December 23, 2019

የመራጮችና የዕጩዎች ምዝገባ ለማከናወን ብቻ አራት ወራት ያስፈልጋሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ቀጣዩን ምርጫ በግንቦት ወር ለማካሄድ እንደማይቻል መገመት ቀላል ነው፡፡

ውሉ ያልታወቀው ቀጣዩ ምርጫ

Reporter Amharic 

በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ሥልጣን የያዘው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሥልጣኑን ካገኘበት ማግሥት አንስቶ ከሕዝብ በገጠመው ተቃውሞ፣ በኋላም በራሱ ውስጥ በተፈጠረ ሽኩቻ ሲናጥ ከርሞ ለአምስት ዓመታት የያዘውን የሥልጣን ኮንትራት ሊያጠናቅቅ የጥቂት ወራት ዕድሜ ብቻ ይቀራል፡፡

በመሆኑም በቀሩት ጥቂት ወራት ውስጥ ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገር የማስተዳደር ኮንትራት የሚሰጠው አጠቃላይ ምርጫ መካሄድ ይኖርበታል፡፡ ይህንንም የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነው ሕገ መንግሥት ያስገድዳል፡፡

ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲዎችን አወዳድሮ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሥልጣን ኮንትራት የሚሰጠው ጠቅላላ ምርጫ፣ መቼ እንደሚካሄድ እስካሁን በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

የአገሪቱ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ የፖለቲካ ልሂቃንና ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ የዘንድሮ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ ለማወቅ፣ ከመጠየቅና ምርጫው የሚጠይቀውን ዝግጅት ከማድረግ ተቆጥበው ይስተዋላሉ፡፡

ከዚህ ይልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የፖለቲካ ልሂቃኑ ምርጫው ዘንድሮ መካሄድ አለበት ወይስ የለበትም በሚሉ ሁለት ተቃራኒ ፍላጎቶች ዙሪያ ሳይግባቡ ቆይተዋል፡፡

ከዓመት በፊት ከስደት ፖለቲካ የተመለሱት የኢዜማ ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር) እና የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ውጣ ውረድን ያዩትና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ዘንድው ምርጫ መካሄድ የለበትም ከሚሉት ወገን ናቸው፡፡ የሚያቀርቡትም አመክንዮ በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ቅድሚያ ካላገኘ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማድረግ አይቻልም የሚል ሲሆን፣ አቶ ልደቱ ደግሞ ከተጠቀሱት ባሻገር ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በመሠረታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት እስካልተፈጠረ ድረስ ምርጫውን ማካሄድ ተመልሶ ወደ ነበረው የፖለቲካ ቀውስ መውሰዱ አይቀርም ባይ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያም ሆነ በኦሮሞ ሕዝብ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተፅዕኖ ፈጠሪ የሆኑት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ዶ/ር) እና ፓርቲያቸው፣ የኢሕአዴግ መሥራችና አባል ፓርቲ የሆነው ሕወሓት ደግሞ የዘንድሮው ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ መካሄድ አለበት የሚል አቋም ከሚያራምዱት መካከል ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡

ይህንን አቋም የሚያራምዱት የፖለቲካ ኃይሎች አመክንዮ ደግሞ አሁን በአገሪቱ ለተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት መሠረታዊ ምንጭ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የቅቡልነት (ሌጅትሜሲ) ቀውስ ውስጥ በመግባቱ እንደሆነ በመጥቀስ፣ ችግሩ ሊፈታ የሚችለው ቅቡልነት ያለው መንግሥት በምርጫ አማካይነት ሕዝብ  ሥልጣን ሲሰጠው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ምርጫውን አለማካሄድ ወይም ማራዘም አገሪቱ የገጠማትን ፖለቲካዊ ቀውስና ደም እያፋሰሱ ያሉ ግጭቶችን ማራዘም እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

መጪውን ምርጫ ምን ልዩ ያደርገዋል?

ኢሕአዴግ በተከለው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ባለፉት 27 ዓመታት አምስት ጠቅላላ ምርጫዎች በየአምስት ዓመት ልዩነት የተካሄዱ ሲሆን፣ ውሉ ግልጽ ሆኖ ባይታወቅም ቀጣዩ ምርጫ ለስድስተኛ ጊዜ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቀጣዩ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች ምን ልዩ ያደርገዋል በማለት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕገ መንግሥትና ሰብዓዊ መብቶች ምሁሩ አቶ ምሥጋናው ሙሉጌታ፣ በፖለቲካ ተዋናዮቹና በፖለቲካ ማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ፖለቲካዊ አቋም በመመዘን ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ከፍተኛ ተስፋና ሥጋትን በአንድነት ይዞ የመጣ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ያስረዳሉ፡፡

በቀጣዩ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተስፋ ያሳደሩ የፖለቲካ ስብስቦች መኖራቸው፣ ምርጫውን የሚያስፈጽመው ምርጫ ቦርድ በድጋሚ መዋቀሩ፣ ቀድሞ ከነበረው የተሻለ ገለልተኝነትና ብቃት ባላቸው አመራሮች እንዲመራ መደረጉ፣ መንግሥት  ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ ቁርጠኝነት እንዳለው መግለጹና ጠቋሚ ዕርምጃዎችንም ማሳየቱ፣ ለዚህም እንደ ማሳያ የምርጫ ሕጉንም ሆነ ሌሎች ለፖለቲካዊ መሣሪያ የነበሩ ሕጎችን ማሻሻሉ፣ እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት ዴሞክራሲያዊ ሚና እንዲጎለብት አዋጁ መሻሻሉ፣ በስደት ላይ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት ተመልሰው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ የፖለቲካ ምኅዳሩ በመደላደሉ፣ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ተስፋና ዕድል በተወሰኑት ላይ መፍጠሩን ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ የሚታዩ የፖለቲካ ግጭቶች በማውሳት ምርጫውን ዘንድሮ ለማድረግ የሚያስችል አስተዳደራዊ ሁኔታ እንደሌለ፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምርጫውን ማድረግ ምርጫን ተከትሎ ለሚከሰት ብጥብጥ እንደሚዳርግ ሥጋት አላቸው፡፡ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት የመጫወቻ ሕጉ (ሩል ኦፍ ዘ ጌም) ማለትም በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ ተደርጎ ቅቡልነቱን ማረጋገጥ፣ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠርና የመሳሰሉት ላይ ስምምነት መድረስ ከሁሉ መቅደም እንዳለበት የሚያነሱ የፖለቲካ ኃይሎች ደግሞ፣ ምርጫው መራዘም እንደሚገባው እንደሚከራከሩ ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የተረበሸ የፖለቲካ ሁኔታ በአገሪቱ መፈጠሩ፣ ማለትም የዴሞክራሲ ተቃማት፣ የመንግሥት መዋቅርና ተቋማት ልፍስፍስና ደካማ መሆን ሥጋትን ከሚያጭሩ ምክንያቶች መካከል እንደሚጠቀሱ አቶ ምሥጋናው ያስረዳሉ፡፡

የመንግሥት መዋቅርና ተቋማት ቀድም ሲል የነበራውን ጥንካሬ የተላበሱት ገዥው ፓርቲ እስከ ታች ድረስ በሚዘልቀው የቁጥጥር ሥልቱ አማካይነት የመንግሥት  መዋቅሩና ተቋማቱ ጥንካሬ እንደ ነበራቸው የሚያወሱት አቶ ምሥጋናው፣ በአሁኑ ወቅት በገዥው ፓርቲ ውስጥ ባለው ሽኩቻ የተነሳ መዳከማቸውን፣ ገዥው ፓርቲ ተክሎት ይጠቀምበት የነበረው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መፍረሱ፣ ክልሎች ቀደም ሲል ከነበራቸው የፖለቲካ ተፅዕኖ እጅግ የፈረጠመ የፖለቲካ ጉልበት መላበሳቸውና አንዱ ከሌላው ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታቸው፣ በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ላይ ጥያቄዎች መመዘዝ መጀመራቸው የፖለቲካ ከባቢው በውጥረትና በሥጋት እንዲሞላ ማድረጉን ያስረዳሉ፡፡

በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ አገር እያስተዳደረ ያለው የፖለቲካ ኃይል ምርጫውን አስመልክቶ ለሁለት የተከፈለ ሐሳብ ማራመዱ፣ ማለትም በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ውይይት ተደርጎ እንዲራዘም የሚወሰን ከሆነ ምርጫውን ለማስተላለፍ እንደሚቻል ሲገልጽ ቆይቶ በኋላ ደግሞ ምርጫው መካሄድ እንደሚገባው አቋም መያዙ፣ በተቀሩት የፖለቲካ ኃይሎች ላይ የአቋም ውዥንብር እንዳስከተለና ወደ ዝግጅት እንዳይገቡ እንዳዘናጋ ያመለክታሉ፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ውሉን ያጣው የዘንድሮ ወይም ቀጣዩ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ልሂቃን ለምርጫ ዝግጅት ሲያደርጉም አይታዩም፡፡ ይህ ሁኔታም ገዥው ፓርቲ የሥልጣን ዘመኑን ከጥቂት ወራት በኋላ ሲያጠናቅቅ አገር የማስተዳደር ሕጋዊ ኃላፊነት እንዴትና በማን ላይ ይወድቃል? የሕጋዊ ቅቡልነት ጥያቄስ እንዴት ሊመለስ ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች አፍጥጠው መጥተዋል፡፡

ቀጣዩ ምርጫ በቀሪዎቹ ወራት ይካሄዳል? ወይስ ይራዘማል?

ከላይ በተገለጹት ሁኔታዎች ምክንያት ውሉን ያጣው የዘንድሮ ወይም ቀጣዩ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ልሂቃን ለምርጫ ዝግጅት ሲያደርጉም አይታዩም፡፡

በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ፣ እንዲሁም በአዲሱ የምርጫ ሕግ ተቀመጡ የምርጫ ሒደት ጅማሮን የሚያመላክቱ የጊዜ ማዕቀፎች የምርጫውን መካሄድና አለመካሄድ ሊጠቁሙ ይችላል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፡፡ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል፤›› ይላል፡፡

ከዚህ በላይ ባለው አንቀጽ 58 (2) ድንጋጌ ላይ ደግሞ፣ ‹‹የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት እስከ ሰኔ 30 ነው፡፡ በመካከሉም ምክር ቤቱ በሚወስነው ጊዜ አንድ ወር ዕረፍት ይኖረዋል፤›› ይላል፡፡

ይህንን የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት በማድረግ ምክር ቤቱ ባወጣው የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 24 (1) ድንጋጌ፣ ‹‹በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 (2) መሠረት የምክር ቤቱ አንድ ዓመት የሥራ ጊዜ ከመስከርም ወር መጨረሻ አንስቶ እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ ይሆናል፤›› ይላል፡፡

በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት በሥልጣን ላይ ያለው ምክር ቤት ሥልጣን ዘመን የሚጠናቀቀው በአምስተኛው ዓመት ሰኔ 30 ቀን ላይ እንደሆነ በርካቶች የተስማሙበት ትርጓሜ ነው፡፡ በምክንያትነትም ያለፉት አምስት ዙር አጠቃላይ ምርጫዎች ከግንቦት ወር አልፈው እንደማያውቁ ይጠቅሳሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሕግ ባለሙያው አቶ ምሥጋናው ግን ከላይ የተቀመጡት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች የምክር ቤቱን ዓመታዊ የሥራ ወቅት የሚያስቀምጡ እንጂ፣ የሥልጣን ዘመን ማብቂያውን አስረግጠው የሚናገሩ አይደሉም ባይ ናቸው፡፡

ስለሆነም የአንድ የተመረጠ ምክር ቤት የሥልጣን ዘመን የሚጀምረው በመስከረም ወር መጨረሻ ሳምንት ላይ በመሆኑ፣ የሥልጣን ዘመኑ አምስተኛው ዓመት የሚጠናቀቀውም በመስከረም ወር ተደርጎ ሊተረጎም እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ትርጓሜ ከተሄደ ቀጣዩ ምርጫ የሥልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት የሚለው ድንጋጌ ተወስዶ ሲሠላ በሐምሌ ወር ምርጫውን ማድረግ እንደሚቻል፣ ነገር ግን ወቅቱ የዝናብና የእርሻ ወቅት በመሆኑ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግም ሆነ ምርጫውን ለማስፈጸም ወሳኝና ከባድ ሥራ ለሆነው ሎጂስቲክስ ፈታኝ እንደሚያደርገው ይገልጻሉ፡፡

በምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችን ማማከር በምርጫ ሕጉ ላይ የተቀመጠ በመሆኑ፣ ምርጫው በክረምት ወቅት ይደረግ ቢባል ውስን ሀብት ላላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስቸጋሪና ወጪን የሚያንር በመሆኑ ስምምነት ይደረስበታል ብለው እንደሚገምቱ ያስረዳሉ፡፡

ከላይ በተቀመጡት ሁለቱም ትርጓሜዎች መሠረት ለምርጫው የቀረው ጊዜ በመጀመርያው አማራጭ ሲወሰድ አምስት ወራት ሲሆን፣ በሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ሰባት ወራት ይቀራሉ፡፡

በአዲሱ የምርጫ አዋጅ መሠረት የጠቅላላ ምርጫ ቦርዱ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሚከናወን ይገልጻል፡፡ ምርጫ ቦርድ እስካሁን የቀጣዩን ምርጫ ጊዜ ሰሌዳ አላወጣም፡፡

በዚሁ ሕግ መሠረት ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳውን ለማውጣት መሠረት ከሚሆኑት አንዱ የምክር ቤቱ የሥልጣን ጊዜ ማብቂ በምን በወር እንደሆነ መለየት፣ በአዲሱ አዋጅ መሠረት የተቀመጡ የዕጩዎች ምዝገባና የመራጮች ምዝገባን የተመለከቱ የጊዜ ማዕቀፎችን ከግምት ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡

በሕጉ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ከመጀመሩ በፊት ለ15 ቀናት በመገናኛ ብዙኃን ማስተዋወቅ የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኃላ ደግሞ ለአሥር ቀናት ምዝገባውን ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ‹‹የዕጩ ምዝገባ ከምርጫው ዕለት ቢያንስ 90 ቀናት (ሦስት ወራት) አስቀድሞ ቦርዱ ለዕጩዎች ምዝገባ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በምርጫ ክልሎች ይከናወናል፤›› በሚለው የምርጫ ሕጉ ድንጋጌ መሠረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ይህም ማለት የመራጮችና የዕጩዎች ምዝገባ ለማከናወን ብቻ አራት ወራት ያስፈልጋሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ቀጣዩን ምርጫ በግንቦት ወር ለማካሄድ እንደማይቻል መገመት ቀላል ነው፡፡

በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና አጋሮቹ ውህደት በመፈጸም ብልፅግና ፓርቲ የተባለ አገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ለመመሥረት ተስማምተው፣ የምዝገባ ጥያቄያቸውን ለምርጫ ቦርድ ማቅረባቸው ነገሩን ያወሳስበዋል፡፡

ለዚህም ምክንያቱ በአዲሱ አዋጅ ላይ በሕግ የተመዘገቡ ፓርቲዎቹ ጠቅላላ ምርጫ ወይም የአካባቢ ምርጫ በሚካሄድበት ዓመት ለመዋሀድ የፈለጉ እንደሆነ፣ ጥያቄያቸውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ከመውጣቱ ከሁለት ወራት በፊት በጽሑፍ ለቦርዱ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል የሚል ድንጋጌ የያዘ በመሆኑ ነው፡፡

የውህደት ጥያቄው ለምርጫ ቦርድ የቀረበ በመሆኑ ቦርዱ የቀጣዩን ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ለማውጣት፣ ቢያንስ እስከ ጥር ወር አጋማሽ ድረስ መጠበቅ ይኖርበታል እንደ ማለት ነው፡፡

ቀጣዩ ምርጫ መቼ እንደሚከናወንና የቀሩት ወራት ጥቂት መሆናቸውን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቦርዱ ሰብሳቢ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ፣ ምርጫው የሚካሄድበትን ቀን ቦርዱ እስካሁን እንዳልወሰነ ነገር ግን ለምርጫው የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን ቦርዱ በማካናወን ላይ እንደሚኝ ተናግረዋል፡፡

የቀሩት ጊዜያት በጣም ጥቂት ቢሆኑም፣ ቦርዱ ለምርጫው የሚያስፈልጉትን ዝግጅቶች በታቻለው አቅም ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል ለ50 ሺሕ ምርጫ ጣቢዎች የሚያስፈልጉ ዘመናዊ የድምፅ መስጫ ሳጥኖች፣ የመራጮች ምዝገባ ፎርም፣ የመራጮች መለያ ካርድና የመሳሰለት ኅትመቶች መጠባበቂያዎችን ጨምሮ በዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር በውጭ አገር ለማሳተም ስምምነት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

ኅትመቶቹ ዓለም አቀፍ ደረጃና ጥራት ይዘው የሚከናወኑ እንደሆነና አጠቃላይ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ግዥ ቦርዱ ባወጣው ዲዛይንና ስፔሲፊኬሽን መሠረት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍና የግዥ ሒደት የሚፈጸም እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ያለው ጊዜ አጭር ከመሆኑ በተጨማሪ ገዥው ፓርቲና አጋሮቹ ለመዋሀድ ጥያቄ ማቅረባቸውና ይህንን ውህደት ለመፈጸም በሕግ መሠረት የሚወስደው ጊዜ ሲታከል፣ የጊዜ መጣበቡን የበለጠ ያባብሰው እንደሆነ የተጠየቁት የሕዝብ ግንኙነት አማካሪዋ፣ ‹‹ገዥው ፓርቲ ውህደት መጠየቁ ከምርጫው ጋር የሚያገናኘውም ሆነ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

የዕጩዎች ምዝገባ ከመካሄዱ በፊት የምዝገባ ሰርተፊኬት ከቦርዱ ያገኘ ማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት፣ በምርጫው ለመሳተፍ እንደሚችልም አክለው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቦርዱ ምርጫው የሚያካሂድበትን ቀንና አጠቃላይ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳውን አለማውጣቱና የገዥው ፓርቲ የሥልጣን ዘመን ሊጠናቀቅ የቀሩት ጊዜያት አጭር መሆን ጋር ተያይዞ፣ ምርጫው የሥልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ በፊት ባይካሄድ አገር የማስተዳደር ሕጋዊ ኃላፊነት እንዴትና በማን ላይ ይወድቃል? የሕጋዊ ቅቡልነት ጥያቄስ እንዴት ሊመለስ ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች አፍጥጠው መጥተዋል፡፡

አቶ ምሥጋናው ይህ አጣብቂኝ ከተፈጠረ ሊሆን የሚችለው የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 60 ድንጋጌ በመጠቀም ፓርላማውን በመበተን መተንፈሻ ጊዜ ማግኘት፣ እንዲሁም ምርጫውን ከመጪው ክረምት በኋላ ማካሄድ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 (1) ላይ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማው የሥልጣን ዘመን ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ፣ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡

በዚህ መሠረት ምክር ቤቱ የተበተነ እንደሆነ ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አዲስ ምርጫ መደረግ እንደሚኖርበት፣ ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ ሥልጣን ላይ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራ ጊዜያዊ አስተዳደር ሆኖ ሕግ የማውጣትና የመሻር ሥልጣኑ ተገድቦ፣ የዕለት ተዕለት የመንግሥት ኃላፊነትን መከወንና ምርጫውን ማከናወን ብቻ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

በዚህ አማራጭ ከተኬደ በተጣበበ ጊዜ ውስጥ ምርጫ ማድረግ ሊፈጥረው የሚችለውን አክል ማስቀረት የሚቻል እንደሆነና ሥልጣኑ የሞግዚትነት አስተዳደር በመሆኑ የቅቡልነት ጥያቄ የሚነሳበት እንደልሆነ አቶ ምሥጋናው አስታውቀዋል፡፡