ዳግማይ ትን ሣ ኤ

ኢሕአፓን በወጉ ለመረዳትና መሠረቱን በሚገባ ለማወቅ የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ከ1950ዎቹ ጀምሮ መመልከት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገራት አንዷ በመሆኗ በአፍሪካና ከአፍሪካ ውጭ ያሉ አገሮች ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

በ1950ዎቹና 60ዎቹ በአፍሪካ ውስጥ ከቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት የሚደረግ እንቅስቃሴና ትግል፣ በሌሎች አገሮች ደግሞ በሶቪየት ኅብረት ተጀምሮ ሁሉም አህጉሮች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ የሶሻሊስት/ኮምኒስት እንቅስቃሴና አብዮት መላውን ዓለም ያናወጠበት ወቅት ነበር። ይህ ዓለምአቀፋዊ ሁኔታም በተለያየ መልኩ የኢትዮጵያን ሁኔታም ይነካካው ጀመር፣ ቀጥተኛ ተጽዕኖም አሳደረ።
ከፍተኛ ትምህርት የቀሰሙና በምዕራብ ሃገሮች ተምረው የተመለሱ የ1940፣ የ50ዎቹና የ60ዎቹ
ትውልዶች አገሪቱን ለምዕት-ዓመታት ተጭኗት የነበረው የፊውዳላዊ ሥርዓት ኢ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ አገዛዝ መቀጠሉና ያገሪቱን ቀጣይ ዕድል በማቀጨጩ ሥርዓቱ መለወጥ እንደሚገባው ተገነዘቡ።

የዳበረው ዓለም ቀርቶ በቅርብ ጊዜ ከአውሮጳውያን የቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡ አፍሪካውያን ጎረቤቶቻችን ወደፊት ሲራመዱ፣ ኢትዮጵያ ግን ባለችበት እንድትሄድ የሚያደርግ መሆኑን ሲያጠኑ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አመኑበት። የትውልድና የአመለካከት ልዩነት ይኑር እንጂ ትውልዶቹ በሀገሪቱ ውስጥ ለውጥ በማምጣት አስፈላጊነት ላይ ልዩነት አልነበራቸውም።

በየፊናቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ጀመሩ። በ1953 ዓ ም በመንግሥቱ ነዋይና በግርማሜ ነዋይ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝቡን ዓይን የከፈተ ፈር ቀዳጅ ነበር ቢባል ከሃቅ መራቅ አይሆንም። እንዲያውም “ያ ትውልድ” ተብሎ የሚታወቀውና በቀጠሉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ይዘት ላይ ተጽእኖ የፈጠረው የ60ዎቹ ትውልድ ላይም የነዋይ ወንድማማቾች የለውጥ ሙከራ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የወንድማማቾቹን የለውጥ ሙከራ በመደገፍ የተጀመረው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ
አመለካከቱ እየጎለበተ ከተራ እንቅስቃሴ ወደ አብዮታዊ አመለካከት አደገ። ከዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር በደሎች በመቃወም የጀመረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የአካባቢያዊና ዓለምአቀፋዊ ለውጦች ባሳደሩበት የለውጥ መንፈስ ጥያቄዎችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመውሰድ “መሬት ለአራሹ፣ የብሄረሰቦች መብት ይከበር፣ የኤርትራ ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ ይፈታ፣ የሃይማኖት እኩልነት ይከበር፣ የሠራተኞች መብት ይከበር፣ ድህነት ወንጀል አይደለም፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ… ወዘተ” የሚሉ የመጠቁ መፈክሮችን በማንሳት ትግሉን አጎለበተ። የማያቋርጥ በሚባል ደረጃ፣ ሰላማዊ ሰልፍ እየወጣ ንጉሡን እንደ መለኮት ይመለከት የነበረን የወላጆቻቸውን ትውልድ
አመለካከትንም ለመቀየር ቻለ። እኒህ እንሰግድላቸው የነበሩ ንጉሥ ለካስ ልክ እንደማንኛችንም ሰው ናቸው ማለት ተጀመረ፤ በአጠቃላይ ንጉሥ አይከሰስ፣ ሰማይ አይታረስ የሚለውን ብሂል የሰበረ ነበረ፡፡


ዴሞክራሲያ —————————- ታህሳስ ፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ————————————— ገፅ 2

ይህ በግልጽ መታየት የጀመረው የአመለካከት ለውጥ የገዥውን መደብ በጣም አደናገጠው። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የገዥው መደብ እጁን አጣጥፎ ቁጭ አላለም። የንጉሡና የደህንነት ኃይሎቻቸው “እቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” የሚል አመለካከታቸውን እያጠናከሩ መጡ። አንዳንድ ታይተው የማይታወቁ እርምጃዎችንም መውሰድ ጀመሩ። የተማሪዎቹ መሪዎች ናቸው ያሏቸውን እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ከትምህርት ገበታ አገዷቸው። የንጉሡም አመለካከት እያመረረ፣ እርምጃውም በሰልፍ ወቅት በዱላ ከመምታት አልፎ ወደ እስር ቤት በገፍ ማጎርና የተወሰኑትን ደግሞ ፍርድ ቤት በማቅረብ የዓመታት እስር ማስወሰን ተጀመረ። ትግሉ ግን አልበረደም፣ ይበልጥ ተጋጋለ እንጂ።
የተማሪው ማኅበር ተጠናክሮ ርዕዮተዓለማዊ ቅርጽ ተላበሰ።

የትግል መርሆው ሶሻሊዝም እንደሆነ
ለንጉሣዊው ሥርዓትና ለመላው ዓለም በግልጽ አሳወቀ። ይህ ለንጉሡና ለደጋፊያቸው ለአሜሪካ
መንግሥት አልዋጥ አላቸው። በዚህ ወቅት ነበር የንጉሡ መንግሥት የድህንነት አባላት የአዲስ አበባ
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረውን ጥላሁን ግዛውን በታህሣሥ ወር 1962 ዓ. ም
ከዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት ወጥቶ አፍንጮ በር አካባቢ ወደ ነበረው ቤቱ ሲሄድ በጥይት የገደሉት።
ጥላሁን ግዛው የንጉሡ ልጅ የልዑል መኮንን ባለቤት የሆኑት የልዕልት ሣራ ግዛው ወንድም እንደነበረ ልብ ይሏል። ምን ማለት ነው? ንጉሣዊው ሥርዓት ከውስጡም ቢሆን ተቃዋሚ ከተነሳበት ዝምድናም የማያቆመው መሆኑን ጥርት አድርጎ ያሳየ ሃቅ ነበር። የንጉሣዊው ሥርዓት እርምጃ እያየለ መሄድ ትግሉን አፋፋመው፣ ወደ ላቀ ደረጃም እንዲመጥቅ አደረገው።
በተማሪ ማኅበሩ ውስጥ ሰፊ ውይይት ተጀመረ። እስከዚያን ጊዜ ድረስ ይካሄድ በነበረው፣ በተማሪ
ማኅበር እንቅስቃሴ ደረጃ፣ ትግሉን መቀጠል ይቻላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ዋና የውይይት ርዕስ ሆነ፡፡
በተወሰነ ጊዜ በተደረጉ የቡድን ውይይቶችና ክርክሮች፣ በአብዛኛው የተማሪ እንቅስቃሴ ተሳታፊዎች መሃል የሃሳብ አንድነት ላይ ተደረስ። ሥርዓቱን ሥር-ነቀል በሆነ መንገድ ለመቀየር በተማሪ እንቅስቃሴ ደረጃ የትም መድረስ ስለማይቻል፣ ትግሉን ወደ ከፍተኛ የድርጅት ደረጃ ማሽጋገር ወቅታዊ ጥያቄ መሆኑም ስምምነት ላይ ተደረስ።

ድምዳሜውም ትግሉን ወደ አብዮት ማሸጋገር ያስፈልጋል የሚል ነበር። ይህ አመለካከት ነው የኢሕአፓና እንዲሁም ሌሎች ግራ ቀመስ ድርጅቶች እንዲመሠረቱ መሠረት የጣለው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርነት ድርጅት ብሎ በጀርመን አገር በሚያዝያ 1964 ዓ.ም የተቋቋመው በኋላ በ1967 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የተባለው በአፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በሶቪየት ኅብረት፣ አስፈላጊ የሆኑ የማደራጀት ተግባራት ካካሄደ በኋላ እንዲሁም ለትጥቅ ትግሉ መሥራች የሆነውን ቡድን ካዘጋጀ በኋላ በመስከረም 1966 ዓ. ም አገር ቤት ገባ። እንቅስቃሴውን የሚያካሂደው በኅቡዕ ስለነበር ከአባላቱ በስተቀር ይህን ክንውን የሚያውቅ
ግለሰብ ወይም ቡድን አልነበረም። ኢሕአፓን የመሠረተው ኃይል አገር ቤት ከመግባቱ ብዙም
ሳይቆይ ከውስጥ ሲብላላ የነበረው የሕዝቡ ብሶት በየካቲት 1966 ዓ. ም በአብዮት መልክ ፈነዳ።
ተድራጅቶና ታጥቆ የነበረው የወታደሩ ክፍልም አገዛዙን ጥሎ ስልጣን ላይ ወጣ፤ይህን ተከትሎም
ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሠረት ተጠየቀ፡፡
ይህ የሆነው ኢሕአፓ ራሱን በሕዝቡ ውስጥ በሚገባ አደራጅቶ በፕሮግራም የቀረጻቸውን ግቦች በሰላም መተርጎም ሳይጀምር ነበር። በወቅቱ ሕዝቡ የሚያውቀው የፓርቲውን ልሳን ዴሞክራሲያን ብቻ ነበር። ኢሕአፓ ለቆመለት ሕዝብ እራሱን ለማሳወቅና ይፋ ለማድረግ አዲስ አበባ ውስጥ ነሐሴ 26 ቀን 1967


ዴሞክራሲያ —————————- ታህሳስ ፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ————————————— ገፅ 3

ዓ.ም መለስተኛ ጉባዔውን በህቡዕ አካሄዶ፣ ፕሮግራሙን በስምንት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮሞኛ፣
ትግርኛ፣ ወላይታኛ፣ ሲዳማኛ እንዲሁም በእንግሊዝኛ፤ ፈረንሳይኛና ዓረብኛ) በዚያን ወቅት
ትልልቅ ይባሉ በነበሩ ከተማዎችና በህቡዕ በተጠናከረባቸው አካባቢዎች በአንድ ሌሊት፣
በማሰራጨት ራሱን አስተዋወቀ። ሲመሠረት ይዞት የወጣውና በመለስተኛ ጉባዔው ያፀደቀው ፕሮግራምም ከዚህ በታች ያሉትን መሠረታዊ ነጥቦችን የያዘ ነበር። ዋና ዋና ነጥቦቹም በወቅቱ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲነሱ የነበሩና ጥያቄዎችንም በሚገባ የሚያስተናግዱ ነበሩ። እነዚህ አታጋይ ነጥቦች፣ በደርግም ይሁን በጠባብ ብሄረተኛው ህወሓት እስካሁን ስላልተመለሱ አሁንም አታጋይ ጥያቄዎች ናቸው።
በ1964 ዓ. ም፣ በኋላም በ1967 ዓ ም በኢሕአፓ መለስተኛ ጉባዔ ላይ ተሻሽሎ የፀደቀው የኢሕአፓ የፖለቲካ ፕሮግራም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄዎችን ለማስተናገድና የአብዮቱ ግቦች ምን እንደሆኑ ለማመላከት የተነደፉ ናቸው። በዋነኛነት የተካተቱትም ቀጥለው የተጠቀሱት ናቸው።
1.መ ሠ ረተ – ሰፊና ተራማጅ የሆነ ዴ ሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መመ ሥ ረት፣ ዴ ሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ማቋቋም፣
2.“ መሬት ለአራሹ ” ን በ ሥ ራ ላይ ማዋል ፣

3.ከውጭ ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ዴ ሞክራሲያዊና በ እቅድ የሚመራ ብሔራዊ ኤ ኮኖሚ
መገንባትና የሠፊውን ሕዝብ ቁሳዊና መንፈሳዊ ደህንነት ማሻሻል፣
4.የብሄ ረሰቦ ች ን እኩልነት ሙሉ በሙሉ በማረጋገጥ ራስን በራስ ማስተዳደር
በሚ ለው መርህ መ ሠ ረት ያልተማከለ ፌደራላዊ የመንግ ሥ ት ዓይነትና ሥርዓት በእኩልነትና በወንድማማችነት እንዲቋቋም ማድረግ፣
5.የሴቶችን የእኩልነት መብት ማስከበር፣
6.ብሄራዊ ዴ ሞክራሲያዊ የሆነ የትምህርትና የባህል ሥርዓት ማቋቋም፣ ለሠፊው
ሕዝብ ግልጋሎት የቆመ የጤና ጥበቃ አገልግሎት ማካሄድ፣
7.ሕዝብና አገሪቱን ሙሉ በሙሉ የሚያገለግልና የሚጠብቅ ሕዝባዊ ጦር ሠራዊት ማቋቋም፣

  1. በገለልተኝነትና ለሰላም፣ ለ ዴ ሞክራሲና ለሶሺያሊዝም ከሚታገሉ መላ የዓለም
    ኃይሎች ጋር በመተባበር ላይ የተመሠረተ የውጭ ፖሊሲ መከተል የሚሉ ናቸው።
    ( ዴ ሞክራሲያ ቅጽ 1 ፣ ቁ 6 ፣ ገጽ 2)

ከላይ የተጠቀሱትን ግቦች ዕውን ለማድረግ ኢሕአፓ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ትግል አካሂዷል፣ አባላቱም ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉት ለነዚህ ጥያቄዎች ተግባራዊነት ነበር። ዛሬም እነዚህ ጥያቄዎች አልተመለሱም፡፡

ገና ከጅምሩ ኢሕአፓ በኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድማማችነት በሃገሪቱ ሉዓላዊነትና የግዛት
አንድነት የማይደራደር፣ ፍንክች የማይል አቋም ነበረው፣ አሁንም በዚህ አቋሙ እንደፀና ነው። እንዲህ በመሆኑም የትጥቅ ትግል በጀመረበት ሰሜን ምሥራቅ ትግራይ (ዓሲምባ) የፈሰሰው የጀግኖች አባሎቹ ደም፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች የተውጣጣ መሆኑ የአባላቱና የድርጅቱ ኅብረብሄራዊነት ማረጋገጫ እንደሆነ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ ለብዙ ሽህ ዓመታት ታፍራና ተከብራ በነፃነት የኖረችው በኢትዮጵያውያን ሁሉ መስዋዕትነት እንደሆነ ኢሕአፓ በፅኑ ያምናል። እያንዳንዱ ብሄረሰብ


ዴሞክራሲያ —————————- ታህሳስ ፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ————————————— ገፅ 4

በተናጠል ለብቻው አገር ሆኖ የኖረበት ታሪክ የለም፡፡


ይልቅስ እርስ በርሱ የተዛነቀና የተዋሃደ ሕዝብ በመሆኑም ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴቶችን ገንብቷል፡፡
የሚጎድለው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እጦት በመሆኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የእኩልነት መብቱ ተከብሮ አብሮ መኖር ይችላል ብሎ ኢሕአፓ ድሮም አሁንም ያምናል። በዚህ እምነቱም ጸንቶ ለ48 ዓመታት ሁሉንም የኢትዮጵያ ልጆች አቅፎ በትግል ኖሯል፣ የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካትም ትግሉን ይቀጥላል።
በኢሕአፓ እምነት “የእኔ ብሔረሰብ ብቻ ወርቅ ነው፤ ሌላው ጨርቅ ነው፣ በመቃብሩ ላይ መጨረሻውን ምስማር መትቼ እኔ ብቻ እኖራለሁ” የሚለው አስተሳሰብ ውድቅ መሆኑን አስረግጦ፣ ይህ የጠባብ ብሄረተኞች መታወቂያ የሆነው አመለካከት እንዲወገድ ታግሏል፤ አሁንም ይታገላል። ይህ ዓይነት አመለካከት ተወግዶ ሁላችንም በጋራ፣ ልዩነታችንን በሰለጠነ መንገድ አካትተን ሰላም፤ ዴሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን መመሥረት ዋነኛ መርሆአችን አድርገን መቆም ይኖርብናል።

ለዚህም ነው ኢሕአፓ ገና ከጥንስሱ ጀምሮ ለዴሞክራሲያዊ መብት መከበር፣ ሁሉንም በእኩል የሚያሳትፍ ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋም፤ መሬት ላራሹ እንዲሆንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን አንግቦ ትግሉን የጀመረውና አስካሁንም የቀጠለው።
በዚህ አቋሙም የደርግን ፋሽሽታዊ ሥርዓት እስከ ውድቀቱ ድረስ፣ ከደርግ ቀጥሎ የመጣውን የህወሓትን ሥርዓትም አሁን ድረስ ያለመታከት በርካታ መስዋእትነት በመክፈል የታገላቸው። የደርግን መንግሥት ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም በሚልና አረመኔያዊና ፋሽሽታዊ ባህሪውን በማጋለጥ፣ በገጠርም የትጥቅ ትግልም በማካሄድ ከሥልጣን እስከሚወርድ ድረስ ኢሕአፓ ከእምነቱ ፍንክች ሳይል ቆይቷል።
የህወሓትን ሥርዓት ከመነሾው ጠባብ ብሔረተኛ አቋሙን በመቃወም በኋላም ኢ-ዴሞክራሲያዊ
ባህሪው እየጎላ ሲመጣም በማውገዝ በሃሳብም ሆነ በትጥቅ ትግል ያለማመንታት ታግሎታል። ህወሓት የኢሕአፓን ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አቋም በመገንዘብ በጠላትነት ስለፈረጀው ፓርቲው ድርጅታዊ ሥራውንና ትግሉን በኅቡዕ ለመቀጠል ተገደደ። አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ኢሕአፓና ህወሓት አንድ ነበሩ በኋላ ነው የተጣሉት የሚል የተሳሳተ ዘገባ መዘገባቸውን አድምጠናል።

ኢሕአፓ ገና ከጥንስሱ ጀምሮ ከህወሓት ጋር አንድ ሆኖ አያውቅም። የዓላማ አንድነትም
የላቸውም። የደርግ አካሄድ አላምርህ ሲለው ኢሕአፓ ከኅቡዕ ማደራጀቱ ተግባር ጎን ለጎን በሰሜን ኢትዮጵያ (ትግራይ፣ በጌምድርና ጎጃም) ትጥቅ ትግሉን አጠናክሮ ቀጠለ። ይህን የኢትዮጵያዊነት አቋሙን ዕውን ለማድረግ ከሰሜን ምሥራቃዊ ትግራይ ጀምሮ እስከ ጎጃም ድረስ የወያኔን ጠባብ ብሄርተኛና ኢ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ከባድ መስዋእትነት በመክፈል ተፋለመው።
የ50ዎቹና የ60ዎቹ ትውልዶች ጠበንጃ የመንከስ ሱስ ኑሮባቸው አይደለም ትግላቸውን በመፈንቅለ
መንግሥትና በትጥቅ ትግል ያካሄዱት። የንጉሡም ሆነ የደርጉ ሥርዓቶች ቅንጣት ታህል ሞክራሲያዊ
እምነትና ባህል ስላልነበራቸው፣ ለየት ያለ አመለካከት ለነበራቸው ዜጎች መደራጀትን፣ ደራጅተውም
ከአገዛዙ አመለካከት የተለየ ሃሳብ አፍልቀው ለውጥ እንዲመጣ የማይፈቅዱ ስለነበሩ ነው የሕዝብን መብት ለማስከበር ትግሉ ያስፈለገው። መግደልም ሆነ መገደልንም መርጠውት አይደለም። የንጉሡና የፋሽሽቱ ደርግ ሥርዓት ኢ-ዴሞክራሲያዊነትን ስለጫነባቸው ነው መታገል ያስፈለገው። ኢ-ዴሞክራሲያዊነታቸውን በአንድ ምሳሌ ለማሳየት ያህል፤ ደርግ መጀመሪያ ሥልጣን እንደያዘ ሲያዥጎደጉደው ከነበሩት መግለጫዎች አንዱ ውስጥ ተግባርንና በግልጽ የታወቀ


ዴሞክራሲያ —————————- ታህሳስ ፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ————————————— ገፅ 5

አቋምን ብቻ ሳይሆን ማሰብን ሳይቀር እንደ ወንጀል አድርጎ ያወጀበት ሁኔታ ነበር። ቀጥሎ የመጣው
የህወሓት ጠባብ ብሄረተኛና አረመኔያዊ ሥርዓትም ሁኔታውን ጎሣዊ መልክ በመስጠት አገሪቱን ወደባሰ አዘቅት ከተታት። ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የወረቀት ላይ ነብሮች ብቻ ሆኑ፡፡
ኢሕአፓ የዓሲምባን መሬት ከረገጠበት ከየካቲት 1967 ዓ.ም ጀምሮ መስዋዕትነትን እየከፈለ በከተማና በገጠር ለረዥም ጊዜ ታግሏል። ከዓሲምባ በኋላ ኢሕአፓ ጎንደር ክፍለ ሀገር፣ ጭልጋ አውራጃ፣ ቋራ ውስጥ በ 1976 ዓ.ም በበርካታ አጀንዳዎች ላይ የሰከነ ውይይት አድርጎ አስፈላጊና ጠቃሚ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ የቻለውን ሁለተኛ ጉባኤውን አደረገ። ጎንደርና ጎጃም ውስጥ ከነበሩ አባላቱ በተጨማሪ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከሱዳን፣ የመጡ ተወካዮችም በጉባኤው ተሳትፈዋል። ድርጅቱ እስከዛን ጊዜ ድረስ መመሪያው አድርጎ ይከተለው የነበረውን ርእዮተ-ዓለም፣ ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን፣ በመተው ሶሽያል ዴሞክራሲን፣ እንደ መመሪያ ርእዮተ-ዓለሙ የተቀበለው በዚሁ ጉባኤው ላይ ነበር። ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ፣ ኢ.ሕ.አ.ፓ. ኢትዮጵያ ውስጥ ለመድብለ ፓርቲ ሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት መታገል እንዳለበትም ወሰነ።
ሆኖም የኢትዮጵያ አንድነትና ጥንካሬ ጠላቶች በሆኑ በህወሓት፣ በሻዕቢያና በሱዳን የተቀነባበረ ወታደራዊ ከበባና ጥቃት፣ ከበርካታ አባላት፣ ፅኑ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊትና (ኢሕአሠ) የፓርቲው አመራር መስዋዕትነት በኋላ ድርጅቱ የትጥቅ ትግሉን እንዲያቋርጥ ተገደደ።
የትጥቅ ትግልን ማቆም ግን በትግሉ ፅኑ እምነት ላላቸው አባላቶቹ ትግል ማብቃት ነው ማለት
አልነበርም፣ ትግሉን በአዲስ ቅየሳ ማስኬድና ማስቀጠል እንጂ። ኢሕአፓ ከመነሻ ትግሉን ያስጀመሩት ጥያቄዎች ስላልተመለሱና አሁንም ህያው ስለሆኑ ትግሉን በአገር ቤት በህቡዕ፤ በውጭ አገር ደግሞ በይፋ ቀጠለበት። ይህን ሁሉ ዓመታትም በአባላቱ ጥንካሬ ይኸው ህያው ሆኖ ከዚህ ደርሷል።
ኢሕአፓ በወቅቱ ብሩኅ አዕምሮ የነበራቸውን ምሁራን በውስጡ ያቀፈ ፓርቲ ነበር። ከሞት የተረፉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለዓመታት ያለፍርድ በእስር ቤት የማቀቁና የአካልና የአዕምሮ ስቃይ የደረሰባቸው ናቸው። በዚያን ጊዜ እነዚያ ኢሕአፓን የተቀላቀሉ ወጣቶች አብዛኛዎቹ በአገሪቱ የሚሰጠውን የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች መልቀቂያ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘግቡ ነበሩ።
አስተማሪዎቻቸውም ብሩኅ አዕምሮ የነበራቸው የፓርቲያችን አባላት የነበሩ ለመሆናቸው ከሞት
የተረፉት አባላት ህያው ምስክር ናቸው። በህወሓት/ኢህአዴግ ውስጣዊ መናጋትና በዚያም
ምክንያት በተፈጠረው የለውጥ ኃይል ሳቢያ አገር ቤት ውስጥ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ የመታገል ዕድል ሲፈጠር ይህን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም፣ ኢሕአፓ በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል በማኪያሄድ ላይ ይገኛል። የኢሕአፓ የማይከስም የትግል ባህሪው ይኸው አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሶ በኢትዮጵያ ምድር ሦስተኛ ጉባኤውን ለማካሄድ እንዲበቃ አድርጎታል። አሁንም ቢሆን ገና ከጥንስሱ ኢሕአፓ ትግሉን ሲጀምር ያነሳቸው፤ መሬት ለአራሹ፣ የብሄረሰብ መብት ይከበር፣ ዓለምአቀፍ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ፣ የሃይምኖት እኩልነት ይረጋገጥ፣
የሠራተኛው መብቶች ይከበሩ፣ የሴቶች የእኩልነት መብት ይረጋገጥ፣ ድህነት ወንጀል አይደለም የሚሉት ጥያቄዎች ሁሉ ዛሬም አልተፈቱም። አሁንም ሊያታግሉ የሚችሉ የፖለቲካ አቋሞች ናቸው። እንዲያውም በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ላይ በሰፈነው የጎሣ ፖለቲካ ምክንያት ዜጎች በማንነታቸው የተነሳ ሲገደሉ፣


ዴሞክራሲያ —————————- ታህሳስ ፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ————————————— ገፅ 6

ከኖሩበት ቀየ እየተፈናቀሉ፣ ንብረታቸውን እየተነጠቁ ስደተኞች ሲሆኑ ማየት የቀን ተቀን ተግባር በመሆኑ ኢሕአፓ ዜጎች በማንነታቸው መፈናቀልና መገደል የለባቸውም በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ እያሰማ ነው።

መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ የሆነውን የሕግን የበላይነት የማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣም አሁንም አጥብቆ ይጠይቃል። ኢሕአፓ ከህቡዕነት ወጥቶ በግልፅ እና ሕጋዊ በሆነ መልክ መንቀሳቀስ ከጀመረ እነሆ ከአንድ ከዓመት በላይ ሆኖቷል። በዚህ አንድ ዓመት መልሶ የማደራጀት ሂደት፣ ሲደርስበት በነበረው ምት ተበጣጥሰው የነበሩትን መዋቅሮቹን በመጠገንና በህቡዕ ይንቀሳቀሱ የነበሩትንና ከትግሉ ውጭ ሆነው የቆዩ የቀድሞ
አባሎቹን በማሰባሰብ ላይ ነበር።

በዚህ ጥረቱም በጣም ተስፋ ሰጪ እርምጃዎችን ተጉዟል። በርካታ ወጣት ምሁራን ወደ ትግሉ ጎራ እንዲሰበሰቡ እያደረገም ይገኛል፡፡
ኢሕአፓ ይህን መጠነኛ ድል መድረስ ከሚገባው ደረጃ ላይ ለማድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሰጠው መመሪያ መሠረት እነሆ ጉባዔውን በማካሄድ ላይ ይገኛል። ይህ ጉባዔ በ1967ዓ.ም ከተደረገው ፓርቲው እራሱን ካስተዋወቀበት መለስተኛ ጉባዔ በኋላ በኢትዮጵያ
ምድር ሲደረግ ሁለተኛው መሆኑ ነው። በ1976 ዓ. ም ቋራ ውስጥ ሁለተኛ ጉባዔውን በተሳካ ሁኔታ አካሂዶ ነበርና። ከብዙ ዓመታት በኋላ ኢሕአፓ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ማድረጉንም “ዳግማይ ትንሣኤ” ብለነዋል።

ሰማዕታቱ የሞቱለትን ዓላማ ለማሳካት ዛሬም ትግሉን የቀጠልን መሆናችንን
አስመልክተንም ለኒያ ለተሰዉ ታጋዮች “በትግል መሞት ሕይወት… ዳግም ትንሳኤ ልደት…” የሚለውን መዝሙር እንዘምርላቸዋለን፡፡

ኢትዮጵያ አንድነቷን አክብራ ለዘላለም በሰላም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!!
ለኢትዮጵያ ህልውና፣ ለዴሞክራሲና ለሕግ የበላይነት እንታገላለን!