
ቢያንስ ለ 140 ዓመታት፣ ከአውሮፓውያኑ 1772 እስከ 1911 ድረስ ማለት ነው፣ ካልካታ በእንግሊዝ ቁጥጥር ስር የነበረቸው ህንድ ዋና ከተማ ነበረች። ይህ ደግሞ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለሚመጡ በርካታ ሰዎች የንግድ ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል።
በዚህ ምክንያት ቻይናውያን፣ አርመኖችና ግሪኮች ንግዳቸውን በካልኮታ በኩል ያቀላጥፉ ነበር። በዚህ መንገድ ነበር ታድኣ ከመካከለኛው ምስራቅ የሚመጡ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት።
ባግዳዲዎች ወይም የባግዳዲ አይሁዶች በመባል የሚታወቁት እነዚህ ህዝቦች ከአሁኖቹ ኢራቅ፣ ሶሪያ እና ሌሎች አረብኛ ተናጋሪ ሀገራት የዘር ግንዳቸው ይመዘዛል። እ.አ.አ. በ 1798 አካባቢ ነበር እነዚህ አይሁዶች በካልካታ መስፈር የጀመሩት።
• ”በፍርሀት የምንኖርና በሃገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ የምንቆጠር ሰዎች ሆነናል”
• የቢላል መስጂድንና ራጉዔል ቤተ ክርስትያንን የሚያሰሩት ካህን
በ1990ዎቹ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዶች ከሂንዱ እና እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ጋር በካልካታ መኖር ጀመሩ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ደግሞ ከ 5000 በላይ አይሁዳውያን ይኖር የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዐት አብዛኛዎቹ ወደ እስራኤል፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ ተሰድደዋል።
በካልካታ የሚኖሩ የአይሁዶች ቁጥር ከ 24 እንደማይበልጥ ይነገራል።
ምንም እንኳን የሀይማኖቱ ተከታዮች ቁጥር እጅጉን ቢቀንስም በአካባቢው ያለው የሌላ እምነት ተከታይ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረውን ባህል እያስቀጠለ ይገኛል።
በካልካታ የቀሩት ሶስት የአይሁድ ቤተ መቅደሶች ደግሞ እንክብካቤ የሚደረግላቸውና ንጽህናቸው የሚጠበቀው በሙስሊም እምነት ተከታይ ወንዶች ነው።
በ1856 የተሰራው ቤት ኤል የሚባለው ቤተ መቅደስ ውስጥ ለመጎብኘት የሚገቡ ሰዎች ብዙም ያልተለመደ ነገር ይመለከታሉ፤ ጭንቅላታቸው ላይ የሙስሊም ቆብ ያጠለቁ አራት ወንዶች በእንጨት የተሰራውን በረንዳና በእምነበረድ የተሰራውን ወለል ጎንበስ ብለው ሲያጸዱ።
ሲራጅ ክሃን ላለፉት 120 ዓመታት ቤተሰቦቹ ተቀጥረው ሲሰሩት የነበረውን ስራ እያከናወነ ይገኛል።
በካልኮታ የአይሁዶች ማህበረሰብ ዋና ጸሀፊ የሆኑት አም ኮኀን እንደሚሉት ሲራጅ ክሃን እና መሰል የእስልምና እምነት ተከታዮች ሆነው ቤተ መቅደሱን የሚንከባበከቡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደ አይሁድ ቤተሰብ አባላት ነው የሚቆጠሩት።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊትና በኋላ በርካታ አውሮፓ አይሁዶች ናዚ ጀርመኖችን ሸሽተው በካልካታ ተጠግተው ነበር። ልክ ከዚህ በፊት ቀድመው እንደመጡት የመካከለኛ ምስራቅ አይሁዶች የአውሮፓ አይሁዶችም በካልካታ ሰላምና አስገራሚ ባህልን አግኝተዋል።
”ፈጣሪ በሁሉም ቦታ ይገኛል፤ በመስጂድም፣ በቤተ ክርስቲያንም፣ በገዳምም፣ በአይሁድ ቤተ መቅደስም። በዚህ ቤተ መቅደስ የምሰጠው አገልግሎት ከፈጣሪ ምስጋናን የሚያስገኝልኝ እንደሆነ ስለማውቅ በሙሉ ፈቃደኝነት ነው የማደርገው” ይላል ሲራጅ ክሃን።
” አያቴ፣ አባቴና ወንድሜ በዚሁ ተመሳሳይ ስራ ተሳትፈዋል። ቤተሰቤ በእስልምና ሀይማኖት ጠንካራ ነው፤ ነገር ግን የአይሁዶችን ቤተ መቅደስ ከመንከባከብ አላስቆምንም።”
የህንድ ምዕራባዊ ቤንጋል ከፍተኛ የሙስሊም እምነት ተከታዮች የሚገኙበት ሲሆን ካልካታ ደግሞ ዋና ከተማ ናት። 4.5 ሚሊየን የሚሆኑት የግዛቱ ነዋሪዎች ሙስሊሞች ሲሆኑ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶች፣ ቡድሂስቶችና የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች በፍቅርና በስምምነት ይኖሩባታል።
ለዚህም ነው ‘የደስታ ከተማ’ የሚል ስያሜ የተሰጣት።
በካልካታ የሂንዱ እምነት ተከታዮች መስጂድ ውስጥ ገብተው የኢድ አል አድሃ በአልን ሲያከብሩ መመልከት የተለመደ ነገር ነው። በአውሮፓውያኑ 1881 በአይሁዶች የተቋቋመው የሴቶች ትምህርት ቤት በአሁኑ ሰአት ሙሉ በሚባል ደረጃ ሙስሊም ተማሪዎች ብቻ ናቸው የሚገኙበት። የሃይማኖቱ ጉዳይ የተረሳ ይመስላል።
ህንድ በ1974 ከእንግሊዝ ነጻነቷን ስታገኝ አይሁድ እምነት ተከታዮች ሀብት ንበረታቸው በአዲሱ የህንድ መንግስት እንደሚወረስባቸው በመፍራት ወደ አሜሪካና እንግሊዝ ተሰደዋል።
ሌላኛው በካልካታ የአይሁዶች ቁጥር መቀነስ ምክንያት በ1948 እስራኤል እንደ አንድ ሀገር መቋቋም ነው።
ምንም እንኳን በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥራቸው እየቀነሰ የመጣው የካልካታ አይሁዶች የወደፊት እጣ ፈንታ ባይታወቅም ሁለቱ ቤተ መቅደሶች በህንዱ አርኪዮሎጂካል ሰርቬይ በሀገር ሀብትነት ተመዝግበው ይገኛሉ።