December 30, 2019

Source: https://www.zehabesha.com/amharic/archives/100027

ሰው ከንሰሳ የሚሻለው የሕይወት መመሪያ ስላለው ነው፤ ስለአገር የሚያስብ ደግሞ ከራሱ ከቤተሰቡና ከጎሣው አልፎ የሁሉንም ሕዝብ የጋራ ፍላጎት የማየት መርህ ሊኖረው ይኖረዋል። በክፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ከተማርነው ነገር ውስጥ አንዱ ስለፍልስፍና/መርህ/ ነው፡፡ የአውሮፓን፣ እስያን፣ የአፍሪቃን፣ የአሜሪካን፣ ወዘተ ታሪኮች  ወይም ስለነአሪስቶትል፣ ስለነጆን ሎክ፣ኒሮ ክላውዲየስ፣ ናፖሊዎን ቦናፓርት፣ አዶልፍ ሒትለር፣ ማህተማ ጋንዲ፣ ካርል ማርክስ፣ ሜሪ ኩሪ፣ አልበርት አይንስታይን . . . ወዘተ ስለማህበራዊ ኑሮ፣ ስለባህልና ቴክኖሎጅ እድገት ወዘተ ታሪኮችንና ግኝቶችን  ያጠናነው ደጉንና ክፉውን አውቀን ስለመልካም የመንግሥት አመራር፣ ስለሕዝብ ዲሞክራሲ ስለለዜጎች እኩልነት፣ ስለሕግና ስለፍትሕ. …. ወዘተ መሠረቶች፣   ፍልስፍና ወይም ዓለም-አቀፍ መርህ/universal principle/ ኖሮን የሰው ልጅ በእኩልነት የሚመራበትንና አገር በተሻለ መንገድ የሚበለጽግበትን ጥበብ ለመቅሰም ነው፡፡ አገር የግለሰቦች ጥርቅም ስለሆነ የግለሰቦች ሕልም በአገር፣ በክፍለአህጉርና በዓለአቀፍ ደረጃ ባሉ ማኅበራዊ እሴቶች ውስጥ እንደሚዋጥ መረዳት ይቻላል፤ ሆኖም ይህን እውነታ የማያውቅ አንድም የመማር ዕድል ያላጋጠመው ሁለተኛ ተምሮም ያልገባው መሆን አለበት። ፍልስፍና ያለው የተማረ ሰው መርህን ይከተላል፤ ፍልስፍና የሌለው ከሆነ ግን ማንም እንደከብት ወደፈለገው አቅጣጫ ይመራዋል። ለምሳሌ አንድ አሜሪካዊ የዘር ሐረጉ ከየት እንደሆነ ቢያውቀውም ስለዜግነቱ ሲጠየቅ “አሜሪካዊ ነኝ” ስለቋንቋው ሲጠየቅ “እንግሊዝኛ ተናጋሪ ነኝ” ከማለት ለአፍታም አይዳዳውም፤ ምክንያቱም በትልቅነት እምነት ስለተካነ ነው፤ ትልቋ አሜሪካ የምታስገኝለትን ጥቅም፣ ነፃነት፣ ልዕልና፣ ክብርና መብቶች ሁሉ እያየ አእምሮው የተቀረጸ ከመሆኑም በላይ በቋንቋ መለያየት ሳይሆን በቋንቁ መግባባት የሁሉንም ማኅበረሰቦች የጋራ ጥቅም እንደሚያስከበር ስለሚረዳ ነው። በአንዳንድ የኛ ምሁራን ግን በጎሣቸው ተለይቶ መደራጀት ትልቁን ጥቅም፣ ነፃነት፣ ልዕልና፣ ክብርና መብቶች ሁሉ እንደሚያጓድልባቸው የመረዳት ብስለት ላይ መድረስ አለመድረሳቸው ሊጤን ይገባል።  ሰው በማኅበራዊ ፍጡርነቱ ብቻውን መኖር እንደማይችል ሁሉ ኅብረተሰብም እርስ በርሱ መደጋገፉ የማኅበራዊ ሳይንስ እውነታ ነው፡፡ የተለያዩ መልከአምድራዊ ባህርዮች በኢትዮጵያ መኖር ለማኅበራዊ የሥራ ክፍፍል፣ አንዱ የጎደለበትን ሌላው አሟልቶለት የተለያዩ ፍላጎቶችን በማሟላት የእሴቶችን ሥርጭት ከባእድ ምዝበራ በማዳንና በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም በአንድ ትልቅ ማኅበራዊ ተቋም (አገር) ውስጥ መታቀፍ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ የበለፀጉ አገሮችን የውስጥ ጥንካሬ ብቻ ማየት ትምህርት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምሥራቅ የመገኘቷን ጥቅም ከእጃችን ወጥቶ  ባህር ተሻግረው በሚመጡ አገሮች ሥር እንዳይወድቅ ያለንን የጋራ አመለካከት ሰፋ አድርጎ መመርመር ይገባናል፡፡

ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ቢያንስ ከ150 በላይ የሆኑ የፖሊቲካ ድርጅቶች እንደአሸን ፈልተው፤ ከፊሎቹ ከስመዋል፤ ከፊሎቹ በሌሎች ተውጠዋል፤ ከፊሎቹ ተዋህደዋል፤ ለደጉም ሆነ ለክፉ ዓላማቸውንና ስማቸውን ይዘው የዘለቁትን ሕዝቡ ራሱ ያውቃቸዋል፡፡ አንድ  ድርጅት የነእከሌ ነው ተብሎ መታወቅ ድርጅቱ ሳይሆን ሰውዬው ዋጋ ስለሚሰጠው ሰዎች ከድርጅት ምን ያህል ገዝፈው እንደሚታዩ ያመለክታል። የድርጅት ትልቅነት የታወቀን የሕዝብ ጉዳይ ቀጥ አድርጎ ይዞ በመቆየት የሕዝብን አመኔታ አግኝቶ በአገር ላይ ፖሊቲካዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፍትሐዊ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የሕዝብ መሣሪያ የሚሆን ባህል መገንባቱ ነው፡፡ የፖሊቲካ ባህላችን በመሬት ላይ ያለውን የሕዝብ ችግር የመፍታት ዓላማ ላይ ያተኮረ፣ ከግለሰባዊ አመለካከት አልፎ ሕዝባዊና ርዕዮተ፟ዓለማዊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ እንደአሸን መፍላቱ በሕዝባዊ መርህ ጋር ከመጣመር ጋር መገናዘብ ይኖርበታል፡፡ እዚህ ላይ መረዳት የሚቻለው ባህል ማኅበራዊ እንደመሆኑ መጠን የኅብረተሰቡ ባህል በመርህ የዳበረ ከሆነ በመርህ የሚመራ ስለሚሆን መሪዎችን እንደጣኦት ማምለክ/personality cult/ ስለማይኖር አምባገነንነት ቦታ አይኖረውም።   ታዲያ የኛ ሰዎች የት ነው ያሉት?

“የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንደሚባለው ባሁኑ ጊዜ በሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ነገር ግን  ለሰው ልጅ እኩልነትና  ነፃነት መቆም ሲጠበቅባቸው፣ ቦዘኔዎችንና በዝቅተኛ ንቃተ-ኅሊና እንደመንጋ የሚነዱ የዋሆችን በመደለል  ለሰው ልጅ ልዕልና ሳይሆን በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሣ እየለዩ ማሰዘረፍ፣  ማሳደድ፣ ማስገደል የአረመኔነት/ savagery/ ተልእኮ ማራመድ የሚያስደስታቸው “ምሁራን” ተብዬዎች ክፖሊቲካ ድርጅት በስተኋላ መኖራቸው  የመሻሻል ማነቆ ሆኖ ተገኝቷል። “ሆድ ሲያውቅ. . .” እንደሚባለው ለሕዝብ ቆመናል በሚሉ ድርጅቶች  የንጹሐን ዜጎችን እልቂት ለመሸፈን ሰው-ሠራሽ አሐዞችን  በመጠቀም የውሸት ዜና በመገናኛ ብዙሐን ማስተላለፍ ወይም መረጃዎችን አዛብቶ በማቅረብ ሕዝብን ማጎሳቆል ማንንም እንደማይጠቅምና  ማንንስ እንደሚጎዳ ፣ ምን ትርፍ እንደሚገኝበት ይገነዘቡ ይሆን? ስለእኩልነት እየደሰኮሩ አሁንም በዘር ላይ የተመሠረቱ ድርጅቶችን ይዞ ለመንቀሳቀስ የሚደረገው  የማኬይቬላዊ ፍልስፍና የአገርን ብሔራዊ ጥቅም እንደሚጠቅም ወይም ወደኋላ እንደሚጎትት ይረዱ ይሆን? በተለይም ሥራ አጦችን በመደለልና በመቅጠር ጭምር የሚደረግ የጥፋት ዘመቻ በሰላም የሚኖሩ ዜጎችን እርስ በርስ በማጋጨት መተማመንን በማጥፋት፣ የርስበርስ ግንኙነትን፣ መገበያየትንና  ምርታማነትን ይቀንሳል ወይስ ይገነባል ብለው ይገምቱ ይሆን?

ድንቢጥ ብታልም ጥሬዋን እንደሚባለው ጠባብ ፖሊቲከኞች ትልቋ ኢትዮጵያ የምታስገኝላቸውን ጥቅሞች ማየት መቻላቸው ያጠራጥራል። በትልቅ ገበታ ከወገኖቻቸው ጋር ተካፍለው ሳይሆን በጠባብ ወጭት መብላትን የመምረጥ ሕልም ያላቸው ይመስላል፤ በጋራ በሚለማ ትልቅ አገር በጋራ ከመኖር ይልቅ በትንንሽ ጎጆዎች ውስጥ ለብቻቸው የመኖር ሕልም ያላቸው ታይተዋል፡፡ ከቁሳቁስ ድህነት የአስተሳሰብ ድህነት የድህነት ሁሉ ድህነት ነው። “በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ…”  እንደተባለው አርቆ የማያስተውልና ከሌላው ስህተት እንኳ የማይማር ከጥፋቱ ተጎድቶ ቢማርም ያመለጠውን መልሶ ማግኘት ግን አይችልም፤ በተለይ በአገር ላይ የሚፈጸም ጥፋት ተመልሶ የሚታረምበት መንገድ ውሱን ስለሆነ ስህተቶች እንዳይፈጸሙ ከፍተኛ ኃላፊነትና ጥንቃቄ ይፈልጋል። የአንድነትን ጥቅም እንኳን ሰው እንሰሳ  እንኳ ያውቃል፤ ሆኖም ከቆየው የአስተሳሰብ ድህነት ለመውጣት አንዱ ተረቶ ሌላው ረቶ የሚመለስበት ሳይሆን ከባላንጣ ጋር በጠረጰዛ ዙሪያ ተነጋግሮ ጠብን ወደሰላም በመለወጥ  ሁሉም የሚያገኝበትን  አስተሳሰብ (win-win) ማሰብ፣  በዓለም ላይ የበለጸጉ አገሮች ለምን እንደበለጸጉ ያልበለጸጉ አገሮች ደግሞ ለምን ወደኋላ ቀርተው እንደደኸዩ በመመልከት፣ መልካም መልካሙንና በተለየም ለአገራችን የሚጠቅመውን ልምድ መምረጥ ብልኅነት ነው።

መማር የተሻለ ነገር መሥራት ወይስ ጥፋትን በጥፋት ለመተካት?

ሰው ማኅበራዊ እንሰሳ ተብሎ የሚታወቅ የማኅበራዊ ሳይንስ ውጤት ነው፤ አንድ ወላጅ እንኳ በልጆቹ መካከል አለመግባባት ቢፈጠር ማቀራረብንና አንድነትን እንጂ ልጁን ከወንድሞቹ አያጣላም፤ አንዱን ልጅ አወድሶ ሌላ ልጁን ኮንኖ አይለያያቸውም፤ ጠበኛውን ከወንድሞቹ ያስማማዋል እንጂ አያባርረውም፤ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ቤተሰብ ልንታይ የምንችል ትልቅ ማኅበራዊ ስብሰብ ነን፤ ከአንድ ወንዝ ጠጥተናል፤ የጋራ ጠላቶችን ተጋፍጠን አብረን ሞተን በአንድ ጉድጓድ ተቀብረን  አገራችንን በጋራ ጠብቀን አቆይተናታል፤ የተፈጥሮና ሰው-ሠራሽ ችግሮችን እኩል ተካፍለናል፤ በዚህም የተነሣ ተወራራሽ ባህል አለን፤ ተወራራሽ አኗኗር አለን፤ ተመሣሣይ ቋንቋም አለን፤ በዘመናት መስተጋብር ደምም የተዋኻደን ስለሆነ በቆዳ ቀላማችን ስለመመሳሰላችንም ሌላው ዓለም እንኳ ይመስክራል። የኛ መዋኻድ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ታሪክ ከመጻፉ በፊት ጀምሮ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሲዳማ፣ ሐዲያ፣ ወዘተ የሚባሉ መለያዎች ከመፈጠራቸው በፊት የነበረ ነው።  ኢትዮጵያ በዘመናት አባቶቻችን የተገነባች አገር መሆኗ ሁሉንም የኢትዮጵያ ወገን ሊያስኮራ ይገባል፤ ኢትዮጵያውያን  እንደንብ ተባብረው አገራቸውን ጠብቀው በነፃነት ከማቆየታቸውም በላይ ለአፍሪቃውያን ነፃነት ጎህ ቀዳጅ በመሆንና  ፓን-አፍሪቃን የሚባለውን  አህጉራዊ የነፃነት ንቅናቄ ፊታውራሪ በመሆን የነፃነት ታጋዮችን መርታ ለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መመሥረትና ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ያልወጡ የአፍሪቃ አግሮች ነፃ እንዲወጡ  ግምባር ቀደም ታጋይና አታጋይ  በመሆን  ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። ለምሳሌ ለሶማሊያ፣ በኔልሰን ማንዴላ የሚመራ የደቡብ አፍሪቃ ነፃነት ትግል (African National Congress)፣ ለዚምባብዌ በሮበርት ሙጋቤ የሚመራው የዛኑ ድርጅት የነፃነት ትግል፣ የአንጎላ [Popular Movement for the Liberation of Angola (MPLA)]፣ . .  ወዘተ የዲፕሎማሲና የወታደራዊ ትግል ሥልጠና በመስጠት ጭምር ወደር በሌለው  እገዛ ነፃነት እንዲያገኙ አድርጋለች፣ ግጭቶትች ሲነሱ የማስታረቅ ሚናዎችን ተጫውታለች። በዚህ የተነሣ ኢትዮጵያ ለቅኝ ገዥዎች ምኞት ጽልመት ስለሆነችባቸው የርሷን መከፋፈልና መዳከም ተግባራዊ ለማድረግ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፤ በአድዋ፣ በማይጨው፣ በሌሎችም ጦርነቶች ተባብረውባታል፤ በኮሪያ፣ በክንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን . . . ወዘተ ለዓለም ሰላም ወታደራዊ አስተዋፅኦ በማድረግ መስዋዕትነት ብትከፍልም ኃያላን አገሮች የራሷን ልማት ለማሳደግ ያደረጉላት እገዛ አልነበረም። እስካሁንም ድረስ በአባይ ወንዝ፣ በቀይ ባህር እንዲሁም በጅቡቲና በአሰብ የባህር በሮች እንዳትጠቀም ተጽእኖ እያደረጉባት ይገኛል። ኃያላን መንግሥታት ለራሳቸው አንድነትና አገራዊ ጥቅሞች ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እዳጊ አገሮች ላይ ግን የሚፈጠሩ የጎጥ ልዩነቶችን ያበረታታሉ፤ ለምሳሌ በ1948 ዓም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰነውን የፍልስጥኤምን ነፃ አገር መሆን እንዳይፈጸም አድርገዋል፤ ዩጎዝላቪያን፣ ኮሪያን፣ ኮንጎን  ከፋፈሏቸው፣ የሱዳንን መከፋፈል አበረታቱ፣ የኤርትራን፣  የጅቡቲን፣ የቲሞርን፣ የታሎኒያን፣  መገንጠል ያበረታታሉ፤ ታይዋን ከቻይና ጋር እንዳትዋኻድ ይጥራሉ፣ የሶቭየት ኅብረትን መፈራረስ ድላቸው አድርገው ያከብራሉ፣ ሆንግ ኮንግ ከቻይና እንድትገነጠል ይጥራሉ፤ በዚያው አንፃር እነፒዬርቶ ሪኮ፣ ፓናማ፣ ሐዋዪ በራሳቸው በቅኝ መያዝን አያወሱም፤  በአጠቃላይ የአገራቸውን ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለአገሮቻቸው ጥቅሞች ቅድሚያ ይሰጣሉ።

ያለፈ የጥፋት ታሪካችንን ለትምህርት እናስታውስ፤ ጠባብ አስተሳሰብ የነበራቸው  ራስ ሚካኤል ስሑል በተሰጣቸው የመንግሥት አደራ ላይ እምነት በማጉደል ማዕከላዊ መንግሥት በማዳከም ዘመነመሳፍንትን የጀመሩ ሲሆን ፣ የየጁ ራሶች ደግሞ የግል ሥልጣን የማግኘት ሕልም እንጂ የአገሪቷ  በመሳፍንት ተከፋፍሎ መዳከም በግል ሥልጣናቸው ላይ ሲያተኩሩ የመከፋፈሉ ዘመን ዘመን ተራዝሞ ያስከተለው መዘዝ የውጭ ወራሪዎች  ከኤርትራ እስከሶማሊያ ድረስ ባሉት አካባቢዎች ላይ መረባቸውን ለመዘርጋት አስቻላቸው።  ያሁኖቹ ጠባብ  ፖሊቲከኞችሞ ወያኔ የከፈተችውን የጎጥ አደረጃጀት በመከተል ከ300 ዓመታት በፊት እንደነበረው ዘመነ መሳፍንት እርስበርሳቸው በመሻኮት ለግል ወይም ለቡድን ሥልጣን ሲሮጡ የተጠቀሱት የጋራ የአገር ጉዳዮች ትኩረት አጥተው ከላይ እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ በባህር ጠረፍ ግዛቶች በውጭ ተጠቃሚዎች እጅ እንደወደቁ ሁሉ ዛሬም በጎጥ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለምሳሌ የባህር በርን በመሳሰሉ የጋራ የአገር ጉዳዮች ላይ እንዳናተኩር አድርጎናል። በዘር ዜግነት መስጠትና በዘር ማካለልን ዓላማ አድርጎ መቀጠል ዲሞክራሲን መተግበር ወይም ሰብአዊ መብቶችን ማክበር ሳይሆን ታጥቦ ጭቃ እንደሚባለው ከአርባ ዓመታት በላይ ስንኮንነው የቆየነውን አሁንም በብሔር-ብሔረሰብ ጎራ እንድንለያይና እርበርስ  የኋልዮስ ስንጓተት በእንቅርት ላይ ጆሮደግፍ በቡሀ ላይ ቆረቆር እንደሚባለው ሰፊው ሕዝባችን በድህነት ላይ ድህነት እየተጨምረ የባንቱስታን አፓርታይድ ሥርዓትን ማዳበር የ21ኛው መቶ ክፍለዘመን አስተሳሰብ ሊሆን አይችልም።

አገርን ማስተዳደር እንደፈረስ ጉግስ ወይም ገና ጨዋታ ቀላል ጉዳይ የሚመስላቸው ኃላፊነት የማይሰማቸው የዋህ ግለኞችና ወገኖቻቸውን ክደው አገርን ሲያጠፉ የነበሩ ባንዶችም በየዘመኑ እንደነበሩ ሁሉ ዝንታለም ተከባብረው የኖሩ ወገኖቻችን እንዲጣሉ ሰው-ሠራሽ ግጭቶችን ለመፍጠር ዛሬም በብዙ የእገራችን ክፍሎች የጥፋት ዘመቻዎችና የእኩይ ተግባር ቅጥረኞች እንዳሉ በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ታይተዋል። የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ለማስከበር ዘር ሳይለዩ በመተማ፣ በአድዋ፣ በማይጨው፣ በዋርዴር፣ ካራማራ፣. . . ወዘተ ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩላቸውን አያቶቻቸውን ረስተው በመንደር ደረጃ ራሳቸውን የሚወስኑ ወገኖች መከሠት ለአገራችን ድህነት እንጅ እድገትን ሊያመጣ አይችልም። የነብርና የኢትዮጵያዊ ዝንጉርጉርነት ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን የዛሬዎቹ ጠባቦች ከመፈጠራቸው ከብዙ ምእተ ዓመታት በፊት የሚታወቅ ሲሆን፣ የእኛ ኢትዮጵያ የዓለም ዘር ምንጭ መሆኗንና እኛም ብዙ መሆናችን የሚያኮራና የሚያስመካ መሆኑን እነዚሁ ምሁራን መረዳት አልቻሉም፤ ዓለም ያወቀውን ጥንታዊ የጋራ ታሪካችንን ተረት ተረት ነው በማለት የአገርን ኅልውና ይክዳሉ፤ ታሪክ ሲያጡ በድርሰት ላይ ተመርኩዘው ሐውልት ይሠራሉ፤ ያውም ጀግንነትንና የአገርንና የወገንን ክብር የሚያሳይ ሳይሆን ጥላቻን የሚያስተምር ሐውልት፤ ገንቢ ነገሮችን በማዳበር ፋንታ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያራርቁ ስድቦችን ያስተምራሉ፤ ይህ ተግባር ራሱ ወገንን የሚያኮራ ሳይህን የሚያሳፍር ነው። አንዱ ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ነፃነት መስዋዕት የመሆን ባህል ካለው ቤተሰብ በመምጣቱ ቢኮራ ወግ ነው፤ ሌላውም ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለአገሩ በተመሣሣይ ሁኔታ አኩሪ ባህል አለኝ ቢል ወግ ነው፤ ምክንያቱም አኩሪ ታሪክ ያለው በዚያ በአኩሪ ታሪኩ ይኮራልና። የኩራት አንዱን ትልቁ መሠረት በራስ መተማመን ነው፤ በራስ መተማመን ደግሞ የሚመጣው ለሰው ወይም ለአገር መልካም ሥራ በመሥራት ነው፤ በሕዝብ አመራር ደግሞ ለሰው ልጅ ያለአድልዎ፤ በፍትሕ፤ በእኩልነት ዲሞክራሲን በመተግበር የሚታይ ነው። በአንፃሩ በሰው ላይ ግፍ በመፈጸም፣ ንብረት በመዝረፍ፣ ሰው በመግደል ባህል ውስጥ ያለፈ የአእምሮ ሰላም በማግኘት ፋንታ የሚያፍርበትና  የሚሰጋበት  ተግባር ስለሚኖረው የመንፈስ እርካታም ሆነ እርጋታ  አይኖረውም፤ ስለዚህ ሙሉነት አይሰማውም፤ ሁልጊዜም በኅብረተሰቡ ዘንድ የበታችነት ይሰማዋል። ለጥፋት ሳይሆን ያለንን ኃይል ለልማት በማስተባበር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኢትዮጵያ የጋራ ግንባታ የሚጠቅም መልካም ሥራ በመሥራት ብንሽቀዳደም አገራችን ሌሎች የበለፀጉ አገሮች የደረሱበት ደረጃ ለመድርስ የሚያስችልን ባህል የመገንባት ተግባር ስለሚሆን ሁላችንንም እኩል ሊያኮራን ይችላል። ለዚህ ነው አሜሪካኖች ያጠፉ የቀድሞ መሪዎቻቸውን እንኳ  እያከበሩ መልካም በሠሩት ላይ እየጨመሩ ለምሳሌ እነ ጅዎርጅ ዋሽንግተን፣ ቶማስ ጀፈርሰን፣ አብርሃም ሊንከን፣ ጆን አደምስ፣ ጀምስ ማድሰን . . . ወዘተ የአባቶቻችን ቅርስ እንዲጠበቅ በማለት በነሱ ሥራ ላይ እየገነቡ አሁን የደረሱበት እድገት ደረጃ ላይ የደረሱት። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወታደር ከአስጨረሰው የእርስ በርስ ጦርነታቸው  እንኳ መጥፎውን ሳይሆን መልካም ገጽታውን ብቻ ያወራሉ፤ በተሽነፉበት የቪየትናም ጦርነት የተሳተፉትን ጀግኖች በማለት ብሔራዊ ገመናቸውን ይሸፍናሉ። በ1777 የወጣው መሪ ሕግ/ሕገመንግሥት/ ብዙ ሳይለወጥ ነው እየተሻሻለ ሥራ ላይ የቆየው፤ መሪዎችን ለወጡ እንጅ በሥርዓተ-አልበኝነት  መንግሥት  አፍርሰው ሌላ  መንግሥት  አልፈጠሩም። አኛስ ከነሱ ያነሰ ነወይ የምናስበው? ለነሱ የሠራው እውነት ለኛ መሥራት ለምን ያቅተዋል? መልሱ እንደዝንጀሮ ለግልና ለቡድን ብቻ የምናስብ ካልሆነ በስተቀር እኛም እንደነሱ አእምሮ ስላለን እንደነሱ መሆን አያቅተንም ነው።

ዲሞክራሲ ከመታወቁ በፊት አገራችን ፍትሐዊ አመራር ነበራት፤ ሰብአዊ መብት በዓለም ከመታወቁ በፊት አገራችን የእምነት ስደተኞችን  በጥገኝነት መቀበል ብቻ ሳይሆን መብታቸውን በኃይል ጭምር አስከብራላቸዋለች። ዛሬ የዲሞክራሲ ጽንሰ-ሐሳብ ዓለም- አቀፋዊ ነው፤ ሰብአዊነት ነው፤ ብሔርተኝነት ግን ባህላችን አይደለም፤ ጠባብና ድውይ አስተሳሰብ ነው፤ ወንዝም አያሽሳግርም፤ የትልቅነት አስተሳሰብ ሳይሆን የስግብግብነት፣ የትንሽነት መገለጫ ስለሆነ በሰፊው ሕዝባችን ዘንድ የተናቀና የተጠላ ነው። በብሔርተኝነት የተደራጀና ለተወሰነ ብሔር-ብሔረሰብ ልዕልና የሚታገል ድርጅት የዚያን የሚታገልለትን ብሔር-ብሔረሰብ ጥቅም ስለሚያስቀድም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሌሎችን ብሔር-ብሔረሰቦች ጥቅም የመፃረር ተግባር ይፈጽማል፤ ለምሳሌ ኦሮሚያ በሚባለው ክልል ውስጥ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎች በራሳቸው ቋንቋ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት አይፈቀድላቸውም፤ የኦሮምኛን ልዕልና ለመጠበቅ ሲባል ሌሎች ዜጎች በሙሉ ይዳመጣሉ ማለት ነው፤ ይህ ድርጊት የዲሞክራሲን ጽንሰ-ሐሳብ የሚፃረርና ለሰዎች እኩልነት ያልቆመ የመንግሥት አደረጃጀት ነው።

በአንድ የታሪክ ዘመን በአገራችን የመኪና መንገድ አይሠራብን፣ ከሌሎች አካባቢዎች የሚያገናኝ ድልድይም አይገንባብን በማለት የተቃወሙ ወገኖች መኖራቸው ይታወሳል፤ ዛሬ ደግሞ ከብሔረሰባችን ውጭ የሆነ ቋንቋ ያውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚናገረውን ብሔራዊ ቋንቋ ማጣጣል የሥልጣኔ ሳይሆን የኋላቀርነት አባዜ መሆኑን መረዳት አያስቸግርም። ዛሬ ዓለም ጥቂት ቋንቋዎችን እየተናገረችና ወደአንድ ቤተሰብነት እያመራች እያለ በጎሣ ፖሊቲካ መናጥ ጥቅሙ ለኢትዮጵያውያን ሳይሆን የአገራችንን የተፈጥሮ ሀብቶች ለመዘረፍ ለሚፈልጉ የውጭ ባላንጣዎቻችን ተከፋፍሎ መውደቅ መሆኑን ማስተዋል ይገባል። በጠባብ ብሔርተኝነት፣ ቋንቋንና ጥቃቅን ልዩነቶችን ሰበብ የሚያደርጉ ጽንፈኞች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ብሔራዊ ልዕልናችንን ለነዚሁ የውጭ ባላንጣዎች በመሸጥ የማገልገል ሚና ይጫወታሉ። መላው አውሮፓ በጭለማ ውስጥ በነበረ ጊዜ የራሷን ፊደል ቀርጻ የሥልጣኔ ቀንዲል ያበረከተች አገር ዜጋ መሆን፣ ዛሬ አሜረካኖች ከሚጠቀሙበት የእንግሊዝኛ ቋንቋ በፊት አማርኛ በራሱ ፊደልና የሥነጽሑፍ ታሪክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ መቆየቱ እንደ ኢትዮጵያውያን ወይም እንደአፍሪቃውያን ሊያኮራን ሲገባ፣ የጭቆናና የጥላቻ ሥዕል ሲሳልበት ሀገራችንን ለመከፋፈል ጠላቶቻችን የሚያበራቱት ጉዳይ መሆኑን ቅን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊረዳው ይገባዋል። በመሠረቱ ሊታወቅ የሚገባው ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ሐዲያ፣ ሲዳማ፣ ከምባታ፣ ወዘተ የሚባሉ መለያዎች ከመፈጠራቸው በፊት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ ትውልድ ሲበዛና ሲባዛ ዘር ተቀያይጦ አሁን በቋንቋ የሚለዩትን ማኅበረሰቦች ቢፈጥር  ይዘረዝራቸዋል እንጂ ኢትዮጵያዊ ማንነታችውን አያጠፋውም። ኦሮሞኛ፣ ከምባትኛ፣ ወላይትኛ፣ ጉራግኛ፣. . . ወዘተ የየራሳቸው ትርክት የሚኖራቸው ሲሆን በተመሣሣይ ሁኔታ አማርኛ ከግዕዝ፣ ከሳባ፣ ከትግርኛ፣ ከጽርእ፣ ከአረብኛ፣ ከአርጎባ፣  ከአገውኛ፣ ከጉራግኛ፣ ከኦሮምኛ፣እና ከሌሎች የአገር ውስጥ  ቋንቋዎች ተከልሶ በጉራማይሌነት የዳበረ ቋንቋ ነው፡፡  በዘመኑ ጉራማይሌ (lingua franca) ይባል የነበረውን  አማርኛ ተናጋሪው ወገን ቋንቋውን ሲናገር ከነበረው ከአያት ከቅም አያቱ ሲወርድ ሲዋረድ የተገኘ ሕዝብ ስለሆነ አማራ ተባለ እንጅ አማራ ከዘር ምንጭ የተገኘ የሕዝብ መለያ አይደለም።በዚህም የተነሣ አማራ የተለየ መልክ የለውም፤ ሁሉም ዓይነት ቀለም ያለው በአብዛኛው አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ነው፤ አፈጣጠሩ ራሱ ኢትዮጵያዊ (የብዙዎች ውሁድ) በመሆኑ ከኢትዮጵያውያን  ቅይጥ ታሪካዊ እድገት ጋር የተያያዘ ነው። ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የዛጉዌ ሥርወ-መንግሥት አማርኛን በብሔራዊ ቋንቋነት የተቀበለው የአገውኛ ቋንቋ የነበረው መሆኑን አጥቶት ሳይሆን አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚግባባበት አማርኛ መሆኑን ስለሚያውቅ የሕዝቡን ለሕዝብ ከማድረግ የተሻለ አማራጭ ስላልነበረው ነበር።  እንደማንኛውም ቋንቋ አማርኛ የባህልና ቲክኖሎጂ ነጸብራቅ በመሆኑ  ከአረብኛ፣ ከጣሊያንኛ፣ ከፈረንሳይ፣ ከእንግሊዝኛ የወሰድናቸው ቃላትም (ለምሳሌ ቤት፣ ሱቅ፣ ቦርሳ፣ ኩባያ፣ ሜትር፣  መኪና፣ ሬዲዎ፣ ቴሌቪዝን፣ ቪዲዮ፣ ዲፕሎማሲ፣. . . ወዘተ) በተውሶ ገብተው የቋንቋው አካል መሆን ባህላቸው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የዳበረላቸውን ኅብረተሰቦች ቋንቋ መስፋፋት ለመቆጣጠር የማይቻል  እውነታ መሆኑን ያሳያል፡፡ የአንድ አገር ባህል እያደገ ሲሄድ ብዙ ቋንቋዎች በጥቂቶች እየተዋጡ መሄድ የሥልጣኔና የቴክኖሎጂ እድገት እውነታ ስለሆነ ይህን ለመቆጣጠር መፈለግ፣ የዓለም-አቀፍ የማኅበራዊ እድገትን ሕግ ወይም ተፈጥሮን ለመቃውም እንደመቃጣት ይቆጠራል።

መፍት

ዛሬ በኃያልነትና በብልጽግና የሚታወቁት አገሮች እነአሪስቶትልንና እነ ሊዮናርዶ ዳቨንሲን፣ ጀምስ ዋትን፣ ቶማስ ኤዲሰንን እያደነቁና ከነሱ እየተማሩ፣ የአባት መሪዎቻቸውን መልካም ቅርስ (legacies of nation building forefathers) በማዳበር እያደጉ መሄዳቸውን ገና የሁለተኛ ደረጃን ትምህርት ያልጨርሰ ሁሉ እንደሚያውቀው ይታመናል። ዘመናት እየታደሱ ሲሄዱ የድሮውን ጎጅ ነገር እየተዉ መልካም መልካሙን ማዳበር የእድገት መንገድ ነው። (ኮሚኒዝምን ወደጎን ትተን) እነቼኮቫራ፣ እነሆቺሚን፣ እነማኦ፣ እነሌኒን፣ እነ ቶማስ ጀፈርሰን፣ እነ ማህተማ ጋንዲ፣ እነ ኔልሰን ማንዴላ፣ …ወዘተ የነበራቸውን ርዕዮት ብንመረምረው ታይቶና ተደርጎ የማይታወቅ የግል ጥቅማቸውን መስዋዕት አድርገው ለሰው ልጆች እኩልነትና ለትልቁ የአገራዊ አርነት ጎህ ቀዳጅ ፍልስፍና እንደነበራቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡

በአንፃሩ ጠባቦች እንኳን አዲስ አገራዊ ጎህ ሊቀዱ ቀርቶ በተቀደደው ጎህ መብራትም መጠቀም አልቻሉም፤ በዜጎች መከራ ላይ ትርፍ ለማትረፍ የሚሹ ተዋናዮችም የዕለት ጥቅም ያገኙ እንደሆን እንጂ ለሕዝብ የሚያስገኙት የዘለቄታ ጥቅም ወይም የሚያተርፉት የሥነልቡና ትርፍ አላገኙም፡፡ በጎጠኝነት ወደኋላ መጓተት ለማንኛውም የሕዝብ ወገን የዘለቄታ ጥቅም እንዳላስገኘ ከዘመነመሳፍንት ጀምሮ ታይቷል፤ የትግሬው ራስ ሚካኤል ስሑል ጎንደር በሚገኘው የኢትዮጵያ ቤተመንግሥት አደራና ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ሳለ  የተሰጣቸውን ኃላፊነት አለአግባብ በመጠቀም ከ1769 ዓም ጀምሮ ዘመነ መሳፍንትን በመክፈት 19 ንጉሦችን ሲያነግሡና ሲሽሩ የየጁ ኦሮሞች ደግሞ በመሳፍንት በተከፋፈለችው አገር በባላባትነት ፈላጭ ቆራጭ ሆነው አፄ ቴዎድሮስ እስከተነሱበት 1855 ዓም ድረሰ ማዕከላዊ መንግሥትንና አገሪቷን አዳክመው መቆየታቸውን ታሪክ ያስታውሰዋል፤ ከዚያ የተረፈው ኋላቀርነትና ድህነት ብቻ ነበር። ዛሬስ? ዓለም እንደዚህ የደረሰበትን እድገት ማወቅ የሚገባቸው የ21ኛ ክፍለዘመን አንዳንድ ፖሊቲከኞቻችን እልፍኝ ሲሏቸው ጋጥ የሚመርጡ ስለሆነ የግል ጥቅማቸውን እንጅ አገር በጋራ ስታድግ ለወገኖቻቸውና ለራሳቸውም አስተማማኝ የጋራ ጥቅም ማስገኘት እንደምትችል ማየት አልቻሉም፤ ሆኖም ምንም ፖሊቲካ ይውደቅ ይነሳ የፈለገው መንግሥት ይቀያየር የሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት የኑሮ መሻሻል ስለሆነ የዚህ በፍትሐዊ መንገድ መተግበር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በፍልስፍና እንደዳበሩት አገሮች የፖሊቲካ ድርጅቶች ውድድር መሆን ያለበት የተፈጥሮ ሀብታችንና የሰው ኃይላችንን ከባእድ ምዝበራ አድነን በጋራ ለመጠቀም የሚያሽችሉ የተሻሉ አማራጮችን በማቅረብ መወዳደር ቢሆን የት በደረስን?

ያለፈን ታሪክ ማንሳት ለመማርና የተሻለ ሥራ ለመሥራት ብቻ ነው። ዶናልድ ሌቪን የሚባሉ አሜሪካዊ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ኑኖ (sociology) ላይ ጥናት ሲያደርጉ የነበሩ ምሁር በአንድ ወቅት ሲናገሩ ኢትዮጵያውያን የሚያኮራችሁ ባህል እያላችሁ የኮሚኒስት ምስሎችንና ሐውልቶችን መሠራታችሁ ተገቢ አይመስለኝም ይሉ ነበር። ፈረንጆችን የመልካም ምሳሌዎች ብቻ እያደረን ራሳችንን ዝቅ አድርገነዋል፤ እነሊዎናርዶ ዳቨንሲ ከመወለዳቸው ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ቅዱስ የሚባሉትን አርቲስት ያሬድ በኋላም እንድ ለማ ጉያ አፈወርቅ ተክሌ፣ ፀጋዬ ገ/መድህን. . . ሙያ ለልጆቻችን ብናስተምር፣ ዘርዓ ያዕቆብ፣ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ ምኒልክ2ኛ፣ ሀ/ጊዮርጊስ ቢነግዴ፣ እምሩ ኃ/ሥላሴ፣ የፊታውራሪ አባ ዶዮ . . . ወዘተ የመሳሰሉትን በዘመናቸው ተራማጅ ወይም በሳል ከነበሩት አባት የሀገር መሪዎች ርዕዮትና ከታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች በመማር በነሱ መልካም ሥራ ላይ ያሉንን ሰብአዊ እሴቶቻችንን ተጠቅመን እድገታችንን በመገንባት እያሻሻልን ወደፊት በመራመድ  አገራችንን በጋራ ልንታደግ እንችላለን፤ ሰላምና ፍቀር ሲኖር የአገራችን ብልፅግና ወሰን አይኖረውም። ድሮ ፖሊስና ፍርድቤት ከመቋቋቸው በፊት የአገር ሰላም የሚከበረው በአገር ሽማግሌዎች ነበር፤ ዛሬም በዋና ዋና ከተሞች በሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና በአስተዋይ ምሁራን የሚደረጉ የሰላም ውይይቶች እጅግ የሚያኮሩ ዜጎች እንዳሉን ያሳያል። በነዚህ እሴቶች መጠቀም ብልኅነት ነው፡፡

ከዓላም እድገት ጎን ለመሰለፍ የአገራችን ሕዝብ በለመደው ብሔራዊ ቋንቋ እየተግባባ ማንኛውም ማኅበረሰብ ባህሉንና ቋንቋውን አንዳች በሕግ የታሠረ ገደብ ሳይደረግበት በነፃነት ከመንቀሳቀስና ከመሥራት ጋር የመማርና ማስተማር ተግባር ቢፈጸም የማንኛውም ማኅበረሰብ ባህል ሲያድግ ተዛማጅ ቋንቋውም አብሮ የማደግ ዕድሉን ማንም ሊገድበው እንደማይችል የማኅበራዊ ሳይንስ ሕግ መሆኑን በመረዳት ይልቅስ ያሁኑ ትውልድ የጋራ እድገት መሠረቶች ላይ ቢያተኩር ለአገራችን የጋራ ልማት ጠቃሚ ይሆናል። ከእድገት መሠረቶች አንዱ ነፃ እንቅስቃሴና ሙሉ የግለሰብ መብቶች መከበር ናቸው። ማንኛውም ወገናችን እንደልቡ ተንቀሳቅሶ፣ በማኅበራዊውም ሆነ በምጣኔ ሀብት በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍለ-ሀገር ራሱንም ሆነ አገር-ወገኑን ለመጥቀም የሚችል መሆኑን የዘመኑ ተጨባጭ ሁኔታ ያረጋግጣል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፉውንና ደጉን እያወቀ በጋራ አብሮ ለመኖር በሚያየው ራእይ በከፍተኛ ትዕግሥትና የመቻቻልን ባህል ከመንግሥት በላይ እየተገበረ መገኘቱ ነው። ይህን እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሕዝብ የሚለያይ ኃይል ሊኖር አይችልም፤ ሰይጣን እንኳ ቢሞክር ለጊዜው ጉዳት ሊያደርስ ይችል እንደሆን እንጂ አይሆንለትም። ጎጠኞች ተግባራቸው የኋላ ኋላ ራሳቸውንም እንደሚጎዳቸው ስላልተረዱት ካላስፈላጊ መስዋዕት በኋላ ፈረንጆች እንደሚሉት “learning the hard way”  ከጥፋታቸው መማራቸው አይቀርም፤ ሆኖም የሚያሳዝነው በዚያው መጠን ያለንበት ኅብረተሰብ እድገት ወደኋላ ነው። በአንፃሩ ዓለም በማያቋርጥ እድገት ወደፊት ይራመዳል፤ ካለፉት ጥፋቶችም ሆነ ልማቶች በመማር፣ ለስሜት ሳይሆን ለአገር ልዕልናና ብልፅግና፣ ለሥልጣን ብቻ ሳይሆን  ለሰው ልጆች ሰብአዊ መብቶችን በእኩልነት ለሚያስተገብር  መርህ ተገዝተን፣ በሕዝብ ላይ ተፅእኖ ማድረግ ሳይሆን የሕዝብን ፈቃድ ለመፈጸም፣ ሕዝብን ለማለያየት ሳይሆን ለማቀራረብ፣ በተንኮል ሕዝብን በማሳሳት አዳዲስ ግጭቶችን ለመጫር ሳይሆን ለሕዝብ ቅን በመሆን ለሰላምና ለጋራ እድገት፣ ለጠብ ሳይሆን ለይቅርታ፣ ለአንድ ወገን ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ሁሉ መብትና ለጋራ ጥቅሞች ወይም ለጋራ ልማቶች የምንተጋ ቢሆን ሕዝባችን መልካም ጉርብትናን ስለሚያውቅበት በሰላም አብሮ በመኖር አብሮ አገሩን ማልማት ይችላል።

የብሔር-ብሔረሰብ ርዕዮት  በኮሚኒስቶች ተጀምሮ በዚያው በመሥራቾቹ አገር ለብዙ ዓመታት ሲታመም ቆይቶ ከሞተ 30 ያስቆጠረ ሲሆን፣ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደተባለው ወያኔዎች አገርን ከፋፍሎ ለመግዛትና ለመዝረፍ አገሪቷን በብሔር-ብሔረሰብ ከፋፍለውና አካለው የሞተውን ርዕዮት ከ27 ዓመታት በላይ ተጠቀሙበት፤ አሁንም የበሉትን እየተፉ በኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት እንዳይፈጸም የማጋጫት ፕሮጀክታቸውን ዘርግተው ቅጥረኞችን በየመንደሩ በማዝመት ከ250 ዓመታት በፊት ገዳ ይጠቀምበት ከነበረው የመስፋፋት መንገድ ጋር በሚመሳሰል ዘመቻ ቅጥረኞችን በየመንደሩ በማዝመት ለዝርፊያ፣ ለሽብርና ሰላማዊ ነዋሪዎችን በማሳደድ ጥፋት እየፈጸሙ ቆይተዋል፣ ይህ ድርጊት በወቅቱና በበቂ ሁኒታ  ካልተገታ በአገር ላይ መረጋጋትን አይፈጥርም፤ መረጋጋት በሌለበት ሁኒታ ደግሞ የሕዝብ ሰላም ስለሚታቀብ በምርታማነት ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል፤ ባልተረጋጋ ሁኔታ ወደምርጫ መሄድም ፍትሐዊ ውጤት ሊያመጣ አይችልም፤ “መካር የሌለው ንጉሥ…” እንደሚባለው። ሁለተኛ በመንግሥት ላይ እምነት ማጣትን ከሚያመለክቱ ነገሮች በብሔር-ብሔረሰብ ተደራጅተው የማያውቁ አዳዲስ ድርጅቶች እየጨመሩ መምጣትና በየቦታው በብሔር-ብሔረሰብ የመካለል አዳዲስ ጥያቄዎች መከሠት ናቸው።  ስለሆነም በየከተሞች በሃይማኖት መሪዎች፣ በሽማግሌዎችና በምሁራን ከሚደረጉ ውይይቶች ባሻገር በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ወደሕዝቡ ዘልቆ የሚገባ በመዋቅር የታቀፈ የእርቅና የሰላም ሥራ ሊሠራ ይገባል።  እንዲሁም አገራችን የውጭ ጠላት ሳይኖርባት ብሔራዊ ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት እያላት ወንጀለኞችን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣  በአገር ውስጥ እየተፈጠሩ የሚገኙትን የፀጥታ ችግሮች እንደመንግሥት በበቂ ሁኔታ በወቅቱ እንዳልተቆጣጠረ በየጊዜው የታየ ክስተት ስለሆነ ሕዝቡ ከዳር እስከዳር በመንግሥት ላይ እምነቱ እየቀነሰ ስለመጣ ከወንበር በፊት አገርን በማስቀደም የምርጫው ጊዜ ለ 6 ወራት ያህል ተራዝሞ ይህ በወቅቱ ታርሞ በመላው አገሪቷ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያለው መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።

ተፈራ ድንበሩ

——————/////——————-