Dec.18,2019
ምስጋና
ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያ — ፍትህና ነጻነት የሚገኝባት ኢትዮጵያ— ዜጎቿ በየትኛውም የቆዳ ስፋቷ ተንቀሳቅሰው በነጻነትና በኩራት የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ለመፍጠር አንድ ነፍሱን የሰጠ ነበር ኢሕአፓ ውስጥ የነበረው ትውልድ። ከድህነት፣ከኋላ ቀርነትና ከማይምነት ሕዝብ ተላቆ እድገት ብልጽግናና ስልጣኔን ለማምጣት አልሞ የተነሳ ትውልድ፡፡ የኢሕአፓ ገድል ገና ታሪኩ አልተጻፈም። የሰማእታት ታሪክ በበቂ አልተጻፈም፡፡
በዚህም ምክንያት ከአምባገነኑ የደርግ መንግሥት የታሪክ ጠባሳ ጋር አበሮ የመወቀጥ እጣ ደርሶታል። አሁን ያለው ትውልድም ትክክለኛውን ታሪክ በአግባቡ ባለማግኘቱና የተጻፉትም ተገቢውን ያህል ባለመነበባቸው የኢሕአፓ ሰማዕት ታሪክ «ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ሆኗል። ሆኖም «እውነትና ንጋት እያደር ይገልጣል» እንዲሉ ጊዜ ይወስዳል እንጂ ትክክለኛው የወቅቱ ታሪክ መውጣቱ አይቀርም። ለዚህም እኛ በህይወት የምንገኝ ጓዶች ያለ አድልዎ እውነታው ለትውልድ ተጽፎ እንዲቀመጥ የቻልነውን ሁሉ የማድረግ ሀላፊነት ወድቆብናል፡፡ የኢሕፓን ሰማእታና በአፋኞች የተሰወሩ ጓዶችን በመዘከር የምትደክሙ ጓዶች መኖራችሁን አውቃለሁ።ያላሰለሰ ጥረታችሁን እያደነኩ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡
ንድ ትውልድ የፈጀው ደርግ በሕዝብ ትግል ቢወድቅም በሌላው መሳርያ በያዘ ሰው በቁሙ በሚበላውና በሚቀብረው ሕወሃት ተተካ፡፡ ህወሃት ለ27 አመት ሲገዛ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያልደረሰ በደልና ስቆቃ አልነበረም፡፡ከሰቆቃዎቹ አንዱ አፍኖ መሰወር የተካነበት ነው፡፡ ይህ አስከፊ በደል ከደረሰባቸው ቤተሰቦች አንዷ ነኝ፡፡ ባለቤቴ አቶ ሙሉ አምባው ሚያዚያ 24 ቀን 1989 ዓ.ም በህወሃት ኢህአዴግ አፋኝ ቡድኖች ተወስዶ እስከ ዛሬ የት እንዳደረሱት አናውቅም፡ ጠ/ሚ አቢይ ከመጡም ወዲህ በተደጋጋሚ አመልክቻለሁ።ያገኘሁት ተስፋ ግን የለም።
አዲስ አበባ በተካሄደው የኢሕአፓ ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በዳዲሞስ ተጽፎ በዮኃንስ አፈወርቅ የተነበበው« ያልመጣ ሰው አለ» የሚለው ግጥም በመንግስትም በሕዝብም የረተሳውን የባለቤቴን የአቶ ሙሉ አምባውን ስም በመዘከሩ ምስጋናዬ ከፍተኛ ነው፡፡ ድርጅቱም ከሚታገልለት ሕዝብ ውስጥ ገብቶ የጀመረው ትግል እንዲሳካለት ምኞቴ ነው፡፡ አገራችን ውስጥ አሁን የሚታየው ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆራጥ ትግል የሚያስፈልግበት ወቅት መሆኑ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም፡፡