ሁሌ እናስታውሳቸው
ተቀብሮ እንዳይቀር
አኩሪ ታሪካቸው!!!!!!!
ስለሺ ዘውዴ (ጥበበ) ማን ነው???

ማሳሰብያ፤…..ከዛሬ 2 አመት በፊት ስለ ስለሺ ዘውዴና ሌላው
ስለተሰዋው ታናሽ ወንድሙ አበራ ዘውዴ አጭር ታሪክ በዚሁ ድረ-ገፅ ላይ ፅፌ ነበር። አሁን ስለ ስለሺ በመጠኑም የተሟላ በከተማና በሠራዊቱ ውስጥ የነበረውን አኩሪ የትግል ታሪክ በማግኝቴ በደስታና እኔም በኩራት ለንባብ አቅርቤላችኋለሁ።
ሌላው ያልተዘመረለት ጀግና!!! የኢሕአፓ አብሪ ኮከብ !!!!!
በአብሮ አደጉ ጓደኛውና የትግል ጓዱ ወንድሙ ነጋ ( በከር) እንደተናገረው፤……..
“ስለሺ ዘውዴ ከልጅነቱ ጀምሮ እንደ ትልቅ ሰው የሚያስብ ረጋ ያለ አስተዋይና ሩህ ሩህ ልጅ ነበር። ለድሃ፤ ለተበደለው ሰው አዛኝና ተቆርቋሪ፤ ታላላቆቹንም ታናሾቹንም አክባሪ ፍፁም ሰብአዊነት የተላበሰ ወጣት ነበር። በዚህም ምክንያት ከጓደኞቹ ጀምሮ በአካባቢው የሚያውቀው ሰው ሁሉ፤ የሰፈሩም ሆነ በአጠቃላይ የተመለከተው የድሬ ዳዋ ነዋሪ ሁሉ የሚወደውና የሚመርቀው ልጅ ነበር ብል ጨርሶ ማጋነን አይሆንብኝም።
ከኔም ጋር ገና ከልጅነት በት/ቤት (ከ 7ኛ ክፍል ጀምረን) ፤ በኳስ ደግሞ የህፃናት የኳስ ቡድኖች በወቅቱ ከነበሩት፤ እሱ በነበርዋን ልጆች የኦሞ ቡድን እኔ ደግሞ በገንደቆው የሸዋ በር ቡድን ስንጫወት በቅርብ እንተዋወቃለን። በኋላም እሱ በኳሱ ኮከብ በነበረበትም ጊዜ እንኳን ብዙም ሳንለያይ፤ ዩኒቨርሲቲ ከገባን በኋላ ደግሞ በደንብ እንቀራረብና እንወያይ እንዋደድም ነበር።
በ 1966 ዓ.ም በ ት/ቤት የተማሪ እንቅስቃሴ ስናደርግና ስንታሰርም፤ ስንፈታም አብረን ተደጋግፈን እንደወንድማማቾች ሆነን እንታይ የነበርን ነን። በኋላም የ አፄ ኅ/ሥላሴ መንግስት ከወደቀ በኋል በመስከረም 2/ 1967 ዓ. ም የወታደራዊ መንግስት ሲመሰረት በድሬ ዳዋ አካባቢ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በራሳችን አነሳሽነት በማድረግ፤ “ህዝባዊ መንግስት” በህዝብ የተመረጠና ” ለህዝብ የቆመ መንግስት” ያስፈልጋል በሚል ወረቀትን እያዘጋጀን እሱ በነበርዋንና በኮተኒ ፋብሪካ ( የኮተኒ ፋብሪካ ኳስ ተጫዋች ስለነበር) ወጣቶችን በማስተባበር ወረቀት እያስያዘ ሲበትንና ሲያስበትን፤ ወጣቱንና ሰራተኛውን ለትግል ሲያደራጅና ሲመራ የቆየበት ሁኔታ ነበር።
በኋላም ኢሕአፓ በድሬዳዋ አካባቢ መጀመርያ ሲመሰረት አብረውን ከመሰረቱት ጥቂት ወጣቶች አንዱ ስለሺ ነበር። ኢሕአፓ በአዋጅ እ 1967 ነሃሴ 26 ቀን በምስጢር ይፋ ሲወጣ ከነሃሴ 25 ማታ እስከ ነጋቱ ነሃሴ 26/ 1967 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በየቦታው ጥቂት የምንተማመን ልጆች ብቻ ተበታትነን ድሬ ዳዋን ስንቀባትና በወረቀት፤ በመፈክር ስናጥለቀልቃት ስናድር ስለሺ ነምበርዋንን፤ አፍተኢሳን፤ ለገሃሬንና “ኮተኒ” ፋብሪካን ምንም ነገር ሳይታወቅ ከሚመራቸው ጥቂት ወጣት ታጋዮች ጋር ሲቀባና ሲያሸበርቅ፤ በያንዳንዱ የሰራተኛ ማመላለሻ መኪና አርማ፤ መፈክርና ፅሁፍ ሲበትንና ሲለጥፍ ነበር። በኋላ ግን እኛ ስንጠረጠር ስለሺን ግን መጠርጠር ቀርቶ በግምት ያስገባውም ሰው አልነበረም። ሁሉም በኳስ ኮከብ ተጫዋችና በወቅቱ የብሄራዊ ቡድንና ወጣት ተመራጭ (8 ቁጥር ቦታ ) ስለነበርና በጣም ጠንካራ ሥነ-ሥርአት ( discipline )የነበረው በመሆኑ የገመተው ሰው/የመንግስት ሰላይ አልነበረም። ይህን የምጠቅሰው ምንም እንኳን በግሉ በኮኮብ ተጫዋችነቱ የትም መድረስ በኑሮውም ከፍተኛ ደረጃ ላይ መውጣት የሚችል ቢሆንም ለሃገሩ መሻሻልና ለህዝቡ ነፃነት ከፍተኛ ስሜት ስለነበረው ከመታገል፤ በቆራጥነት በህይወቱ ሊመጣ የሚችል አደጋን ከመቋቋም ለአንድ አፍታም ወደኋላ ያላለ ነበር።
ከዚያም ከ 1967 እስከ 1969 አጋማሽ በድሬዳዋና በሓረርጌ ክፍለ ሃገር በኢሕአፓ አባልነት በሰራተኛውና በወጣቱ ውስጥ፤ “ህዝባዊ መንግስት” ለመመስረት በሚል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ከመቆየቱም በላይ መጀመርያ በድሬዳዋ አውራጃ (regional) የፓርቲ ኮሚቴ አባል በመሆን በድሬ ዳዋና አካባቢው የነበረውን የተቃውሞ ትግል በመሪነት ያፋፋመና ያንቀሳቀሰ ከመሆኑም በላይ ተደጋጋሚ አስጊ ሁኔታዎችን በጀግንነት ያለፈና የተወጣ ነበር።
በኋላም ከ 1968 አጋማሽ እስከ 1969 አጋማሽ በድሬ ዳዋና በሃረር ከተማ በመመላለስ በአጠቃላይ የ ክ/ሃገሩን እንቅስቃሴ በ ኢሕአፓ አመራር ኮሚቴ አባልነት ( Zonal Committee)) የመራና በቆራጥነት ታግሎ ያታገለ ጓድ ነበር።
በዚህ ወቅት በድሬ ዳዋና ሓረር ከተሞች የደርግ ፀር-ህዝብ ጭፍጨፋ በወጣቶች በተለይም በዩኒቨርሲቲና በሁለተኛ ደረጃ ወጣት ተማሪዎች ላይ ከማተኮሩም በላይ የመንግስት “የህዝብ ድርጅት” ጽ/ ቤቶች በከሃዲዎችና በጥቂት አድርባይ ምሁራን የሚመሩ የመንግስት ገዳይ ቡድኖች ከፍተኝ ጭፍጨፋና ግድያዎችን ያፋፋሙበት ወቅት ነበር።
ምንም እንኳን እኔ ትንሽ ቀደም ብዬ በሰኔ / 1968 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሜዳ ” አሲምባ” ሲባል ወደ ነበረው ጉዞ የጀመርኩ ቢሆንም ሁኒታዎችን ግን በነበረኝ ቅርበት ስከታተል ነበርና፤ ዋና ዋናዎቹን አሁንም አልዘነጋም። በዚህን ግዜ አንድ ስለሺ የሚደነቅበትና እኛ እሱን በከተማ የትግል ሁኔታ የምናስታውሰው ቢኖር፤ ቆራጥነቱና የአላማ ፅናቱ ብቻ ሳይሆን በጣም አስቸጋሪ በሆኑና በተጣበቡ ሁኔታዎች ተልእኮውን ለመፈፀም ይፈጥራቸው የነበሩ አስደናቂ ጠላትን የማሳሳትና የመሸወድ ችሎታዎቹ ናቸው።
አንዷን እንኳን የማስታውሰውን ለመጥቀስ፤..በመጋላና በነበርዋን አካባቢ የሚታወቁ ልጆችን በሚያሳድዱበት ወቅት እዚያ አካባቢ የነበሩትን አንዳንድ የሚስጥር ሰነዶችን (documents) ለማዳንና ለማውጣት የግድ ያስቀመጥዋቸው ጓዶች መሄድ በነበረባቸው ወቅት፤ እሱ እየተፈለገና እያሳደዱት በጠላት አሰሳና ትርምስ መሃል ምንም ሳይደናገጥ ቆራጣ ቁምጣ፤ የተቀዳደደ ሸሚዝና ኮፍያ አድርጎ ፤ ከሰል ቸርቻሪ መስሎ የሚፈለገውንና ተልእኮው የሚጠይቀውን ፈፅሞ፤ ካሁን አሁን ተበላ ተብሎ ወገን ሲጨነቅ፤ ማምሻ ላይ የማይለየውን የሱ ምልክት የሆነውን ፈገግታውን እያሳየን ብቅ ያለበት ወቅት አሁንም አይረሳኝም። እንደ ፊልም ሁኔታው ሁሉ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል።
ስለሺን በጣም ልዩ ከሚያደርጉት ባህሪዎቹ መሃልና የማይረሳኝ ፤ ሰው በጣም ባዘነበትና በተበሳጨበት ወቅት ለማፅናናትና ብርታት ለመስጠት በቀላሉ የሚፈጥራቸው ቀልዶችና ብልሃቶች በአንዴ ያጋጠመንን ሁሉ ዘንግተን እንድንስቅና እንድንዝናና የሚያደርገው ብልሃትና ጥረቱ ነው። ከራሱ ስሜት ይልቅ ለሌላው እንደሚጨነቅ ለማወቅ የሚያስቸግር አልነበረም።
ተጠቁሞበትም በመፈለግ ላይ ሳለ ኮተኒ ፋብሪካ ሄደው ሊይዙት ሲሉ አምልጧቸው በድርጅቱ ትእዛዝ ወደ አሲንባ ያቀናል። ስለሺ ዘውዴ በ1969 መጋቢት መጀመርያ አካባቢ አሲምባ ደረሰ። እንደ አጋጣሚ በአካባቢው ( ማለትም ሰንገደ ተብሎ ይጠራ የነበረው የሰራዊቱ የአሲምባ አካባቢ ማሰልጠኛ ሲደርስ) እኔም ለስራ ከሌላ ቦታ ተንቀሳቅሼ ስለነበር ተገናኘን።
መጀመርያ ስንተያይ ሁለታችንም ደንግጠን ፈዘን ቀረን።ወድያው ደግሞ ተቃቅፈን ለምን እንደሆነ እንኳን በኋላም ባላውቅነው ምክንያት ተላቀስን። ምንም ሳንነጋገር እየሳቅን አለቀስን። ባካባቢው የነበሩት ሁሉ እንዴት እንደገረማቸው እስካሁን ትዝ ይለኛል። ቀስ በቀስም ማውራት ጀመርን። “የታናሽ ወንድሜን እሬሳ እኮ ተራምጀው! እየተቃተልኩ መጣሁ” አለኝ። ታናሽ ወንድሙ አበራ ዘውዴ በድሬዳዋ ውስጥ ሌላው የደርግ ሰለባ የሆነ ወጣት ነው። ይበልጥ አለቀስን። ሌላም ሌላም አወራን። ይህ ሁኔታ እስከመቸውም አይረሳኝም። ሌላው ቀርቶ ተቀምጠንበት የነበረው የዛፍ ሥር ጥላ አሁንም ትዝ ይለኛል።
ሌላው ሰው ግን የገረመው እንደሌሎቹ አብረውት የመጡ አዲስ የከተማ ልጆች እግሩ ሳይላላጥ፤ ብዙ ሳይደክመውና በየመንገዱ ልረፍ እያለ ሳያስቸግር እንዲያውም ሌሎችን ከአጀቧቸው ነባር ታጋዮች ጋር ሆኖ የደከሙትን እየደገፈና አብሮ እየተሸከመ አሲምባ በመድረሱ ነው።
ማንነቱን ከኔ በቀር በቅርብ የሚያውቀው ማንም አልነበረምና በጣም ኮራሁ። ልክ የናቴ ልጅ ከጎኔ መጥቶ እንደቆመ ተሰማኝ። እሱም እንደዚያ ነበር የተስማው።
ሠራዊቱ ውስጥ በገባ በሶስተኛው ወር አስፈላጊውን ስልጠናና ልምምድ፤ የሽምቅ ተዋጊ አኗኗርና ዝግጅቱን አጠናቆ በተዋጊ ሃይል ውስጥ ታጥቆ ተመደበ። ወሩም ግንቦት/ 1969 ዓ.ም ነበር። የተመደበበት ሃይል ( ማለትም በመደበኛ ጦር ትርጉም የሻንበል ጦር ወይም company መሆኑ ነው)። የሃይሏም ስም ሃይል 5 ትባል ነበር።
ይህች የተጠናከረች የሽምቅ ተዋጊ ሃይል ከሌሎች በወቅቱ ከነበሩ ሃይሎችና አሃዶች ጋር በምስራቅ፤ በመሃል በምእራብና ደቡብ ትግራይ አውራጃዎች ውግያዎችንና የመስፋፋት እንቅስቃሴን አድርገው፤ የእነ ስለሺዋ ሃይል ወደ ጎንደር ክ/ሃገር ስሜን አውራጃ ጠለምት ይባል በነበረው ወረዳ ይንቀሳቀስ ወደነበረው የኢሕአሠ ክፍል ተከዜ ወንዝን ተሻግራ ትንቀሳቀሳለች። እዚያ አካባቢ በሰኔ መጀመርያ 1969 ዓ.ም በመድረስ አብራ ተንቀሳቅሳ ከደርግ ሃይሎች ጋር ትዋጋ ጀመር። ከግንቦት 1969 –እስከ ህዳር መጀመርያ 1970 ዓ.ም ከኔ ጋር የተለያየን ቢሆንም በህዳር 1970 ዓ.ም እኔ የነበርኩበት ሃይልም ወደ ጎንደር በመዛወሩ ከስለሺ ጋር እንደገና ተገናኘን።
በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ ስለሺ በነበረበት የሽምቅ ተዋጊ ሃይል አባላት ዘንድ በሁሉም መስክ ተወዳጅነትንና ተደናቂነትን ከከፍተኛ አክብሮት ጋር የተጎናፀፈ ታጋይ ነበር። በዚሁ ወቅት ጥቅምት/1970 በጠለምት ወረዳ ውስጥ ማይለሃም በሚባል ጠመዝማዛ ( እንደ ደንገጎ አይነት የመኪና መንገድ) ጎዳና ላይ የእነ ስለሺ ሃይል ያለበት የኢሕአሠ ከፍተኛ ሃይል ደፈጣ አድርጎ 22 የጦር መኪናዎችንና አብረው የነበሩት ነበልባል ይባል የነበረውን ጦር ክፍሎችን ደምስሰው በርካታ ከባድና ቀላል የጦር መሳርያና ወታደሮችን ከነአዛዡ ሻለቃ ጌታቸው ዮሴፍና ከነረዳት መኮንኖች የማረኩበት ሁኔታ ነበር። ስለሺ በዚህ ታላቅ የወቅቱ ወታደራዊ ድል የተሳተፈና በጀግንነት የተዋጋና ያዋጋ ታጋይ ነበር።
ከዚያም በኋላ ለተማረኩት ወታደሮች ስለ አላማችን በማስተማርና በመቀስቀስ ሥራ ላይ በደንብ የተሳተፈ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ባገኘው ተወዳጅነትና ክብር የሃይሏ የፖሊቲካ ኮሚቴ ( በወቅቱ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ በዚያ ምድብ ውስጥ የነበረ ነበር)አባል ሆኖ በግንባር ቀደም ታጋዮችን ያስተምርና ያታግል የነበረ ነበር።
ከታህሣሥ/ 1970 ዓ.ም እስከ 1971 መጀመርያ ድረስ በዚሁ በሰሜን አውራጃ ( ጎደር ክ/ሃገር) በጃናሞራ፤ በበየዳ፤ በበለሳና በወልቃይት አካባቢዎች ከጠላት ጋር በመዋጋትና አካባቢዎችን ነፃ በማውጣት እንዲሁም በነዚህ ክፍሎች ያሉትን ገበሬዎች በማስተማርና በማስተባበር በሃላፊነት ድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል።
ከ1971 መጀመርያ ጀምሮ እስከ የካቲት/1971 ድረስ ደርግ የሌለ ያለ ሃይሉን አግበስብሶ ነፃ ባወጣነው ክፍሎች ላይ መጠነ ሰፊ የከቦ ማጥፋት ዘመቻ ሲያውጅብንና ሲዘምት፤ ተከታታይና ከባድ ውግያዎችን በማድረግ በአነስተኛ ሃይል በየተራራውና ገደሉ፤ በጫካና ጉድጓዱ ጠላት ላይ አደጋ በመጣልና፤ ጥቃቱንም ከህዝብ ጎን ሆኖ በመከላልከል፤ ዘመቻውን ለማክሸፍና ጠላትን አሳፍሮ ለመመለስ ከፍተኛ ግድያና ተጋድሎ ካደረጉትና ከተጋፈጡት ጀግኖች አንዱ ስለሺ ነበር።
በነገራችን ላይ ስለሺ ሰራዊቱን ከተቀላቀለበት ቀን ጀምሮ በቤተሰቦቹና በዘመዶቹ ላይ የበቀል እርምጃ እንዳይወሰድ ሁሉም ታጋይ እንደሚያደርገው ሁሉ ማንነቱን ላለማሳወቅ ስሙን ቀይሮ ነበር። ስለሆነም በሰራዊቱ ውስጥ በወቅቱ የሚታወቅበት ስለሺ ሳይሆን “ጥበበ” በመባል ነበር።
ከ የካቲት/1971 በኋላ በተከታታይ በጠላት ላይ የተለያዩ ወረራዎችንና ጥቃቶችን በመሰንዘር፤ በቀይ ሽብር ከጎንደርና ከሌላም ከተሞች እየተባረሩ የሚመጡትን ወጣት ታጋዮች ለማደራጀት ለማስታጠቅና ሰራዊቱን ለማጠናከር ከፍተኛ ተጋድሎ ይደረግ የነበረበት ወቅት በመሆኑ በየአካባቢው ያሉ የኢሕአሠ ሃይሎች ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር።
እኔና ስለሺ( ጥበበ) በነበርንበት በጠለምትና፤ በበለሳ እንዲሁም በወቃይት አካባቢዎች የተሰለፍንባቸው ሃይሎች በዚሁ ክልል ባሉ የጠላት የጦር ሰፈሮችና ኮንቮዮች ላይ አደጋ እየጣልን ከፍተኛ የሆኑ ድሎችን ያስቆጠርንበት ወቅት ነበር።
በኋላም የተለያዩ ራቅ ራቅ ብለው በሚገኙ ጥልሎች ቀጠና ተሰጥቷቸው ይንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ሃይሎችን በአንድ እዝ ስር በማስተባበርና በማሰለፍ አንድ የተጠናከረና ቁልፍ ቦታን፤ ነፃ በወጣው የጠለምትና የወልቃይት ክልል መሃል የሰፈረን የጠላት ጦር ለመደምሰስና ከአካባቢው ለማባረር ተወሰነ።
ቦታው፤.. ማይፀብሪ ተብላ የምትጠራው ትንሽ የወረዳ ከተማ ዙርያ ባሉ ኮሮብታዎች ላይ የተሰራ የጠላት የጦር ሰፈር ወይም ምሽግ ነበር።
ማይፀብሪ የምትባለዋ ከተማ ከደባርቅ ( የሰሜን አውራጃ ከተማ) ወደ ትግራይ የተከዜን ድልድይ ተሻግሮ የሚሄደው ዋና ጎድና ላይ የምትገኝ ስትራቴጂያዊ ቦታ ናት። ይህንን ቦታ መቆጣተር ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጥቅምን ያስገኛልተብሎ የሚገመት ወሳኝና ቁልፍ እርምጃ ነበር።
አስፈላጊው የመረጃ ማሰባሰብና ቅድመ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ጠላት ሳይሰማ በርካታ ሃይሎችን በአጭር ግዜ በማሰባሰብ የህዝቡን ድጋፍ በመጠቀም፤.… ሚያዝያ 25/1971 ዓ.ም ከሌሊቱ 6 ሰአት ( እኩለ ሌሊት ላይ) የጦር ሰፈሩን በመውረር የጠላት ወደ 2 ሻለቃ የሚገመት መደበኛ ጦርና የከባድ የአየር መቃወምያ ምድብ ሃይል የተጠናከረውን፤ ጨካኙ ሻለቃ መኮንን የሚመራውን የጠላት ጦር ለመደምሰስ ዥግጅቱ ተጠናቀቀ። ይህን ጦር ለመደምሰስ ከፍተኛ መስዋእትነትን ለመክፈልም በኢሕአሠ ሃይሎች፤ መሪዎችና ተዋጊዎች ከፍተኛ ፍላጎትና ስሜትነበር።
ስለሺና እኔ የምንመራው/ የነበርንባቸው ዋና አጥቂ ምድቦች፤ ላይ-ቡርቃቂያ ከሚባል ቦታ አጠገብ ካለ ኮረብታ ላይ ማምሻው ላይ ተሰባስበን፤ እረፍት አድርገን ከዋልን በኋላ፤ ሰአቱ ሲደርስ በማታ ወደ የ 3 ሰአት ጉዞ ርቀት ላይ ወደሚገኘው ከላይ ወደ ጠቀስኩት የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር፤ ለጉዞ ከምሽቱ 1 ሰአት ማታ ተዘጋጀን።
” በናንተው የትግል ደም”፤” በናንተው ውጋገን” የሚባለውን የወደቁን ጓዶችን የምናስታውስበትንና ወኔ የምንቀሰቅስበትን መዝሙር ደመቅ አድርገን ዘመርን። በተራ ሰልፍ በከፍተኛ ንቃትና ፀጥታ ጉዞ ጀመርን። በዚያን ወቅት ለምን እንደሆነ ባላውቀውም እኔና ስለሺ በልዩ ሁኔታ እየተያየንና እየተጠቃቀስን አብረን ሊገለፅ በማይችል ስሜትና ሲቃ ጉዞ ጀመርን።
ስለሺ በዚያን ወቅት የይዘው ክላሽን መሳርያ ባለሁለት መጨበጫውን ሲሆን፤ የለበሰው ልብስ ከላይ ካኪ ሸሚዝና ቡና አይነት “ተነፋነፍ/ተፈሪ ቅድ” ሱሪ ነበር። እኔና እሱ በሷ ሱሪ ብቻ ብዙ ግዜ ስቀናል። ስለሺ ሰው ማዝናናትና ማሳቅ ስለሚወድ ሆነ ብሎ የመረጣት ነበረች። እርግጥ ልብስ ሲታደልም “መጀመርያ ለጦሩ” ስለሚል፤ የቀረውን ተመርጦ የተረፈውን ነው የሚለብሰውና አይገርመኝም ነበር። ብቻ ይህ ሁኔታ በምንም አይነት ከህሊናዬ አይጠፋም፤ አሁንም እንደበፊቱ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል።
ከ 3 ሰአት ጉዞ በኋላ ጠላት ሳይሰማ ከቦታው ደርሰን ከበባ አደረግን። እኔና ስለሺ የነበርንበት ዋናው አጥቂና መቺ ሃይል በመሆኑ ቁልፍ ወደሆነውና ወደ ዋናው የጦር ምሽግ በሰአቱ ደርሰን መጠጋት ጀመርን። ጉዟችንን ያጀበችው የምሽት ጨረቃም ልክ ከምሽጉ ስንደርስ ጠፋች። ዝናብም ካፍያ ጀመረ። በጣም የተመቻቸ ሁኔታ ሆነ።
ሁሉን አጠናቀን ተኩስ ከፈትን። ድብልቅልቅ ያለ የጨበጣ ውግያ ተደርጎ ዋናውን ምሽግ ሰብረን ገብተን ጠላትን መበታተንና መምታት ቻልን። ሆኖም ከዋናው ምሽግ ገባ ብላ በምትገኝ ኮረብታ ቦታ ላይ የጠላይ ከባድ መሳርያና የአየር መቃወምያ ተኩስ ችግር ይፈጥርብን ጀመር። እዚያች ኮረብታ ላይ ያለው ትንሽ የቀረ ሃይል ቢሆንም የተኩስ ሃይሉ በነበሩት ከባድ መሳርያዎች የተጠናከረ ነበር። ስለዚህ በዚህን ጊዜ ሃይላችንን በግራና በቀኝ ቆረጣ በማስገባት፤ ያቺን ኮረብታ ለመያዝ ተንቀሳቀስን።
በዚህን ጊዜ ስለሺ ከጥቂት ምርጥ ጓዶች ጋር ጨበጣ በመግባት በቦምብና አዳፍኔ እየተረዳ በመግባት ቀድመው ጠላትን ደምስሰው ኮረብታውን በመቆጣጠር ፀጥ አደረጉት። በዚህ ወቅት ይህንን ድብልቅልቅ ያለ ውግያ እያደረግን እያለን ነበር ከኛ በኩል ጉዳቱ እየጨመረ የመጣው። ስለሺም በዚህ ወቅት ነበር ግቡን ከያዘ በኋላ መቁሰሉን የገለፀው። ቁስሉም የቀኝ እግሩ የውስጥ ጭኑን በከባድ መሳርያ ፍንጣሪ ተመቶ፤ አንገቱ ላይ ጠምጥሞት በነበረ “ከሹክ” የምንለው ( የአቡጀዲ ቁራጭ የመሳርያ መሸፈኛ፤ መሬት ስንተኛ ደግሞ አንጥፈን የምንተኛበት ጨርቅ ነው) እግሩን ጠምጥሞ “በለው!”፤ “በለው!” እያለ ሲዋጋና ሲያዋጋ ቆይቶ በኋላ ደም በብዛት እየፈሰሰው ሲመጣ ነው ሃኪም የጠራው። ጨለማም ስለነበር ማንም አላየለትም ነበር። ሁሉም ነገር በቁጥጥር ሥር ሁኔታም ስለነበር፤ እኔም ተጠርቼ ከምሽጉ እሱን ወጣ አድርገን ደሙን ለማቆም እየተሞከረ እያለ፤ እጄን ጨበጥ አድርጎ “አይዟችሁ በርቱ! ጠንክሩ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ድል ማድረጉ አይቀርም!” እያለ ፈገግታው ሳይለየው ደም ብዙ ስለፈሰሰው አረፈ።
ከሱ ጋር በዚህ ቀን 25 ታጋዮች ተሰውተዋል። 30 ያህል ቆስለዋል። ከጠላት ግን ከ250 በላይ ተገድለዋል የተወሰኑትም ተማርከዋል። ስለሺንና ጥቂት የተሰዉ ጓዶችን በዚያው አካባቢ ወጣና ራቅ አድርገን እንዲቀበሩ አድርገናል።
ጦሩም ተደመሰሰ፤ እጅግ በርካታ ጦር መሳርያ፤ ከባድና ቀላል ፈንጅዎችና ንብረት ማርክረን ድል አድርገናል። ይሁንና በጦርነት ውስጥ መግደልና መሞት አብረው የሚሄዱ በመሆናቸው ስለሺም ለሚያምንበት ዓላማ ለሚወዳት ሃገርና ህዝብ ተገቢ ነው ብሎ ባመነው ታሪክ ሰርቶ አልፏል።
ስለሺም ሆነ እኔ በጣም ያንገበግበንና ሁሌም ጠንክረን እንድንታገል ያደርገን የነበረው፤ በከተማም ሆነ በገጠር የወደቁት ወንድሞቻችን፤ ጓደኞቻችን ደምና የተፈፀመውና እየተፈፀመ የነበረው የግፍ ጭፍጨፋ፤ የፋሺስታዊው መንግስት ፀረ-ህዝብ አመፅ ነበር።
መቼም አሁን የተለያዩ በወቅቱ ያልነበሩና ቢኖሩም የተለያየ ግላዊ ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ የኖሩ ሰዎች፤ የተለየ ትርጉም ሊሰጡት ቢሞክሩም፤ በኛ በኩል ታሪካችን በዚያን ወቅትና ሁኔታ በውስጡ ያለፉትን ጀግኖችና የቆሙለትንና የወደቁለትን ህዝባዊ አላማና የሃገር ፍቅር ታሪክ፤ ማንም ሊያጨልመውና ሊያዳፍነው እንደማይችል፤ የኢትዮጵያ ህዝብና ታሪክ የሚመሰክረው እንደሚሆን አልጠራጥርም።”
ስለሺ ዘውዴ ከወያኔ ጋር እየተዋደቀ ላለው ወጣት ትውልድ አርአያና ምሳሌ ነው !!!!! ነፍስ ይማር!!!! በጣም እንኮራባታለን!!!!
አንድነት ሃይል ነው !!!
የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!
