ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ተቀበሉ
10 ዲሴምበር 2019

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኖርዌይ ኦስሎ ተገኝተው የኖቤል ሽልማታቸውን ተቀበሉ።
የኖቤል የሰላም ኮሚቴ ሊቀመንበር ቤሪት ሬይሳ አንደርሰን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ባስመዘገቧቸው ሦስት ዋና ዋና ውጤቶች የ2019 የኖቤል ሰላም ተሸላሚ እንዲሆኑ መመረጣቸውን አስታውቀዋል።
እነዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በተለይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀውን ውዝግብ በሰላም ለመፍታት ባሳዩት ተነሳሽነት፣ በኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ግንባታ ለተጫወቱት ሚና እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሰላምና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋፅኦ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሊቀመንበሯ በንግግራቸው፤ “እንደ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነትዎ በአገር ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጡ ነው፤ የክልል እና የብሔር ክፍፍል ወደ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ሰዎች በራሳቸው ሃገር ቤት አልባ ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው። የኢኮኖሚ ቀውስ ፣ ሥራ አጥነት ፣ ትምህርት እና ጤና ላይም መሰራት አለባቸው” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ እንደተናገሩት፣ የኖሮዌይ ኖቤል ኮሚቴ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማስፈን የወሰዱትን እርምጃ ከግምት በማስገባት ሽልማቱን ስላበረከተላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ሽልማታቸውን በኢትዮጵያ ሕዝብና በፕሬዝዳንት ኢሳያስ ስም በተለይ ደግሞ ሰላምን ለማምጣት የማይተካ ዋጋ በከፈሉ ግለሰቦች ስም እንደሚቀበሉ ገልጸዋል።
• የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኖቤል ሽልማትን በመቃወም ኤርትራውያን በኦስሎ ሰልፍ ወጡ
ዛሬ ከፊት ለፊታችሁ ቆሜ ስለ ሰላም ለማውራት የቻልኩት በእድል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ ኤርትራ ጦር ከፊት ተሰልፈው የጦርነትን አስከፊነት ማየታቸውን ገልጸዋል።
ባድመ የሬዲዮ ኦፕሬተር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩበት ጦር፣ ለጥቂት ዞር ብለው ሲመለሱ በደረሰበት ጥቃት አባላቱ ሙሉ በሙሉ መሞታቸውን ጠቅሰዋል።
ጦርነት ለክፉዎች፣ ለልበ ደንዳኖችና ለጨካኞች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዛን ዕለት በጦርነት አውደ ግንባር ያጧቸውን ጓደኞቻቸውም ዛሬም ድረስ እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል።
100 ሺህ ወታደሮችና ንጹኀን ሕይወታቸውን በዚህ ጦርነት አጥተዋል በማለትም በኢትዮጵያም በኤርትራም ወገን ያደረሰውን ቀውስ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ኤርትራ ለሁለት አስርታት ያለ ሰላምም ያለጦርነትም በቆዮበት ዓመታት ቤተሰቦች ተቆራርጠው መቅረታቸውን ገልጸዋል።
ከ18 ወር በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑበት ወቅት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማምጣት እንደሚችል ጠንካራ እምነት እንደነበራቸው ገልጸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስም ይህ እምነት እንደነበራቸው ገልጸዋል።
• ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ
ዛሬ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተለያዩ ቤተሰቦች ተገናኝተዋል፣ የአየርና የስልክ ግንኙነት እንዲሁም ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ተጀምሯል በማለት ለሰላም ያላቸው ቁርጠኝነት ብርቱ እንደሆነ ገልፀዋል።
የሰላም ያላቸው ግንዛቤ በመደመር እሳቤ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
የዓለም ኃያላን ሀገራት በቀጠናው ወታደራዊ ኃይላቸውን ለማስፈር አሸባሪዎችና ጽንፈኛ ኃይሎች ደግሞ በቀጠናው ጠንካራ መሰረት ለመጣል እየጣሩ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀጠናው የኃያላን ሀገራት ጦርነት ሜዳ እንዲሆን የሽብር ነጋዴዎችና ደላሎችም መደበቂያ እንዲሆን እንደማይፈልጉ ቁርጠኝነታቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም እንደ አለም ዜጋ አባልነታችን ሰላም ላይ ሀብታችንን ማፍሰስ አለብን ብለዋል።