9 ዲሴምበር 2019

የሲዳማ ክልልነት በሕዝበ ውሳኔነት መፅደቁን ተከትሎ፤ በደቡብ ክልል የተለያዩ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ተጠናክረው እየቀረቡ ነው። እነዚህ የክልልነት ጥያቄዎች አዲስ ሳይሆኑ ከዚህ ቀደም የተነሱና ምላሽ ሳያገኙ በመንከባለል ላይ ናቸው።
ከሁሉም ጥያቄዎች የሚለየው የጌዲዮ ዞን ጥያቄ ነው የሚሉት የአካባቢው ምሁራንና ተወላጆች በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ ዞኑ በደቡብ ክልል ውስጥ መቀጠል አይችልም ሲሉ ያብራራሉ።
የጌዲዮ ዞን በይፋ የክልል እንሁን ጥያቄውን ለዞኑ ምክር ቤት ያቀረበው ሕዳር 11፣ 2011 ዓ.ም መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የዞኑ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ የጥያቄውን ተገቢነት በማመን ቡድን አዋቅሮ ጉዳዩን አሳልፎ ሰጥቷል።
ይህንን ቡድን የዞኑ ምክር ቤት ሕግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ እንዲያስተባብረው ተደርጎ፣ የብሔረሰቡ ተወላጅ ምሁራን ተካተውበት የጥያቄውን ተገቢነት መርምሮ እንዲያቀርብ ሥራ ተሰጥቶት ነበር።
የጌዲዮ ዞን ምክር ቤት የሕግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወደሆኑት ግለሰብ፣ ይህ ጉዳይ ምን ደረሰ ብለን ብንደውልም በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው በመናገራቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም።
በደቡብ ክልል ምክር ቤት የብሔረሰቦች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና በጌዲዮ ዞን ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ውስጥ የባህል ታሪክና ቅርስ ጥናትና ልማት አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ፀጋዬ ታደሰን ይህ የዞኑ ምክር ቤት ወደ ሕግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የመራው ጥያቄ ምን ደረሰ ብለን ጠይቀናቸዋል።
ከሕዳሩ ውሳኔ በኋላ ሚያዚያ ላይ በድጋሚ የዞኑ ምክር ቤት መሰብሰቡን አስታውሰው ሚያዚያ 16፣ 2011 ዓ.ም በተጠራው ጉባዔ የተሰጠው ሥራ ምን ደረሰ በማለት ጉዳዩን መልሶ መገምገሙን ይናገራሉ።
ነገር ግን በነበረው የአስፈጻሚው አካል ምክንያት ጉዳዩን ወደ ፊት መግፋት እንዳልተቻለ ቋሚ ኮሚቴው በወቅቱ ሪፖርቱን ማቅረቡን ያስታውሳሉ።
በዚህ ስብሰባ ላይ የተወሰነውን ሲናገሩም፣ ሥራ አስፈጻሚው በድጋሚ ይህንን ውክልና ወስዶ እስከ ግንቦት 15፣ 2011 ዓ.ም ድረስ የሚሰራው ሥራ ሰርቶ፣ በአስቸኳይ ለክልል ምክር ቤት ጥያቄው እንዲቀርብ ወስኖ ማስተላለፉን ይናገራሉ።
የዞኑ ምክር ቤት በክልል እንዲደራጅ፣ የራሱን አስተዳደር መመስረት እንዳለበት ውሳኔውን አሳልፏል የሚሉት አቶ ጸጋዬ ይህ ጥያቄ ግን እስካሁን ድረስ ለክልሉ አለመቅረቡን አረጋግጠዋል።
አቶ ጸጋዬ “ከደህዴን የሥራ አስፈጻሚ አካላት ባለው ግፊት የተነሳ የዞኑ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ይህንን ተልዕኮውን መወጣት አልቻለም” ሲሉ ያስረዳሉ።
• የወላይታ ዞን ተወካዮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ሊወያዩ ነው
ከጥቅምት 25-28 2012 ዓ.ም ምክር ቤቱ በነበረው ስብሰባ ላይም ይኸው ጉዳይ መነሳቱን የሚያስታውሱት አቶ ጸጋዬ አስፈጻሚው አካል የተሰጠውን ውክልና እየተወጣ ባለመሆኑ እንዲወጣ የሚል ውሳኔ በድጋሜ ተላልፏል ይላሉ።
የክልልነት ጥያቄ ለምን አሁን ቀረበ?
የጌዲዮ ሕዝብ በተደጋጋሚ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን ለቢቢሲ የገለጹት በዲላ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ታደሰ ኪጤ “ጥያቄው ግን ሲታፈን” መኖሩን ያስረዳሉ።
አቶ ጸጋዬ በበኩላቸው ይህ የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለዞኑ ምክር ቤት በይፋ መቅረብ የጀመረው በ2010 ዓ.ም ከዞኑ ውጪ በሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ላይ የደረሰው መፈናቀልና ሞት በክልሉ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት ባመቻሉ መሆኑን ያስቀምጣሉ።
በወቅቱ በምክር ቤቱ አባላት ላይ “ስንበደል ቀጥታ የፌደራል መንግሥቱ አባል ብንሆን ኖሮ ጥያቄያችንን ያለ ስማ በለው በቀጥታ ማቅረብ እንችላለን” የሚል ስሜት እንደነበርም ያስታውሳሉ።
አቶ ጸጋዬ ለክልልነት ጥያቄው ገፊ ምክንያቶች ናቸው ብለው ካስቀመጧቸው ነጥቦች መካከልም በ2009 ዓ.ም በዞኑ ተፈጥሮ በነበረው ቀውስ ንጹኃን ከጥፋተኞች ሳይለዩ በጅምላ መታሰራቸውን ነው።
• ወገኖቹን ለመርዳት ጠመኔ የጨበጠው ኢትዮጵያዊው ሐኪም
አቶ ጸጋዬ በ2009 በዞኑ ከተሞች የተፈጠረውን ሲያስታውሱ “ጥፋተኞች መጠየቅ ቢኖርባቸውም” ይላሉ፣ “በሥፍራው የነበሩም ያልነበሩም፣ በድርጊቱ የተሳተፉም ያልተሳተፉም፣ ከሀገር ውጪ የነበሩ ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ፣ የዞኑ ተወላጅ ነጋዴዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች በጅምላ ታስረዋል” በማለት ላይ በዚህ የጅምላ እስር ከ3000 ያላነሱ ሰዎች እስር ቤት ቢገቡም ማስረጃ በመጥፋቱ መለቀቃቸውን ይገልጻሉ።
በ2009 ዓ.ም መስከረም ወር መጨረሻ በጌዲዮ ዞን ይርጋጨፌ፣ ኮቸሬ፣ ዲላ፣ ወናጎ፣ ፍስሃ ገነትና ጨለለቅቱ አካባቢዎች ግጭቶች ተከስተው የተለያዩ ሰብዓዊ ጥሰቶች መፈፀማቸውን በወቅቱ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በመግለጫው ላይ አስታውቆ ነበር።
በዚያን ጊዜ የተፈጠረው የዞኑን ማህበረሰብ በአንድነት ያስደነገጠ መሆኑን በመጥቀስ፣ በመንግሥት የጸጥታና ደህንነት መዋቅር አካላት የተፈጸሙ ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ግን የዞኑ ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ፍላጎት ያለማንም ጣልቃ ገብነት የሚለው ሀሳባቸውን እንዲገፉበት እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ።
በዚህ መካከል በ2010 ዓ.ም ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የጌዲዮ ማህበረሰብ አባላት መፈናቀልና ያገኘው ትኩረት ማነስ ለጥያቄው ወደ ፊት መምጣት ሌላ ሰበብ መሆኑን ያብራራሉ።
አቶ ጸጋዬ አክለውም “መፈናቀሉ ብቻ ሳይሆን የሕግ የበላይነት ሳይረጋገጥ፣ የተፈናቀሉት ለተራዘመ መከራ መጋለጣቸው ሌላው ምክንያት ነው” ብለዋል።
የጌዲዮ ሕዝብ የማንነት ጥያቄዎች ታሪክ
የጌዲዮ ሕዝብ ይላሉ ፕሮፌሰር ታደሰ፣ ባሌ የሚባል የራሱ የሆነ ጠንካራ የአስተዳደር ስርዓት ያለው ነው። አቶ ጸጋዬ በበኩላቸው የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ያለው ሕዝብም ነው ሲሉ ያክላሉ።
ነገር ግን ይላሉ ሁለቱም፣ ሕዝቡ ከለመደው የአስተዳደር ሥርዓት ውጪ የሆነ ነገር ሲመጣበት ከምንሊክ መስፋፋት ጀምሮ እምቢተኝነቱን ገልጿል።
የጌዲዮ ሕዝብ ባህላዊ የሆነ የመሬት ሥሪት፣ ደረባ የሚባል ፣ ያለው ሕዝብ ነው የሚሉት ግለሰቦቹ፣ በ1880ዎቹ መጨረሻ የምንሊክ ጦር ወደ ስፍራው መስፋፋት የጌዲዮን የመሬት ባለቤትነት ሙሉ በሙሉ ነጥቋል ይላሉ።
የጌዲዮ ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የሚያነሱ አካላት በጋራ የሚጠቅሱት ሌላ ታሪካዊ ክስተት በ1952 ዓ.ም የተካሄደውን የገበሬዎች አመጽ ነው።
• ሲፈን ሐሰን፡ ”ለኢትዮጵያ የመሮጥ ፍላጎት ኖሮኝ አያውቅም”
ይህ የገበሬዎች አመጽ የተካሄደው ‘ምችሌ’ ላይ መሆኑን የሚጠቅሱት እነዚህ ግለሰቦች የምችሌ የአርሶ አደሮች አመጽ በጌዲዮ ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዳለው ያብራራሉ።
ፕሮፌሰር ታደሰ በበኩላቸው ከዚህ ጦርነት በኋላ የኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ከጌዲዮ አካባቢ ሕዝቦችን በማንሳት ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢ ማስፈሩን ይገልጻሉ።
በደርግ ጊዜ ቢሆንም ይላሉ ፕሮፌሰር፣ ከ1971 ዓ.ም እስከ 1973 ዓ.ም ድረስ የነበረው አመጽ ዋና ምክንያት የራሱን ምርት ገበያ በሚወስንለት ዋጋ መሸጥ እንዲችል የጠየቀ፣ በራሴ ጉዳይ ራሴ ልወስን የሚል እንደነበረ ያብራራሉ።
ይህ አመጽ ከይርጋ ጨፌ ራቅ ብላ በምትገኘው ‘ራጎ ቅሻ’ ላይ መካሄዱንም ያስታውሳሉ።
ይህ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በኢህአዴግ አስተዳደር ወቅት ቀጥሎ የፍትሀዊነት ተጠቃሚነት ጥያቄ፣ የእኩልነት የዲሞክራሲ ጥያቄ እስከዛሬ ድረስ መቀጠሉን ፕሮፌሰር ታደሰም ሆኑ አቶ ጸጋዬ ይናገራሉ።
ፕሮፌሰር ታደሰ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን በመጣባቸው የመጀመሪያ ዓመታት፣ የጌዲዮ ሕዝብ ከሲዳማ እና ከምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ሕዝቦች ጋር በአንድነት ይኖር ነበር በማለት፣ በአካባቢው በተለይ በኦሮሚያ ጉጂ ዞንና በጌዲዮ መካከል በ1988 በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ የተወሰኑ አካባቢዎች ወደ ኦሮሚያ እንዲጠቃለል መደረጉን ይገልጻሉ።
ፕሮፌሰር በወቅቱ የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ሕጋዊውን መንገድ መከተሉ ላይ ጥያቄ እንዳላቸው በመግለጽም፣ በአባያ አካባቢ የሚኖሩ የጌዲቾ ማህበረሰብ፣ በወቅቱ ከጌዲዮ ጋር አንድ ወረዳ የነበሩ ቢሆንም ወደ ኦሮሚያ መካለላቸውን ያስታውሳሉ።
ኢህአዴግ ሥልጣን እንደያዘ በመሰረተው ክልል 8 ውስጥ የኮሬ ማህበረሰብም ሆነ ቡርጂ ከጌዲዮ ጋር ነበሩ የሚሉት ፕሮፌሰር እነዚህም ግን ወደ ኦሮሚያ መካለላቸውን ያነሳሉ።
እነዚህ ጎረቤቶች በአሁን ሰአት ከጌዲዮ መራቃቸውን በመናገር እንደ ጌዲቾ ያሉ በባህልም በቋንቋ የሚዛመዱት ሕዝቦች ጋር የጌዲዮ ሕዝብ ተራርቋል ይላሉ።
ጌዲዮ በዞን ሲካለል ጌዲቼ፣ ኮሬ እንዲሁም በቡርጂ በኢህአዴግ አስተዳደር የመጀመሪያ አመታትም ሆነ ከዚያ በፊት ከእኛ ጋር ነበሩ የሚሉት ፕሮፌሰር ታደሰ በአሁኑ ወቅት የጌዲዮ ዞን ከሲዳማና ከኦሮሚያ ጋር እንደሚዋሰን ያስረዳሉ።
• ኤችአይቪ በኢትዮጵያ ከሦስት ክልሎች ውጪ በወረርሽኝ ደረጃ ነው ያለው
በአሁኑ ወቅት በምስራቅና በምዕራብ ጉጂ የሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች ተበታትነው የሚኖሩ ጌዲዮዎች እንዳሉ ገልፀዋል።
ክልል የመሆን ጥያቄው ተቀባይነት ባያገኝስ?
የጌዲዮ ሕዝብ ፍላጎት ክልል የመሆን ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ታደሰም ሆኑ አቶ ጸጋዬ፣ ከኦሮሚያም ጋር ሆነ ከሲዳማ ክልል ጋር የመቀላቀል ፍላጎት እስካሁን ድረስ ከሕዝቡ አለመነሳቱን ይገልጻሉ።
ፕሮፌሰር ታደሰ በበኩላቸው፣ የጌዲዮ ሕዝብ ከሲዳማም ሆነ ከኦሮሚያ ሕዝቦች ጋር የኩሽ ሕዝቦች በመሆናቸው የሚጋሩት ነገር ቢኖርም የጌዲዮ ሕዝብ የራሱ ባህል፣ ቋንቋ እንዲሁም ማንነት እንዳለው አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
ለዚህም በማስረጃነት የሚያነሱት በአጼ ምንሊክ ወደ ጌዲዮ አካባቢ ሲመጡ እንኳ ከኦሮሚያም ሆነ ከሲዳማም ሕዝብ ጋር አልነበርንም፤ ህዝቡ ራሱን ችሎ ይኖር እንደነበር በወቅቱ የነበሩ መረጃዎችን በማጣቀስ ያስረዳሉ።
ፕሮፌሰር አክለውም ከአንድ ትንሽ ቦታ ከፍተኛ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ የሚያቀርበው ጌዲዮ ብቻ ነው በማለት፣ ዞኑ ለፌደራል መንግሥቱም ሆነ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እንዳለ ያብራራሉ።
ኦሮሚያም ሆነ ሲዳማ ቡና ቢያቀርቡም ክልሎቹ ሰፊ ናቸው የሚሉት ፕሮፌሰር፣ ከትንሽ ስፍራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የጌዲዮ ዞን ይክልልነት ጥያቄው መታፈኑን ያስረዳሉ።
“የራሳችን ኢኮኖሚ አቅም አለን ፤ የራሳችን ሕዝብ ባህል ቋንቋ ታሪክ አለን ሲሉ” ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።
• ኢትዮጵያ የካንሰር መከላከያ ክትባት ከሚሰጡ ጥቂት አገራት አንዷ ናት
ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋር የጌዲዮ ሕዝብ ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖረው የሚያደርገው ጥያቄና ትግል “ካድሬዎችና አንዳንድ አካላት ለማፈን የሚሞክሩ ቢኖሩም ሲዳማ ክልልነቱን በሕዝበ ውሳኔ ሲያረጋግጥ ያለ ምንም ውጣ ውረድ ክልል መሆን ነበረብን” ይላሉ።
በደቡብ ክልል በአሁኑ ሰዓት ከ50 በላይ ብሔሮች ቢኖሩም አሁን ሲዳማ ክልል ሲሆን በመልከ አምድሩ አቀማመጥ የተነሳ ከቀሪዎቹ የክልሉ ሕዝቦች ጋር መገናኘት እንደማይችሉ በማስቀመጥም፣ ከደቡብ ጋር አንድ ክልል ብሎ ጌዲዮን መጥራት ፈታኝ መሆኑን ያስቀምጣሉ።
አቶ ጸጋዬ በበኩላቸው የጌዲዮ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄን ተገቢነት ሲያብራሩ ሕገመንግሥቱን በመጥቀስ ነው።
ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 በአንድ ክልል ውስጥ ያሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል መመስረት ይችላሉ የሚለውን አንቀፅ በመጥቀስ “ሕገመንግሥቱን ካየን ሰጪና ከልካይ ያለበት አይደለም” ሲሉ ይጠቅሳሉ።
ፕሮፌሰር ታደሰ በበኩላቸው የሕዝቡን ጥያቄም ለመንግሥትም ሆነ ለሁሉም አካላት የማቅረብ ሥራው እንደሚቀጥል ተናግረው፣ “ጥያቄያችን በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች መለስ ዜናዊና ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም አሁን ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብናቀርብም ታፍኖ ቆይቷል፤ መልስ እስክናገኝ እንቀጥልበታለን” ብለዋል።