December 9, 2019

Source: https://mereja.com/amharic/v2/180518

በቅርቡ ይፋ የሆነው የብልጽግና ፓርቲ፣ ለጊዜው አምስት የአገራችን ቋንቋዎች፣ አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ሶማሌኛ፣ አፋርኛና ኦሮምኛ፣ የድርጅቱ የስራ ቋንቋ እንደሚሆን ገልጿል፡፡ የድርጅቱ መሪ ጠ/ሚ አብይ አህመድም ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችም የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ ድርጅታቸው እንደሚሰራ ማሳወቃቸው ይታወቃል፡፡

ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችን የስራ ቋንቋ ይሁኑ ሲባል የሚነሱ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አንደኛው የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ ቋንቋዎች ሲመረጡ መመዘኛው ምንድን ነው የሚለው ነው ? ኢትዮጵያ ወስጥ ከሰማኒያ በላይ ቋንቋዎች አሉ፡፡ ሁሉም የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ ካልተደረገ፣ የተወሰኑት ተመርጠው የተወሰኑት የሚቀሩ ከሆነ፣ በግልጽ ምክንያቶቹና መመዘኛዎቹ መቀመጥ አለባቸው፡፡

ያ ብቻ አይደለም መመዘኛው ፍትሃዊ ስለመሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡የተወሰኑ ቡድኖች፣ አመጽ ስለቀሰቀሱ፣ ወይንም ስላስፈራሩ፣ እነርሱ የሚናገሩት ቋንቋ ቅድሚያ የሚሰጠው ከሆነ፣ መስፈርቱ አመጽና ኃይል ነው ማለት ይሆናል። ያ ደግሞ ለዘለቄታው ችግር የሚፈጥር ነው። ምን ጊዜም በኃይልና በጉልበት በማስፈራራት የሚሆን ነገር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያይል ስለሚሆን። ቋንቋውን መጠቀም ከመግባቢያነቱ አልፎ ሌላ ትርጓሜ እንዲሰጠውም ስለሚያደርግ።

ሁለተኛው ጥያቄ የአፈጻጸም ጥያቄ ነው፡፡ አንድ ቋንቋ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ሆነ ሲባል ምን ማለት ነው ? የቋንቋው ተናጋሪዎች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢዎች በቋንቋ የፌዴራል መንግስት አገልግሎት ያገኛሉ ማለት ነው ? ያ ካልሆነ ደግሞ “ የፌዴራል ሰራተኞች የፌዴራል ቋንቋዎችን ማወቅ ፣ ወይም በያንዳንዱ የፌዴራል መስሪያ ቤት ፣ በሁሉም የፌዴራል ቋንቋዎች ፣ ተገልጋይ ባይኖርም፣ ቋንቁዎቹን የሚናገሩ በእኩልነት መቀጠር አለባቸው” ማለት ነው ? እነዚህም ጥያቄዎች ግልጽ ምላሽና ጥናት የሚጠይቁ ናቸው። ተጨማሪ ቋንቋዎች የፌዴራል የስራ ቋንቋ ይደረጉ ብሎ ሲወሰን ቋንቋዎቹ የፌዴራል ቋንቋ በመሆናቸው የሚከተሉት፣ የሚለወጡ ጉዳዮች በጥልቅና በግልጽ ነቅሶ ማውጣት፣ ለሕዝብም ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል።

ለዚህ ውይይት እንዲረዳን የደቡብ አፍሪካ ተመክሮ ለማየት እንሞክር፡፡ የደቡብ አፍሪካ መንግስት የፌዴራል መንግስት አይደለም፡፡ አሃዳዊ ነው፡፡ በአገሪቷ ከ36 በላይ ቋንቁዎች ይነገራሉ። ከነዚህ መካከል 11 ቋንቋዎች የደቡብ አፍሪካ ኦፌሲል ወይም የስራ ቋንቋዎች ናቸው፡፡ ቋንቋዎቹ፣ የዙሉ (23%)፣ ሾሳ ( 16%)፣ የዳች(ሆላንድ) ዝርያ ያላቸው ነጮች ቋንቋ አፍሪካነርስ ( 14%)፣ እንግሊዘኛ (9.6%)፣ ሰሜናዊ ሶቶ (9.1%)፣ ትሶና (8%)፣ ሴሶቶ ( 7.6)፣ ጾንጋ (4.5)፣ ስዋቲ( 2.5)፣ ቬንዳ ( 2.4) እና ንደቤሌ (2.1 ) ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ አሃዳዊ መንግስት እያለ የቋንቋዎችን ብዝሃነት ማክበር እንደሚቻል ደቡብ አፍሪካ ማሳያ ናት። ፌዴራሊዝም ከሌለ የብሄረሰቦች መብት፣ ቋንቋቸው ይከበርም ማለት አይደለም)

ሌሎች ቋንቋዎች ለምን አልተካተቱም ቢባል አንዱ ምክንያት ከደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ከ2% በታች የሆነ አነስተኛ ቁጥር ስላላቸው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ብዛት የስራ ቋንቋን ለመምረጥ አንደ መስፈርት ተደርጎ ማለት ነው።

ደቡብ አፍሪካን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2007 የተደረገውን የሕዝብ ቆጠራ ዉጤት መሰረት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከ2% በላይ እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋ የሚነገሩ ቋንቋዎች፣ ኦሮምኛ (33.8%)፣ አማርኛ (29.3 %)፣ ሶማሌኛ (6.2%)፣ ትግሪኛ (5.9%)፣ ሲዳሚኛ ( 4%)፣ ወላይትኛ (2.2%) እና ጉራጌኛ ( 2%) ናቸው። 2% የሚለውን መመዘኛ ወደ 1% ብናወርደው ደግሞ አፍርኛ (1.7%)፣ ሃዲዪኛ (1.7%) ፣ ጋምኛ (1.5%)፣ጌዴኦኛ (1.3%)፣ ሽታኛ ወይም የስልጤዎች ቋንቋ (1.2%) እና ከፋኛ (1.1%) ይጨመራሉ። መስፈርቱን ወደ 5% ካወጣነው አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛና ሶማሌኛ ብቻ ይቀራሉ። መስፈርቱ ወደ 10% ካደገ አማርኛና ኦሮምኛ ብቻ ይሆናሉ።

እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ፣ ቁጥር ከሆነ አንዱ መመዘኛው፣ “ስንት በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚናገረው ነው የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ የሚሆነው ?”፣ የሚለው መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶር በደሉ ዋቅጅራ በቅርቡ በመሩት አንድ ጥናታዊ የፓናል ውይይት ላይ፣ ዶ/ር በድሉ ኦሮምኛና አማርኛ የፌዴራል ቋንቋ ሆነው፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ታይቶ ሌሎች ይጨመራሉ የሚል አስተያየት አቅርበዋል። ይሄ አስተያየት ከአማርኛ ሌላ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ መጨመር ሊያስከትለው የሚችለውን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ሁኔታዎች በሂደት፣ “በኦሮምኛ ሞክረን እንየው” የሚል አስተያየት ነው። በኔ እይታ ይሄ “እንሞክረው” የሚለው ነገር ከጥቅሙ ጉዳቱ በጣም ያመዝናል ባይ ነኝ። በሙከራ ሳይሆን በሚገባ ተጠንቶ፣ ጉዳቱ ከጥቅሙ ተመዝኖ፣ ህዝብ ተወያይቶበት ፣ ይጠቅማል ከተባለ ፣ ኦሮምኛ ብቻ ሳይሆን በፍትሃዊነት ሌሎችን ቋንቋዎችን አካቶ መሄዱ ነው የሚያስፈልገው። እንጂ ምን አልባት ለጊዜው ባለተረኞች፣ የኦሮሞ ብሄረተኖች የበለጠ ድምጻቸውን ስላሰሙ፣ ኦሮምኛን በችኮላ ማስቀደም ትልቅ ስህተት ነው።

በደቡብ አፍሪካ አሥራ አንድ ቋንቋዎች የስራ ቋንቋ ቢሆኑም፣ የደቡብ አፍሪካ ህገ መንግስት የክፍለ ሃገራትና የማእከላዊ መንግስቱ ከኦፌሴል የስራ ቋንቋዎች ውስጥ ቢያንስ ሁለቱን መጠቀም እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ቋንቋዎቹ ሲመረጡ ሕገ መንግስቱ መስፈርቶችንም አስቀምጧል፡፡ እነርሱም፡

• ቋንቋው ምን ያህል ሰው ይጠቀመዋል (usage)?
• ቋንቋውን የስራ ቋንቋ ማድረግ ይቻላል ወይ (practicality)?
• ቋንቋዉን የስራ ቋንቋ ለማድረግ ምን ያህ ወጭ ያስፈለጋል?
• የአካባቢው ሁኔታ እንዴት ነው ? የህዝብ ፍላጎትና ለህዝብ አስፈላጊነቱ ምን ያህል ነው ?

የሚሉት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዙሉዎች በብዛት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች የመንግስት አገልግሎት በዙሉና በእንግሊዘኛ ይሰጣሉ። ዙሉ የማይናገሩ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች አገልግሎት በእንግሊዘኛ ያገኛሉ።

በደቡብ አፍሪካ በሁሉም ቦታዎች ቢያንስ ሁለት ቋንቋ የስራ ቋንቋ መሆን አለበት የሚለው፣ ሁሉም ጋር እንግሊዘኛ የማወቅ እድሉ ሰፊ ሰለሆነ፣ ሁለት ቋንቋ ማለቱ ችግር ላይፈጥር ይችላል። በኢትዮጵያ እንተግብር ቢባል ግን በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ፣ እንደ አዳማ ባሉ ሌሎች ከተሞችም፣  አብዛኛው ሕዝብ አማርኛ ነው የሚያውቀው። አብዛኛው የፌዴራል መስሪያ ቤቶችም ያሉት በአዲስ አበባ ነው። የአዲስ አበባና የአማራ ክልል መስተዳደር ሰራተኞች አብዛኞቹ አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው። ሁለት ቋንቋ የሚለው መስፍረት እነዚህን ማህበረሰባት የሚያገል ነው የሚሆነው።

የስራ ቋንቋ ሲባል በዋናነት አገልግሎት በመስጠት ላይ ያተኮረ ነው መሆን ያለበት። በአዲስ አበባ የሚኖረው ሕዝብ ከ 98% በላይ እንደ አፍ መፍቻ ወይንም እንደ ተደራቢ ቋንቋ አማርኛ ይናገራል። የከተማዋ መስተዳደር ሆነ በአዲስ አበባ ያሉ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ከአማርኛ በተጨማሪ ትግሪኛን ወይንም ኦሮምኛን መጠቀማቸው፣ “ቋንቋው ምን ያህል ሰው ይጠቀመዋል (usage)?” በሚለው መስፈርት ምንም ትርጉም አይሰጥም።

ሆኖም ግን ሆስፒታሎች፣ እንደ አገር ውስጥ ገቢ፣ መንገድ ትራንስፖርት፣ ፖስታ ቤት ቴሎኮሚኒኬሽ ..ያሉ መስሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚኖሩ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በተጠና መልኩ፣ እንዳስፈላጊነቱ፣ በኦሮምኛ አገልግሎት መስጠት መቻል ያለባቸው መሰለኝ። ለምሳሌ አንድ የኦሮሞ ገበሬ ሕክምና ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ በፈረስ ቢመጣ፣ ቋንቋ ባለማወቁ መቸገር የለበትም። በተለይም ከአዲስ አበባ ወደ ዳር ባሉ አካባቢዎች።

በቄሌም ወለጋ አብዛኛው ነዋሪ ከ97% በላይ ኦሮምኛ ተናጋሪ ነው። በአዲግራት ትግሪኛ ተናጋሪዎች፣ በደገሃቡር ደግሞ ሶማሌኛ ተናጋሪዎች። በነዚህ ከተሞች እንደ ፖስታ ቤት ባሉ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ኦሮምኛ፣ ትግሪኛና ሶማሌኛ የሚናገሩ ተቀጥረው መስራታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። አብዛኛው ህዝብ ኦሮምኛ ተናጋሪ ባለበት ኦሮምኛ የማይችል ሰራተኛ ምንድን ነው የሚያደርገው ?

እዚህ ጋር አንድ መረሳት የሌለበት ነገር አለ። “ኦሮምኛ የማይቻል ሰራተኛ ምንድን ነው የሚያደርገው ?” ስል በቄሌም ወለጋ እንጂ በኦሮሞ ክልል እንዳለ ማለቴ አይደለም። ለምሳሌ አዳማ/ናዝሬት ብትሄዱ አብዛኛው ሰው እዚያ አማርኛ ተናጋሪ ነው። በአዳማ ኦሮምኛን የስራ ቋንቋ ማድረግ ገንዘብ ማባከን ነው። “ቋንቋው ምን ያህል ሰው ይጠቀመዋል (usage)?” የሚለው መስፈርት የማያሟላ ነው። ለምን ተገልጋዩ ኦሮምኛ ተናጋሪ ያልሆነ ፣ አማርኛ ተናጋሪ የሆነ ነውና። ስለዚህ “የሚገለገለው ህዝብ ማን ነው ?”የሚለው ጥያቄ ተጠይቆ ነው እንደ አስፈላጊነቱ ቋንቋዎቹን የሚናገሩ ሰራተኞች ናቸው በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግስታት መቀጠር ያለባቸው።ሰለዚህ አንድ ቋንቋ የፌዴራል ቋንቋ ይሆናል ሲባል፣ ቋንቋዉን የሚናገሩ በብዛት በሌሉበት ቦታ በዚያ ቋንቋ የፌዴራል አገልግሎት ይሰጣል ማለት መሆን የለበትም።

በደቡብ አፍሪካ ሁሉም ኦፌሴል ቋንቋዎች እኩል ናቸው ቢባልም፣ የማእከላዊ መንግስቱ ዋና የስራ ቋንቋ እንግሊዘኛ ነው፡፡ ፓርላማውና አብዛኞቹ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚጠቀሙት በእንግሊዘኛ ነው፡፡ ያ ብቻ አይደለም በደቡብ አፍሪካ ዙሉዎች ከሾሳዎች፣ ቬንዳዎች ከሴሴቶዎች ጋር .…የሚግባቡት በእንግሊዘኛ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ቋንቋ የአፍ መፍጫ ቋንቋቸው የሆኑ ዜግች የሚግባቡት በአማርኛ ነው። አማርኛ የ”አማራዎች” የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የብሄረሰቦችም መግባቢያ ቋንቋ ነው። አንድ የፌዴራል መስተዳደር ከሌላ የፌዴራል መስተዳደር ጋር የሚነጋገረውና የሚግባባው በአማርኛ ነው። ከስድስት ወራት በፊት የሶማሌና የኦሮሞ ሕዝቦች ግንኙነት ተብሎ ስብሰባዎች ሲደረጉ፣ ይነጋገሩ የነበሩት በአማርኛ ነበር። አማርኛ የሁላችንም ቋንቋ ነው።

ተጨማሪ የስራ ቋንቋ ይጨመር ሲባል አማርኛ መተካት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። በደቡብ አፍሪካ አንድ ዙሉ እንግሊዘኛ ማወቁ አስፈላጊ እንደሆነ በኢትዮጵያም በአለም አቀፍ ደረጃ እንግሊዘኛ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ አማርኛ ማወቁ አስፈላጊ ነው።