SourceURL:https://www.bbc.com/amharic/news-50839154 – BBC News አማርኛ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 7 2012 ዓ.ም ባካሄደው ስድስተኛ መደበኛ ስበሰባው የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።
ከእነዚህ ረቂቅ አዋጆች መካከል ተሻሽሎ የቀረበው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ይገኝበታል።
በሥራ ላይ የሚገኘው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ያሉበትን ጉድለቶች መቅረፍ ያስችላል ተብሎ የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ፤ በሃገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጪ በሚገቡ የተመረጡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ታክስ ጥሏል።
ረቂቅ አዋጁ የኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው የለያቸው የምርቶች አይነት የሚከተሉት አይነት ናቸው።
- የቅንጦት የሚባሉ ምርቶች
- የማህብረሰቡን ጤና ሊጎዱ እና ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚባሉ ምርቶች እንዲሁም
- መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው የማይቀንስ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ ነው።
መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው አይቀንሱም የተባሉት የምርቶች አይነት፤ እቃዎቹ ኤክሳይዝ ታክስ ስለተጣለባቸው በተጠቃሚዎች ላይ ብዙም የዋጋ ልዩነት የማያመጡ፤ ነገር ግን ለመንግስት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ስለመሆናቸው ተነግሯል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው ከተለዩ ምርቶች መካከል የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው።
የምርቱ ዓይነት | የታክስ ምጣኔ (ጭማሪ) | ማብራሪያ |
---|---|---|
ምግብና መጠጥ | ||
ስብ እና ዘይት፡ የታክስ ጭማሪው መሠረት ያደረገው ለምግብነት የተዘጋጀው ዘይት በውስጡ የያዘው የሳቹሬትድ ስብ መጠንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። | በ100 ግራም ውስጥ ከ40 ግራም ወይም ከዛ በላይ ሳቹሬትድ ስብ፣ ለጤና ጎጂ የሆነ ቅባት ከያዘ የታክስ ምጣኔው ከ30-50% | ለምሳሌ በ100 ግራም ውስጥ 40 ግራም ሳቼሬትድ ስብ ኖሮት በ100 ብር ይሸጥ የነበረ 1 ሊትር ዘይት 140 ብር ይገባል ማለት ነው። |
ስኳር | ማንኛውም አይነት ስኳር 20% | ለምሳሌ 45 ይሸጥ የነበረው 1 ኪሎ ስኳር 52 ብር ይሆናል ማለት ነው። |
ዱቄት፣ ለስላሳ መጠጦች፣ አልኮል አልባ የታሸጉ መጠጦች | 15-30% | ይህ ከለስላሳ መጠጦች በተጨማሪ የታሸገ ውሃ እና ጋዝ ያላቸው የታሸጉ ውሃዎችን ይጨምራል፤ 12 ብር የሚሸጥ ለስላሳ 15 ብር ይገባል፤10 ብር የነበረ 1 ሊትር የታሸገ ውሃ 11.50 ብር ይሆናል። |
ቢራ | ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ በበቀለ ገብስ የተመረተ ቢራ 35% ወይም 9 ብር በአንድ ሊትር | 15 ብር የነበረው 19.50 ይሆናል። |
ወይን መጠጥ | ከ30-40% | ለወይን ምርት ግብዓት በሚሆነው ጥሬ እቃ መሠረት |
ሲጋራ | 30% | 20 ፍሬ የሚይዘውን እሽግ ሲገዙ ተጨማሪ 5 ብር ይከፍላሉ |
የመዋብያ ቁሳቁሶች | ||
ሸቶዎች፣ የቁንጅና እና መኳኳያ ምርቶች | 100%። ዋጋው በእጥፍ ይጨምራል ማለት ነው። | ሰን ስክሪን እና ሻምፖን አይጨምረም |
የሰው ጸጉር (ሂዩማን ሄር) እና ዊግ | 40% | ሂዩማን ሄር፣ ቅንድብ፣ የእንስሳት ጸጉር እና የመሳሰሉት |
ተሽከርካሪዎች | ||
ትራክተር ከ4-7 ዓመት ያገለገሉ | 100-400% | ብዙ ዓመት ያገለገሉ ከፍተኛ ታክስ ይጫንባቸዋል |
ከ16 ተጓዥ ያልበለጠ ተሳፋሪ የሚይዙ – የተለያየ ሞተር | 100-400% | ከ 4-7 ዓመት ያገለገሉ፣ የተለያዩ አይነት ሚኒባሶችን ይጨምራል |
የሲሊንደር ይዘት ከ1300 ሲሲ ያልበለጠ | 30%-430% | አዲስ በሆኑት ላይ 30%፣ ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ 430%ምሳሌ፡- 350ሺ ብር ገደማ ትሸጥ የነበረችው 2008 ሞዴል 1ቪ ሲሲ ቪትዝ- የአገልግሎት ዘመኑ ከ7 ዓመት በላይ ስለሚሆን ዋጋው 1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ሊሆን ይችላል። |
የሲሊንደር ይዘት ከ1300 ሲሲ የበለጠ | 60%-460% | አዲስ- ከውጪ የገቡ ወይም በሃገር ውስጥ በከፊልም ይሁን ሙሉ በሙሉ የተገጣጠሙ 60%፤ ከ2 ዓመት በታች ያገለገሉ- 110%፤ ከ2-4 ዓመት ያገለገሉ160%፤ ከ4-7 ዓመት ያገለገሉ 260%፤ ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ 460% |
የሲሊንደር ይዘት ከ1800 ሲሲ የበለጠ | 100%-500% | አዲስ- ከውጪ የገቡ ወይም በሃገር ውስጥ በከፊልም ይሁን ሙሉ በሙሉ የተገጣጠሙ 100%፤ ከ2 ዓመት በታች ያገለገሉ 150%፤ ከ2-4 ዓመት ያገለገሉ200%፤ ከ4-7 ዓመት ያገለገሉ 300%፤ ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ 500% |
ሌሎች | ||
የፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) | 40% | በአንድ ኪሎግራም ፌስታል ላይ |
የፎቶ/ቪዲዮ ካሜራ፣ ድምጽ መቅረጫ | 10% | ቴሌቪዥን እና የቴሌቪዥን ስርጭት መቀበያ መሣሪያዎችን ይጨምራል |
ሲጋራ | 30% |
ኤክሳይዝ ታክስ ለመንግሥት ከፍተኛ ገቢ ከማስገኘቱ በተጨማሪ፤ ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ሃገር ውስጥ የተመረቱትን ከገበያ ውጭ እንዳያደርጓቸው ታስቦ ይጣልባቸዋል። ይህም የሃገር ውስጥ አምራቾችን እንደሚያበረታታ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ኤክሳይዝ ታክስ በአምራቹ ወይም አስመጪው ይከፈላል። ምርቶች የተመረቱት በሃገር ውስጥ ከሆነ፤ ከተመረቱበት ወር ቀጥሎ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ እንዲሁም ምርቶቹ ከውጪ የሚገቡ ከሆነ አስመጪው ግለሰብ ወይም ድርጅቱ ከጉምሩክ ክልል በሚያወጣበት ጊዜ ታክሱ ይከፈላል፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ የሚጸድቅ ከሆነ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ 307/1995 ተሽሮ በዚህ አዋጅ ይተካል።
በተጨማሪም ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን ማንኛውም ሕግ፣ መመሪያ ወይም አሠራር ይህንን አዋጅ በሚመለከት ተፈፃሚነት አይኖረውም።