በዘ-ሐበሻ
- December 18, 20192
ኢንጂነር ይልቃል ለአገርና ለሕዝብ ብዙ ሊሰራ የሚችል ፖለቲከኛ ነው። ኢሃን የሚባል የፖለቲካ ድርጅት መሪ ነው። ኢሃን ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቅናቄ የሚል ነው። ኢሃን ምን ያህል አባላት እንዳሉት አላውቅም። እንደ ድርጅትም ስለሰራው ነገር የማውቀው ነገር የለኝም። ምን አልባት በአዲሱ የምርጫ ቦርድ ሕግ አንድ አገር አቀፍ ድርጅት 10 ሺህ ፊርማ ማሰባሰብ ስላለበት፣ ኢሃን ያንን መመዘኛ ላያሟላም ይችላል።
አብን ከተመሰረተ ጊዜ ጀመሮ በአገሪቷ ትልቅ ተጽኖ ፈጣሪ መሆን የቻለ አንጋፋ ድርጅት ነው። የዶ/ር አብይ አስተዳደር አብን ላይ ከፍተኛ ጫናና ግፍ እየፈጸመ እንደሆነም የሚታወቅ ነው። እንደ ክርስቲያን ታደለ ያሉ አንጋፋን የአብን አመራሮች አሁንም በመሰረተ ቢስ ክስ፣ በነ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ተከሰው በወህኒ እየማቀቁ ነው። አብን ከአማራ ክልል ውጭ በሌሎች ክልሎች መዋቅር ያለው ሲሆን፣ በተለይም በኦሮሞ ክልል በኦህዴድ ዘረኛ ሃላፊዎች ፣ “አብኖች ናችሁ” እየተባሉ ብዙዎች እንግልትና መከራ እየደረሰባቸው ነው።
አብን ራሱን የአማራ ድርጅት አድርጎ ቢቆጥርም፣ መጀመሪያ ኢትዮጵያ የሚል ድርጅት ነው። በአማራነት ስም ተደራጅቶ የመጣውም፣ ፈልጎ ሳይሆን ሁኔታዎች አስገድዶት፣ አማራ በሚባለው ማህበረሰብ ላይ ከፈትኛ ግፍ ስለተፈጸመ ራስን ለመከላከል መደራጀት ያስፈለጋል በሚል ነው።
ሆኖም አብን በአማራነት ብቻ ተደራጅቶ ብዙ ዘልቆ መሄድ የሚችል ነው ብዬ አልስብም። ይሄንን በግል ለአንዳንድ አመራሮቹ፣ በይፋ በተለያየ ጊዜ የገለጽኩት ነው። ከአማራ ክል ውጭ ተደራሽነቱ በጣም ውስን ነው የሚሆነው። ምን አልባት ከግማሽ በላይ የአዲስ አበባ ሕዝብ ራሱን አማራ ብሎ በመታወቂያ ላይ ያስዘመዘገ ስለሆነ፣ በአዲስ አበባ እድል ሊኖረን ይችላል ብለው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም ግን ግማሹ ሕዝብ አማራ ነው ቢባልም፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ማንነቴ ኢትዮጵያዊነት ነው የሚል ነው። የኢትዮጵያዊነትን ማንነት ተቋቁሙ፣ አብን በአዲስ አበባ ድምጽ ያገኛል ብሎ ማሰብ ትንሽ አስቸጋሪ ነው።
መኢአድ አንጋፋ ድርጅት ነው። ላይ ላዩ የደከመ ድርጅት ቢመስልም፣ በተለይም ወደ ገጠር ወረድ ሲባል ትልቅ ሕዝባዊ መሰረት ያለው ድርጅት ነው። በአማራና በደቡብ ክልል ከፍተኛ መዋቅር አለው። መኢአድ ድርጅታዊ ጥንካሬ መኢአድን በቅርበት ለምንከታተል እንግዳ ባይሆንብንም፣ ድርጅቱ ያለው ድርጅታዊ መረብ ተጠቅሞ ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀድሞ መሄድ አልቻለም። ትልቅ የሕዝብ ግንኙነት ችግሮች አሉበት። ስትራቴጂ ነድፎም፣ አማራጮችንም አቅርቦ መንቀሳቀስ አልቻለም።
እንግዲህ ከላይ እንደጠቀስኩት መኢአድ፣ አብን፣ ኢሃን ጥንካሬዎች ቢኖራቸውም ፣ የራሳቸው ድካምም አላቸው። በተናጥል መጓዛቸው ኃይላቸው እንዲበታተን የሚያደርግ ነው።
የነዚህ ድርጅት አመራሮች እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የምመክረው ነገር ቢኖር በአስችኳይ ተቀናጅተው በጋራ መስራት እንዲጀምሩ ነው። ተነጋግረው፣ በምርጫ ቦርድ ሕግ በቅንጅት እንደሚሰሩ አሳውቀው፣ ለምሳሌ ትብብር ለአንዲትና ዴሞክርሲያዊት ኢትዮጵያ በሚል (Alliance for One and Democratic Ethiopia) ስም በጋራ ለምርጫ መቅረብ ይችላሉ። ባልደራስ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ከተቀየረም ይሄንን ስብስብ ሊቀላቀልም የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
ያንን ካደረጉ በአማራ፣ በደቡብ፣ በአዲስ አበባ ፣ በአፋር ፣ በቢነሻንጉል፣ በኦሮሞ ክልል በዋናነት ሸዋ፣ በኢሊባቡር፣ በአርሲ …ከፍተኛ ተፎካካሪ መሆን ይችላሉ።
ስለተሸንፈውና እየሞተ ስላለው ሕወሃት በማውራት ጊዜ ማጥፋት አያስፈለግም። ብስት ማሰማት፣ ክሶችን ብቻ ማቅርብ፣ የአገዛዙ ኡፍትሃዊ አሰራሮች ማጋለጥ ብቻ እትም አያደርስም። በተናጥን መንቀሳቀስ የትም አያደርስም። የብልጽግና ፓርቲ መሪ ዶ/ር አብይ በግልጽ ቻሌንጅ አድርጓቸዋል። እኛ የምንሰራው ካልጣማችሁ የተሻለ አማራጭ ይዛቹህ ኑ ብሎ። እንግዲህ ለዶ/ር አብይ ተግባራዊ ምላሽ ይሰጡ ዘንድ፣ እንደ ፖለቲከኞች ስትራቲጂክ ሆነው፣ ዉጤት ላይ ያተኮረ ስራዎችን መስራት ይጀመሩ ዘንድ በአክብሮት አሳስባለሁ።