማለት፣ ‹‹ባለፉት ዓመታት መንግሥት በሕዝቡ ላይ የተስፋ መንፈስ የዘሩ ለውጦችን አካሂዷል፣ ኢኮኖሚውም በንፅፅር የተሻለ ደረጃ ላይ ነው፤›› ብሎ በመገምገም፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እየሠራ አለመሆኑን፣ የማዕከላዊ መንግሥት በ2012 ዓ.ም. ያለው ተቀባይነት ዝቅተኛ መሆኑንና የዴሞክራሲ ተቋማት መዳከማቸውን በመጥቀስ ጉድለቶችን ይጠቁማል፡፡
ስለዚህም ወደፊት ምሥል ዕይታ ሲገባ፣ ‹‹የ2012 ምርጫ የፖለቲካውን ምኅዳር ብዙ አልቀየረውም፣ የተፈጠረው ክፍተት በአንዳንድ አካባቢዎች አዳዲስ የመብት ተሟጋቾች እንዲፈጠሩ እያደረጉ ነው፣ የኢትዮጵያ ዕድገት ባለፉት አሥር ዓመታት እንደነበረው እየቀጠለ ነው፣ ዜጎች የማኅበራዊ ልማት ዕድገት አለመምጣቱ በእጅጉ ያሳስባቸዋል፣ በፉክክር ቤት እንደሚታየው በተናጠል ማሰብ ወጥነት ያለው ተጠያቂነት እንዳይሰፍን አድርጓል፣ በ2022 ዓ.ም. ከባድ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀናል፣ የብድር ግዴታዎችን በአግባቡ አለመፈጸማችን ለውጭ ጣልቃ ገብነት ተጋላጭ አድርጎናል፣ በሕገወጥ መንገድ የታጠቁ በንቃት እየተንቀሳቀሱና ብሔርን፣ የሀብት ደረጃንና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው በዜጎች ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ነው፣ በ2027 ዓ.ም. የተለያዩ ቀውሶችን እያስተናገድን እንገኛለን፣ በ2037 ዓ.ም. የፌዴራል ሥርዓቱን ድክመት ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ይፈጠራሉ፤›› በማለትም እስከ 25 ዓመታት ድረስ ሊኖሩ ስለሚችሉ ሁኔታዎች ትንበያ ይሰጣል፡፡
በቢሆን ሦስት አፄ በጉልበቱ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመንግሥት መር የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተመራ በንፅፅር የተሻለ ዕድገት ማሳየቱንና በአፍሪካ ትልቁ ግድብ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ታልሞ እየተገነባ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ማኅበራዊ ዕድገቱ ከኢኮኖሚና ከመሠረተ ልማት ዕድገቱ በእጅጉ ወደኋላ ቀርቷል በማለት ይገመግማል፡፡ ያልተገታ የሕዝብ ዕድገት፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ለውጥ እንዲደረግ ተቃዋሚዎች ቢናገሩም ምን እንደሚቀየር ከስምምነት መድረስ ማዳገቱ፣ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች የተደረጉ ድርድሮች ምርጫ 2012 ሲደርስ መቋረጣቸው በተግዳሮትነት ተመልክተዋል፡፡
ከዚህ በመነሳትም፣ ‹‹በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የ2012 ዓ.ም. ምርጫን በአብላጫ ድምፅ ያሸንፋል፣ በ2017 የሴቶች፣ የወጣቶችን የሙያ ማኅበራትን ጨምሮ የሲቪክና ማኅበራዊ ድርጅቶች በመንግሥት ተፅዕኖ ሥር ይወድቃሉ፣ መንግሥት በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ሳቢያ በመላው አገሪቱ አመፅ እየተባባሰ ይገኛል፣ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው አመፅና መፈናቀል የጋራ መግባባት ላይ መድረስን አይጨበጥ አድርጎታል፣ ኢንቨስትመንትና የመሠረተ ልማት ግንባታ በመቀጠሉ ዕድገቱ ቀጥሏል፣ የአገዛዙ መሠረታዊ መነሻ ማናለብኝ ባዮች እንደሚያደርጉት ሁሉ በተገኘው መንገድ ሁሉ ራሱን በሥልጣን ላይ መቆየት ነው፤›› በማለት በ2032 ዓ.ም. መንግሥት ኢትዮጵያን እያጋጠሟት በሚገኙ ተግዳሮቶች ላይ ቁጥጥር በማጥበቁ አንዳንድ ስኬቶችን አስመዝግቧል፣ የሕዝብ ቁጥር ዕድገቱ ተመጣጥኗል ሲል መፃኢውን ጊዜ ይጠቁማል፡፡
በአራተኛው ቢሆን ሰባራ ወንበር፣ በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት የተመዘገቡ ውጤቶች ቢኖሩም ድህነት፣ የዕርዳታ ጥገኝነት፣ ብሎም ዋና ዋና አገራዊ እሴቶችን ጠብቆ መሄድ አለመቻል በተግዳሮትነት የተቀመጡ ሲሆን፣ የሰባራ ወንበር ቢሆን አንዱ ባህርይ የሥራ ፈጠራ አቅም አለመከበር ነው በማለት፣ አሁን ባለው ሥራ አጥነት በከተሞች ብቻ አንድ ሚሊዮን ሥራዎች በየዓመቱ መፈጠር እንዳለባቸው ይጠቁማል፡፡
በዚህ ረገድም፣ ‹‹በትምህርት ላይ ዕድገት እያሳየን ስለመጣን የተማሩ ዜጎች ብዛት እየጨመረ ነው፣ ችግሮቻችንን ግን አልቀረፉም፣ ራዕያችንን ዕውን ለማድረግ ብርታት አላገኘንም፣ የአቅም ዕጦቱ በመንግሥት ተቋማት ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ በሁሉም ማኅበራዊ መስኮች ጭምር የሚንፀባረቅ ነው፣ በ2012 ዓ.ም. ምርጫ ገዥው ፓርቲ የሚያሸንፍ ቢሆንም ምርጫው ተጭበርብሯል የሚሉ ሒሶች ይበረክታሉ፣ የፌዴራል መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ከክልል መንግሥታት ጋር የመሥራት አቅም የለውም፣ በ2017 ዓ.ም. ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ ሄዷል፣ በሁሉም ዘንድ የተመጣጠነና ፍትሐዊ አይደለም፣ የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው፣ በ2022 ዓ.ም. የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰው ተፅዕኖ በከፍተኛ ደረጃ ተባብሷል፣ በዓባይ ወንዝ ፍትሐዊ አጠቃቀም ዙሪያ ኢትዮጵያ ከአጎራባች አገሮች ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብታለች፣ በ2027 ዓ.ም. በፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ ሕዝብ ከየክልሉና ከየመኖሪያ ቤቱ በብዛት ይፈናቀላል፣ ተዓማኒ ምርጫዎችን ማካሄድ የምንችልበት አቅም አልገነባንም፣ በ2037 ዓ.ም. በየዓመቱ ግማሽ ሚሊዮን ያህል የመኖሪያ ቤቶች እየገነባን እንገኛለን፤›› በማለት የመፃኢውን ጊዜ ምሥል ይከስታል፡፡
እነዚህ ቢሆኖች ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድን ጊዜ አልፋና የመጀመርያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ከተፈቱ በኋላ የተከናወነውን ተመሳሳይ ሥራ እንደሚመስል የጠቆሙት የሪዮስ ፓርትነርስ ተወካይና የሒደቱ አማካሪ አዳም ካህን፣ ከአራቱ አንዱ አዎንታዊ፣ የተቀሩቱ ደግሞ አሉታዊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት የእሳቸው ሚና ዘዴ ላይ ማማከር እንደነበር የጠቆሙት ካህን፣ በ50 አገሮች ያላቸውን ተሞክሮ የማጋራት ሚና እንደነበራቸውም ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የዚህ ሥራ ውጤት የሚያሳየው በመደማመጥ ውስጥ ያለውን ጥበብ፣ የአንድነትና የመተባበር ልምድ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ሳይቸግረን የተቸገርነው ራስን በሌላው ቦታ አድርጎ ማየት ስለሆነ፣ እያለን የሌለን ራስን በሌላ ቦታ አስቀምጦ ማየት ስለሆነ ይኼ ሒደት ይኼንን የሰበረ ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ ‹‹አዲስ የፖለቲካ ሒደትን ለመገንባት አስቸኳይ የሆነ ሒደት ነው፤›› ሲሉም አሞካሽተዋል፡፡