10 ዲሴምበር 2019

ከአስተዳደር እና ማንነት ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት እንደሚያደርግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።
ከሠላም እና ደኅንነት፤ ወቅታዊ የግብርና ተግባር እና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው እንዳሉት “የአማራ ህዝብ ከወሰን እና ማንነት ጋር ተያይዞ ጥያቄዎችን ያነሳው ዛሬ ብቻ አይደለም። ለዘመናት የነበሩ ጥያቄዎች ናቸው። የክልሉ መንግሥትም ጥያቄዎች ናቸው” ብለዋል።
• ከ20 ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
• “አሸባሪዎችና ጽንፈኞች በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ መሰረት ለመጣል እየጣሩ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
• የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኖቤል ሽልማትን በመቃወም ኤርትራውያን በኦስሎ ሰልፍ ወጡ
በዚህም የክልሉ መንግሥት ከአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ጋር በመሆን በእውነት ላይ ተመስርቶ የሕብረተሰቡን ጥያቄ እስከ መጨረሻው ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
“ክልሉ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለባቸው የሚል ጽኑ እምነት አለው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ጥያቄዎቹን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ተሳትፎ ያደርጋል ብለዋል።
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት ደግሞ ውይይቶች እና እርቆች መካሄዳቸውን በመጠቆም የሠላምና ደኅንነት ሥራው ባለፉት ጊዜያት በተሻለ ሁኔታ ክልሉን ሠላማዊ ለማድረግ የተሻሉ ሥራዎች ተከናውነዋል።
130 የቅማንት የማንነት ኮሚቴ አባላት የተደረገላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው መግባታቸውን በመግለፅ፤ በአካባቢዎቹ እንቅስቃሴዎች በተለመደው ሠላም እንዲቀጥሉ በመደበኛነት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
በክልሉ በሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተማሪዎች በሠላማዊ መንገድ እንዲማሩ ጥረቶች እየተካሄዱ መሆኑን አቶ ጌትነት ጠቁመው “ሊማሩ የሚመጡ ልጆች ወደ ክልሉ ከመጡ በኋላ የራሳችን ልጆች ናቸው። ተማሪዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሁሉም ሊያወግዘው ይገባልም” ብለዋል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልለዊ መንግሥት የሚማሩ የክልሉ ተማሪዎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል።
የአንበጣ መንጋ እና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የተቀናጀ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑንም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።