December 29, 2019

Source: https://mereja.com/amharic/v2/190647

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመቀነስ በአብሮነትና በሰላም ላይ እየሰራን ነው

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመቀነስ በአብሮነትና በሰላም ላይ እየሰሩ መሆናቸውን የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

በሀገሪቷ ከፍትኛ ትምህርት ተቋማት የሚፈጠሩ ግጭቶች ብዙዎቹ መነሻቸው የጥቂት ግለሰቦች የፖለቲካ ሴራ እንደሆነ ይናገራሉ።

በመሆኑም ተማሪዎቹ የሁላችንም ልጆችና የነገ ሀገር ተረካቢዎች መሆናቸውን አውቀን የጥቂት ሰዎች የፖለቲካ ንግድ ማስፈፀሚያ እንዳይሆኑ የመከላከል ትልቅ ሃላፊነት አለብን ሲሉም ተናግረዋል ።

ለዚህም መንግስት ከሚያደርገው ህግና ሰላም የማስጠበቅ ስራ ጎን ለጎን ለተማሪዎቹ ቀደም ብሎ የነበሩንን የአብሮነት፣ የመተሳሰብ እንዲሁም የአንድነት እሴቶቻችንን ከማስተማር አኳያ እየሰራን ነው ብለዋል።

“እሴቶቻችን መፈቃቀር ነው፤ እሴቶቻችን በተቸገርን ጊዜ በጋራ እንድንቆም እንጂ ያለንን ሰላም፣ ልማትና ትምህርት የማውደም፣ የማጥፋት አይደለም።“የሚሉን ፓስተር ዳኒኤል ገብረስላሴ ከአዲስ አበባ ናቸው፡፡

የድሬ ደዋው አቶ ሃጂ መሐመድ ጅብሪል በበኩላቸው “እኛ እንደ ሀገር ሽማግሌ እንደ ኃይማኖት አባት ገብተን ያንን ነገር ከመንግስት ጋር ሆነን ልጆቻንን እየመከርን “ነው ብለዋል፡፡

ተማሪዎቹም በማህበረሰቡ ውስጥ በሚፈጠሩ የፖለቲካና ሌሎች ግጭቶች እንዲሁም በጥቂት ፖለቲከኞች ሃሳብ ተፅዕኖ ስር በመውደቅ ዓላማቸውን መሳትና ባልሆነ ግጭት ውስጥ መግባት የለባቸውም ሲሉም ተናግረዋል።

ግጭትና ፖለቲካ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የነበረና የሚኖር መሆናቸውን የተናገሩት የአገር ሽማግሌዎቹ፤  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ለችግሮቹ መፍትሄ እንጂ የግጭት ቦታ መሆን እንደሌለባቸውም ተናግረዋል።

ይልቁንም በከፍታኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የመጡበትን አካባቢ ባህልና ወግ በማስተዋወቅና በማዳበር አንድነታቸውን አጠናክረው ህብረ ብሄራዊ ኢትዮጵያን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋልም ሲሉ ተናግረዋል።

ኢዜአ