4 ዲሴምበር 2019

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ያስመዘገበቻቸው የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን ጨምሮ (በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈው አርባዕቱ ወንጌል እና ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ለሞስኮው ንጉሥ ኒኮላር ቄሳር ሁለተኛ የጻፉት ደብዳቤ ይገኙበታል) የበርካታ ጥንታዊ መዛግብት ባለቤት ናት።
እነዚህ ጽሑፎች የቀደመውን ዘመን ታሪክ ከማንጸባረቅ ባሻገር የማኅበራዊ መስተጋብር፣ የፖለቲካዊ ሥርዓት፣ የህክምና፣ የሥነ ከዋክብት ጥናት እና ሌሎችም መረጃዎችን ይዘዋል።
ዲጂታይዜሽን (ጽሑፎችን በካሜራ ቀርጾ በዲጂታል ቅጂ ማስቀመጥ) እነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገሩበት ዘመነኛ መንገድ ነው።
ያለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን ሰዎች እንደቀድሞው ጽሑፍ የሚያገላብጡበት ሳይሆን በኮምፒውተር መረጃ የሚያገኙበት ነው። ይህንን ከግምት በማስገባትም በርካታ አገሮች ጥንታዊ ጽሑፎችን ዲጂታይዝ ማድረግ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በብራና ላይ በግዕዝና በአረብኛ የሠፈሩ ጥንታዊ ጽሑፎችን በዲጂታል ቅጂ የማስቀመጥ ሂደት ውስጥ ከሚሳተፉት አገራዊ ተቋሞች መካከል ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ይጠቀሳል።
ውጪ አገር የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች እና ተመራማሪዎችም ጥንታዊ መዛግብትን ዲጂታይዝ ማድረግ ጀምረዋል።
የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ሰው ሰራሽ ወይም ተፈጥሯዊ አደጋ ቢደርስባቸው፤ ቅጂያቸውን ለማትረፍ በካሜራ ይቀረጻሉ። ቅርሶቹ ባሉበት ቦታና ይዞታ ተጠብቀው፤ ቅጂያቸው ለተመራማሪዎች እንዲሁም መረጃውን ለሚፈልጉ ግለሰቦች በአጠቃላይ ተደራሽ እንዲሆንም ዲጂታይዜሽን ሁነኛ አማራጭ ነው።
• የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን የባህል ጥናት እና ምርምር ማዕከል ተመረቀ
በርካታ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ያሏት ኢትዮጵያ ምን ያህሉን መዛግብት ዲጂታይዝ ማድረግ ችላለች? በባለሙያዎች ከሚነሱ ጥያቄዎች አንዱ ነው። ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አንጻር የጽሑፎቹን ዲጂታል ቅጂ ለተጠቃሚዎች ማድረስ ተችሏል ወይ? ሌላው ጥያቄ ነው።
የዘርፉ ባለሙያዎች በዋነኛነት ከሚያነሷቸው ተግዳሮቶች መካከል በቴክኖሎጂ ብቁ አለመሆንና የባለሙያ እጥረት ይገኙበታል። በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስና የታሪክ ከፍተኛ ባለሙያ እንዲሁም የፊሎሎጂ ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ እስራኤል አራጌ በበኩላቸው የቅርሶቹ ባለቤቶች ዲጂታይዜሽንን እንደማይደግፉ ያስረዳሉ።
የቅርሶቹ ባለቤት ከሆኑት አንዷ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን፤ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶቹ ይሰረቃሉ በሚል ስጋት ዲጂታይዜሽንን እንደማታበረታታ ይናገራሉ።
“በተለይም የውጪ አገር ምሁራን ዲጂታይዝ ለማድርግ ሲመጡ፤ ቅርሶቹ ተዘረፉ ስለሚባል በቤተ ክርስቲያን ዘንድ የዲጂታይዜሽን ጥቅም አይታይም። ቤተ ክርስቲያኗ እንኳን ለውጪ ተመራማሪዎች ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ሠራተኞችም በሯን መዝጋት ጀምራለች።”
ጥንታዊ ጽሑፎችን ለመቁጠር፣ ያሉበትን ሁኔታ ለማጥናትና ለቱሪስቶች ክፍት የሚሆኑበትን መንገድ ለማመቻቸት ሲሞከርም፤ ቤተ ክህነት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኖች አስተዳዳሪዎችም ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ያስረዳሉ።
በእርግጥ ቅርሶች ይሰረቃሉ የሚለው ስጋት መሠረት አልባ አይደለም። ባለፉት ዓመታት በርካታ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ተዘርፈው ከኢትዮጵያ ወጥተዋል። በተለይም ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ብዙ የብራና መጻሕፍት በተለያየ መንገድ በውጪ አገር ሰዎች መወሰዳቸው ይታወቃል።
የቅርስና ታሪክ ባለሙያው እስራኤል፤ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የተወሰዱ ብርቅዬና በሌላ አገር የማይገኙ ቅርሶችን እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ።
“እንደምሳሌ መጽሐፈ ሔኖክ፣ መጽሐፈ ኩፋሌ፣ ገድለ አዳም ወ ሔዋን ይጠቀሳሉ። በሐረርና በደቡብ ወሎ የነበሩ የእስልምና መዛግብትም ተዘርፈዋል። አሁንም በቱሪስቶች፣ በዲፕሎማሲ ሠራተኞችና በሌሎችም ሰዎች የብራና መጻሕፍት እየተሰረቁ እየወጡ ነው።”
• ለኢትዮጵያዊያን የንባብ ወዳጆች ምርጡ መጽሐፍ የትኛው ነው?
ሆኖም ግን መፍትሔው ስርቆትን መከላከል እንጂ ዲጂታይዜሽንን መግታት አለመሆኑን ባለሙያዎች ይስማሙበታል።
የቅርስና ታሪክ ባለሙያው እንደሚሉት፤ በዋነኛነት በሰሜን ኢትዮጵያ ብዙ መጻሕፍት ዲጂታይዝ ቢደረጉም አጥጋቢ ነው ማለት አይቻልም። በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ የተስተዋለው አለመጋጋት የፈጠረው ስጋት ሥራው ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ያክላሉ።
“ከዘመኑ ሥልጣኔ አንጻር ዲጂታይዜሽን አማራጭ የሌለው ዘዴ ነው። የብራና ጽሑፎችን ገልብጦ ማስቀመጥ ጊዜ ይወስዳል፤ በብራና የሚጽፉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥርም እየተመናመነ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ፤ ዲጂታይዜሽን በ1963 ዓ. ም ገደማ መጀመሩን ሰነዶች ያሳያሉ።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቲዎፍሎስ፤ ሜኖሶታ ከሚገኝ የቅዱስ ዩሐንስ ዩኒቨርስቲ፣ የሂል ገዳም የብራና ቤተ መጻሕፍት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት በፎቶ ተቀርጸው እንዲቀመጡ ማድረጋቸውን ባለሙያው እስራኤል ይናገራሉ።
ይህ እንቅስቃሴ በ1980ዎቹ በአገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ በጊዜያዊነት ተቋርጦ ነበር።
ባለሙያው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዲጂታይዜሽን ከሚጠቅሷቸው የውጪ ተቋሞች መካከል፤ የኢትዮጵያ ብራና ማይክሮፊልም ቤተ መጻሕፍት (ኢትዮጵያን ማኑስክሪፕት ማይክሮፊልም ላይብረሪ ወይም ኢኤምኤምኤል) ይገኝበታል። በተቋሙ ወደ 9238 የብራና መጻሕፍት በማይክሮፊልም መቀረጻቸውን ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ተቋም (ኢንስቲትዮት ኦፍ ኢትዮጵያን ስተዲስ ወይም አይኢኤስ) ከተሠራው የፕ/ር ታደሰ ታምራት እና ሥርግው ሀብለሥላሴን እንቅስቃሴ፤ ውጪ አገር መቀመጫቸውን ካደረጉ መካከል ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌን ይጠቀሳሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የብራና መጻሕፍትን ዲጂታይዝ ያደርጋል።
የሙዝየም ባለሙያ እና በአሁን ወቅት በአረብኛና ግዕዝ ጽሑፎች ላይ ጥናት እያደረጉ ያሉት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ እንደሚሉት፤ በአገር ውስጥም ይሁን በውጪ አገር ዲጂታይዝ የሚደረጉ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ተደራጅተው ለተጠቃሚዎች የሚቀርቡበት ወጥ አሠራር ያስፈልጋል።
“ለሥራው ያለው ተነሳሽነት ጥሩ ቢሆንም ማቀናጀቱ ላይ ክፍተት አለ። አጠቃቀሙ ሕግና ሥርዓት ይፈልጋል” ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከድንጋይ ጽሑፎችና ከዋሻ ሥዕሎች አንስቶ በብራና ላይ የሰፈሩ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ባለቤት እንደመሆኗ፤ በተለያየ ዘመን የነበሩ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶችን ዲጂታይዝ አድርጎ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል።
ፕሮፌሰር አህመድ፤ በግዕዝም በአረብኛም በየቦታው የሚገኙ ጽሑፎችን በመሰብሰብ ረገድ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች እያደረጉ የሚገኙትን ጥረት ያደንቃሉ።
• በኦሮምኛና በትግርኛ አፋቸውን የፈቱ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ባለውለታዎች
ሀምቡርግ ዩኒቨርስቲ፤ በአፍሪካ ቀንድ የእስልምና ጽሑፍን የማሰባሰብ ንቅናቄውንም ይጠቅሳሉ። ጥንታዊ ጽሑፎች በተጠቀሱት የአገር ውስጥና የውጪ አካሎች ዲጂታይዝ መደረጋቸው ቢበረታታም፤ ወደ አንድ ማዕከል መምጣት እንዳለባቸው ያስረግጣሉ።
ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ የሚመራ ሥርዓት ከተዘጋጀ፤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደራሽ እንደሚሆኑም ያክላሉ።
“ተመራማሪዎች እንዴት እንደሚጠቀሙበት ደንብ መውጣት አለበት፤ አቀራረቡም ሕጋዊ አካሄድ ያስፈልገዋል።”
ጥንታዊ ታሪክን፣ ማኅበራዊ ኑሮን፣ ምጣኔ ሀብትን፣ ፖለቲካን፣ ሀይማኖትን ወዘተ. . . የሚያሳዩትን መዛግብት በመተንተን የዛሬው ትውልድ ጥቅም ላይ እንዲያውለው የሚያደርግ የተማረ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግም ፕ/ር አህመድ አያይዘው ያነሳሉ።
“ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አንጻር ብዙ የሥነ ጽሑፍ ሀብት አለን። ሚስጥሮቻችን ብዙ ናቸው። የቀደመውን ዘመን እውቀት ማብላላት፣ ወደ ዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ መለወጥም ያስፈልጋል። እኒህ የትላንት እውቀቶች ለአገርም፣ ለዓለምም ይበጃሉ” ይላሉ።
ጥንታዊ ጽሑፎችን ዲጂታይዝ የማድረግ እንቅስቃሴ በአንድ አካል መመራት እንዳለበት የሚያስረዱት ደግሞ በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ (ወመዘክር) የመረጃ ሀብቶች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሉእመቤት ጌታቸው ናቸው።
“በአገር ውስጥም በውጪም እንቅስቃሴ አለ። ሁሉም በየራሱ ዘርፍ መሮጡ ግን ውጤታማ አያደርግም። ሁሉም በየራሱ መንገድ ሲሄድ ክፍተት ይፈጠራል። ሀብቶቹ ሊጠፉም ይችላሉ። ስለዚህም የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መሥራት አለባቸው።”
ወመዘክር በአዋጅ የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን ዲጂታይዝ ያደርጋል፤ የመዛግብቱን ቅጂ አከማችቶም በቤተ መጻሕፍቱ ለተጠቃሚዎች ያቀርባል።
መዛግብቱ በድረ ገጽ ተለቀው ማንኛውም ሰው ባለበት ሆኖ መጠቀም እንዲችል ፖሊሲ ቢረቀቅም ገና አልጸደቀም። ዳይሬክተሯ እንደሚሉት፤ ሰዎች ያለውን ክምችት እንዲያውቁ እንዲሁም በሚፈልጓቸው ወቅትም እንዲጠቀሙ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል።
“ሙሉ መረጃው በድረ ገጽ የሚለቀቅ፣ የማይለቀቅም ሊኖር ይችላል። ሰው የትኛውን መረጃ፣ እንዴት ይጠቀምበት? በነጻ ይሁን ወይስ በክፍያ? የሚለውም በፖሊሲ የሚወሰን ይሆናል” ሲሉ ያስረዳሉ።
ወመዘክር የትኛው የሥነ ጽሑፍ ቅርስ የት ይገኛል፤ የሚለውን በዳሰሳ ጥናት ይለያል። በጥቆማ የሚያገኛቸው መዛግብትም አሉ። ቅርሶቹ እንዴት ተጠብቀው መያዝ እንዳለባቸው ለባለቤቶቹ ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር ዲጂታል ቅጂም ይወስዳል።
የዲጂታይዜሽን ጅምሩ ቢኖርም ሂደቱ አመርቂ አለመሆኑን ሙሉእመቤት ያስረዳሉ። የባለሙያ እጥረትና የቴክኖሎጂ ውስንነትም በሚፈልጉት መጠን እንዳይሄዱ እንቅፋት ሆነዋል። መዛግብቱ የት እንዳሉ ለማወቅና ለመሰነድ የሚደረገው ጥረት የተጓተተ መሆኑንም ዳይሬክተሯ ያክላሉ።
“ወመዘክር እየሞከረ ነው እንጂ እየሠራ ነው ለማለት ያስቸግራል። እየሠራን ነው ለማለት የሚፈለገውን ያህል እየሠራን አይደለም፤ የምንሰበስባቸው መዛግብት ቢኖሩም በቂ አይደሉም።”
የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን እንዲሰበስቡ በአዋጅ ቢፈቀድላቸውም የመዛግብቱ ባለቤቶች ቅርሱ ዲጂታይዝ እንዲደረግ ፈቃደኛ የማይሆኑበት አጋጣሚ አለ።
“ለምሳሌ በቤተ ክህነት ማንም ሰው ዲጂታይዝ እንዳያደርግ መመሪያ ወጥቷል። ከመዛግብቱ ባለቤቶች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ እየሞከርን ነው። የእስልምና የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችና ሌሎችም መዛግብትን ከባሌቤቶቹ ጋር በመነጋገር መሰብሰቡን ግን ቀጥለናል።”
ጥንታዊ የኢትዮጵያ መዛግብት ዲጂታይዝ የሚደረጉት አገር ውስጥ ብቻ አይደለም። ከኢትዮጵያ ውጪ ከሚገኙ ተቋሞች የእንግሊዙ ብሪትሽ ላይብረሪ ተጠቃሽ ነው።
በቤተ መጻሕፍቱ የእስያና አፍሪካ ስብስብ ክፍል ውስጥ በ ‘ኢትዮፒክ ኮሌክሽንስ ኢንጌጅመንት ሰፖርት’ የሚሠራው እዮብ ድሪሎ እንደሚናገረው፤ በመላው ዓለም አደጋ ያንዣበበባቸው መዛግብት የሚሰነዱበት ‘ኢንዴንጀርድ አርካይቭስ ፕሮግራም’ የተሰኘ ክፍል አለ።
ይህም ቸል የተባሉ፣ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርሶች የሚሰነዱበት ክፍል ሲሆን፤ በየዓመቱ ጥንታዊ መዛግብትን ለይተው ዲጂታይዝ ለሚያደርጉ ተመራማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።
በዓለም በ90 አገሮች፣ ከ100 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች፣ ከ400 በላይ ፕሮጀክቶች የነበሯቸው ሲሆን፤ ከ 1000 በላይ የኢትዮጵያ ጥንታዊ መዛግብት ዲጂታይዝ ተደርገዋል። ከነዚህ መካከል ከገዳማት የተገኙ መዛግብት ይጠቀሳሉ።
በቤተ መጻሕፍቱ የሚገኙ ጥንታዊ መዛግብት ለሕዝብ እይታ ከመቅረባቸው ባሻገር፤ የ25 መዛግብት ዲጂታል ቅጂም በድረ ገጽ ይገኛል። ባለፈው ዓመት የዘመናት ውጤት የሆኑ ጽሑፎች ዓውደ ርዕይ ተካሂዶም ነበር።
“ዘመናትን ያስቆጠሩ የእውቀትና የጥበብ ሥራዎችን አሳይተናል። ‘አፍሪካን ስክራይብስ፡ ማኑስክሪፕት ካልቸር ኦፍ ኢትዮጵያ’ በሚል የተዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ዋነኛ አላማው ላልታወቁ ኢትዮጵያዊያን ጸሐፍትና ጥበበኞች ቦታ መስጠት ነበር” ሲል እዮብ ይገልጻል።
በቤተ መጻሕፍቱ ከሚገኙ ስብስቦች መካከል የመቅደላ መዛግብን የመሰሉትን በመጥቀስም “የኢትዮጵያዊያን ጸሐፍት የእውቀትና ጥበባዊ ተሰጥኦ መገለጫ ናቸው” ሲል ያስረዳል።
ቤተ መጻሕፍቱ በዚህ ዓመት፤ ወደ 100 የሚደርሱ ጥንታዊ መዛግብትን ለወመዘክር መስጠቱን በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ተቋሞች ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውንም ያክላል።