
ክራይሲስ ግሩፕ የተሰኘው ተቋም ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት [2020] ግጭት ሊበረታባቸው ከሚችሉ አገራት መካከል አንዷ ልትሆን ትችላለች ሲል ይፋ አድረገ።
በተለያዩ የዓለማችን አገራት ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን የሚከታተለው ተቋሙ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት 2020 ዓ.ም ግጭት እጅግ ገዝፎ ሊታይባቸው ይችላል ያላቸውን 10 አገራት ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ሦስተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።
• የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደቤታቸው ለመላክ ለምን ወሰነ?
• ህወሓት፡ ሃገራዊ ምርጫ የሚራዘም ከሆነ ትግራይ የራሷን ምርጫ ታካሂዳለች
በተቋሙ ዝርዝር አናት ላይ የምትገኘው አፍጋኒስታን ስትሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ተባብሶ የቀጠለው ግጭት በሚመጣው ዓመትም [2020] የሚያባራ አይመስልም ይላል።
በሁለተኛ ደረጃ ላይ ደግሞ የመን የምትገኝ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታትም የመን የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ትኩረት የምትሻ ሃገር ሲል ማወጁ አይዘነጋም።
የየመን ጦርነት ቢያንስ የ100 ሺህ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያም የአረቡ ዓለም ደሃ አገር የሆነችው የመን ረሃብ እያጠቃት ይገኛል።
ኢትዮጵያ
2020 ለኢትዮጵያ ተስፋና ስጋት የደቀነ ዓመት ሲል ‘ክራይሲስ ግሩፕ’ ይገልፀዋል። በሕዝብ ብዛት ምሥራቅ አፍሪካን የምትመራው የቀጣናው ‘ኃያል’ አገር ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መምጣት በኋላ ብዙ ለውጦችን አይታለች።
ሚያዝያ 2010 ዓ.ም ሥልጣን የጨበጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የፖለቲካ ምሕዳሩ እንዲከፈት ብዙ ተራምደዋል ይላል የተቋሙ ዘገባ።
አልፎም ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ለዓመታት የዘለቀውን ጠላትነት ማስወገድ መቻላቸው፣ የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታታቸው፣ ስደት ላይ የነበሩ ተቃዋሚ ኃይሎች በነፃነት አገር ቤት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀዳቸው እና ተቋማዊ ለውጦችን ማካሄዳቸው መልካም እመርታ ነው ሲል ተቋሙ ይዘረዝራል።
በአገር ቤት ከተሰጣቸው እውቅና ባለፈም በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ክብር ተሰጥቷቸዋል ሲል የኖቤል የሰላም ተሸላሚነታቸውን ያነሳል።
ነገር ግን ከፊታቸው ከባድ ፈተና ተደቅኗል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መምጣት በፊት የነበሩ ተቃውሞዎች ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ መጎሳቆል የወለዳቸው ብቻ ሳይሆኑ ብሔር ተኮር ይዘት ያላቸው ናቸው፤ በተለይ ደግሞ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ ከእሳቸው ቀደም ብሎ በነበረው ሥርዓት መዋቅር ላይ ለውጥ ያካሄዱበት መንገድ ብሔር ተኮር ፖለቲካ የበለጠ እንዲያብብ እና ማዕከላዊው መንግሥት እንዲዳከም ዕድል ፈጥሯል ሲል ተቋሙ ትዝብቱን ያስቀምጣል።
የብሔር መልክ ያላቸው ግጭቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸው እንዲጠፋ ምክንያት ሲሆን ሚሊዮኖች እንዲፈናቀሉ አድርጓል። አልፎም በክልሎች መካከል መቃቃር እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል ብሏል ሪፖርቱ።
ከጥቂት ወራት በኋላ እንደሚከናወን የሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ ግጭት እንዲበረታ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተቋሙ ስጋቱን ገልጿል።
ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት አድርጎ የሚጠቅሰው ዕጩዎች ድምፅ ለማግኘት በሚያደርጉት ግብግብ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፉክክር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚለው አስተሳሰብ ነው።
አገሪቱ በይፋ የምትተዳደርበት ብሔርን የተንተራሰ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ሌላኛው ለግጭት መፋፋም እንደ ቤንዚን ሊሆን የሚችል ነው ባይ ነው ተቋሙ።
ነገር ግን የሥርዓቱ ደጋፊዎች አሁን ያለው ፌደራላዊ አወቃቀር እንደ ኢትዮጵያ ላለ የብሔር ስብጥሩ ለገዘፈበት አገር አዋጭ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። የሥርዓቱ አውጋዦች ደግሞ ፌዴራሊዝም አንድነት የሚባለውን ሃሳብ የሚያፈርስና ከዘመኑ ጋር የማይሄድ ነው ሲሉ ይተቹታል።
ኢሕአዴግን አክስመው አንድ ሃገራዊ ፓርቲ ያቋቋሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በሚቀጥለው ምርጫ ከብሔር ተኮር ፌዴራሊስቶች ከፍተኛ ፉክክር እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል።
• የትግራይና የፌደራል መንግሥቱ ግንኙነት በጣም አሳሳቢ ነው- ዶ/ር አብረሃም ተከስተ
ኢትዮጵያ እያለፈችበት ያለው ለውጥ ትልቅ ተስፋ ያለውና ድጋፍ የሚሻ ቢሆንም ስጋት የተጫጫነው መሆኑ ሊካድ አይገባውም ይላል ተቋሙ በሪፖርቱ አክሎም አንዳንዶች አገሪቱ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነች ስጋታቸውን እንደሚገልጹ አመልክቷል።
ክሎም የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ ኃያል አገራት ኢትዮጵያዊያን ፖለቲከኞች ግጭት ቀሳቃሽ ንግግሮችን ከማሰማት እንዲቆጠቡ ግፊት ማድረግ አለባቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አገሪቱን ይታደጓት ዘንድም የገንዘብ እርዳታ ማድረግ ይገባቸዋል ሲል ክራይሲስ ግሩፕ አቋሙን ያንፀባርቋል።
ሎሎች በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ሃገራትና ቀጣናዎች ቡርኪናፋሶ፣ ሊቢያ፣ አሜሪካ-እስራኤል-ኢራን እና የፋርስ ባሕረ-ሰላጤ በጋራ፣ አሜሪካ-ከሰሜን ኮሪያ፣ ካሽሚር፣ ቬንዝዌላና ዩክሬን ናቸው።