ሠላማዊት ገብሬ የበርኖስ ሥራ ላይ

ነዋሪነቷን አዲስ አበባ ያደረገችው ሠላማዊት ገብሬ የበርኖስ ሥራን ከአባቷ እንደተማረች ትናገራለች። አባቷ ከዓመታት በፊት በርኖስ በማሠራት ወደ አዲስ አበባ እያስመጡ ይሸጡ ነበር። መርካቶ መንዝ በረንዳ ወይንም 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚባለው አካባቢም መሸጫ ሱቅ ነበራቸው።

በዚህ ወቅት ነው ሠላማዊት ስለበርኖስ ብዙ ነገሮችን የተማረችው። በርኖስ የሚሠራው ከበግ ጸጉር ቢሆንም ሁሉም የበግ ጸጉር ግን ለበርኖስ ሥራ አያገለግልም ትላለች።

እንደበጎቹ መጠን ታይቶ ከአስር እስከ አስራ ሶስት የሚሆኑ ጥቁር በጎች ይመረጣሉ።

• የኬንያ ዳኞችን አለባበስ የቀየረች ኢትዮጵያዊት

• ሜድ ኢን ቻይና- የሀገር ባህል አልባሳቶቻችን

“ለበርኖስ ሥራ የሚያገለግሉት በጎች የሪዝ በግ መሆን አለባቸው። ይህም በርኖሱ ለስላሳ መሆን ስላለበት ነው” ይላሉ የመንዝ ማማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የቅርስ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታምሩ ፍቅረ።

ጥቁር በጎች ሆነው ጸጉራቸው በተደጋጋሚ ከተቆረጠ ጸጉሩ ጠንካራ ስለሚሆን ሲለበስ ይኮሰኩሳል። የእነዚህ በጎች ጸጉር ጠንካራ ስለሆነ ባና ወይንም ዝተት ለሚባለውና እንደጋቢ ያለ በብርድ ወይንም በመኝታ ወቅት የሚለበስ ልብስ ይሠራበታል።

“ባና ከማንኛውም በግ ጸጉር ይሠራል። ቀለሙም ዳልቻ፣ ነጭ ወይንም ጥቁር ሊሆን ይችላል። ለበርኖስ ግን ለስላሳ ሪዝ ያለው የጥቁር በግ ጸጉር ነው የሚያስፈልገው” ይላሉ ባለሙያው።

ለበርኖስ ሥራ ጸጉራቸው የተመረጡት በጎች በደንብ ይታጠባሉ። ከዚያ እንዲደርቁ ይደረጋል።

“ምንም እንዳይጎሳቆል እና ቆሻሻ እንዳይነካው ቁርበት ላይ ተደርጎ ጸጉሩ ይቆረጣል” ይላሉ አቶ ታምሩ።

በግ የሚሸልቱ አርሶ አደር

ቀጥሎ የሚከናወነው በእናቶች ፋቶው ይፋታል። ፋቶ ማለት ጸጉሩን ነጣጥሎ እንዲደርቅ ማድረግ ነው።

የደረቀው የበግ ጸጉር እስኪልም ድረስ በደጋን ተነድፎ አመልማሎ ይሠራል። አመልማሎ ማለት እየተሽመለመለ ማድበልበል ማለት ነው።

ቀጣዩ ሥራ የተድበለበለውን የበግ ጸጉር በእንዝርት መፍተል ነው። ፈትሉ በኳስ መልክ የሚዘጋጅ ሲሆን ኳሱን እየተረተሩ የማድራት ሥራው ይከናወናል።

ከዚህ በኋላ ያለው ሥራ ሽመና ነው። ከጋቢ ወይንም ከነጠላ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የሽመና ሥራው ይከናወናል።

የሽመና ሥራው አልቆ ከተጠናቀቀ በኋላ ንጹህ ውሃ ውስጥ ይረገጣል።

“ጋቢ እንደማጠብ ነው የሚረገጠው። ጥቅጥቅ እንዲል ነው የሚረገጠው። ካልተረገጠ አይጠቀጠቀም። ሲረገጥም በየቀለሙ እየተለየ ነው። ጥቁሩ ከጥቁር ጋር ነጩ ከነጭ ጋር ብቻ ይረገጣል። ከተደባለቀ በርኖሱ ነጭ ይሆናል” ትላለች ሠላማዊት።

• ባህልን በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ የቀመመው ሮፍናን

• ‘ኢትዮጵያዊነት’ ከጄሰን ድሩሎ ጀርባ ያለው ቡድን

ቀጣዩ ሥራ የተዘጋጀውን በርኖስ ወደ ልብስነት መቀየር ነው። አንዱ በርኖስ ወደ ልብስነት ሲቀየር ከአንድ ሰው በላይ አይሆንም።

“በስፌት ወቅት ከሚለበሰው በርኖስ የሚተርፈው ቁርጥራጭ የጣውላ ወለል ላላቸው ቤቶች መወልወያነት ያገለግላል”

“ቀደም ሲል ጀምሮ ለልብስነት የሚውለው በርኖስ ቀለም ጥቁር ብቻ ነው ይለኝ ነበር አባቴ” የምትለው ሠላማዊት “ሌላ ቀለም ካለው ግን እንደ ብርድ ልብስ ያገለግላል” ትላለች።

በርኖስ በአንድ በኩል ወጣ ያለ ቅርጽ ያለው ባህላዊ ልብስ ነው። ይህም የጦር መሣሪያ ለመያዝ እንዲያመች ሆኖ የተሠራ መሆኑን ሠላማዊት ትናገራለች።

በሠላማዊት ሃሳብ የሚስማሙት አቶ ታምሩ “አባቶቻችን ጀግኖች ናቸው። የጦር መሣሪያ በዛች ውስጥ ይይዙ ነበር። መሣሪያ ይያዙ አይያዙ አይታወቅም። መሣሪያ ለመደበቅ የሚጠቀሙባት ቀንድ መሰል ቅርጽ ያለው ነው” ብለዋል።

በርኖስ በተለይ በመንዝ አካባቢ በስፋት የሚለበስ ባህላዊ ልብስ ነው። በሃዘንም ሆነ በደስታ ወቅት የሚለበስ ነው። “በተለያዩ አካባቢዎች ለሠርግም ሆነ ለሃዘን የሚለበስ ባህላዊ ልብስ ነው” የምትለው ሠላማዊት “የገና በዓል ሲከበር ደግሞ የገና ጨዋታም የሚከናወነው በዚሁ ልብስ ነው” ትላለች።

ቀደም ሲል በርኖስ በስፋት ይለበስ ነበር። “በቀን እሰከ 30 የሚደርስ በርኖስ ከአባቴ ሱቅ ይሸጥ ነበር” የምትለው ሠላማዊት “ከበርኖስ በተጨማሪ እንደ ብርድ ልብስ የሚያገለግለው ባና ወደ አሥመራ ጭምር ይላክ ነበር” ትላለች።

አይደለም በሌሎች አካባቢዎች በርኖስ በስፋት ይሠራበታል በሚባልበት መንዝ አካባቢ ጭምር ሥራው ተቀዛቅዟል።

“አሁን ሰዉ ወደ ብርድ ልብስ ሄዷል። በርኖስ የሚለብሱ ሰዎች ስለሌሉ ሥራውን የሚሠሩ 10 የሚሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው” ይላሉ አቶ ታምሩ።

በርኖስ የሚለብሱ ሰዎች ቁጥር ከማነሱም በላይ ሥራውም ረዥም ጊዜ የሚፈልግ እና አድካሚ ነው።

“ይኮሰኩሳል” ትላለች ሠላማዊት “ይኮሰኩሳል። ስለሚኮሰኩስም ሰዉ መጠቀም ተወው። በፊት እንደብርድ ልብስ ከአንሶላ ጋር ይለበስ ነበር። እኛም ለብሰነው ነው ያደግነው። አሁን በብርድ ልብስ እየተቀየረ ነው። ዘመኑ የሻረው ይመስለኛል” ብላለች።

ቀደም ሲል መርካቶ ሚሊተሪ ተራ በሚገኙ ሱቆች ውስጥ በብዛት የሚሸጥ የነበረው በርኖስ በአሁኑ ወቅት ከሁለት እና ሶስት ሱቆች በላይ ይህንን አይሸጡም።

በተለያዩ የባህል ቁሳቁስ መሸጫ ሱቆች ውስጥም ቢሆን በርኖስም ሆነ ባና የመሸጥ ልምዱ እየቀዘቀዘ ይገኛል።

“የሰሜን ሸዋ የባህል አለባበስ ሲነሳ በርኖስ በቀዳሚነት ይጠቀሳል” የሚሉት የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት መኳንንቴ “በርኖስ በመንዝ ማማ ወረዳ በደንብ ይሠራል” ይላሉ።

ባህሉን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እና ሥራውን ሌሎችም እንዲያውቁት በማድረግ የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው ይላሉ።

“ሌሎች ባህላዊ ቁሳቁሶችን የሚሠሩ እና ምንሊክ መስኮት በሚባለው አካባቢ ያሉ ሰዎች እንዲሠሩ ለማስተማር የቤት ሥራ ወስደናል” ብለዋል።

በርኖስ የሚሠሩ ጥቂት ሰዎች መኖራቸው በራሱ እረፍት እንደሚሰጣት ሠላማዊት ትናገራለች።

ሥራውን ለማጠናከር ደግሞ አንድ ፕሮጀክት ተቋቁሞ ቢሠራ ውጤታማ እንደሚሆን ታምናለች።

“በፊት ሞላሌ ከተማ ላይ የባና ፕሮጀክት ነበር። ፕሮጀክቱ ተመሥርቶ ይንቀሳቀሱ በማህበር ተደራጅተው ይሠሩ ነበር። አባቴም በበርኖስ ንግድ እና ሥራ ላይ በተሠማራበት ወቅት ፕሮጀክቱ ነበር” ትላለች።

ሠላማዊት ተመሳሳይ ፕሮጀክት ተቋቁሞ የበርኖስ ሥራ እንዲስፋፋ እና ከአባቷ ያገኘችው የበርኖስ ሥራ በቀጣይ ትውልድም ቀጥሎ ማየት ህልሟ ነው።