January 6, 2020
Source: https://mereja.com/amharic/v2/196108
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአገር አቀፍና የክልል ፓርቲዎች ማሟላት ያሉባቸው ግዴታዎች መመርያ አጸደቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቦርዱ ተመዝግበው የሚገኙ የአገር አቀፍና የክልል ፓርቲዎች (በአዋጅ ቁ. 1162/2011 መሰረት) ማሟላት ያሉባቸው ግዴታዎች መመርያ አጸደቀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ 1162/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን አስመልክቶ ታህሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም መመሪያ አጽድቋል፡፡ መመሪያው ከመጽደቁ በፊት ከፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን ሰባት ፓርቲዎች ደግሞ በጽሁፍ ግብአታቸውን አስገብተዋል፡፡ በመመሪያው የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.ሁሉም ተመዝግበው የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎች በአዋጅ 1162/2011 የተቀመጠውን የመስራች አባላት ፊርማ ለማሟሟላት ሁለት ወራት የጊዜ ገደብ አላቸው፡፡
2.ጠቅላላ ጉባኤ ሳያካሂዱ ጊዜ ያለፈባቸው ፓርቲዎች በአዋጅ 1162 መሰረት አሟልተው በሁለት ወር ውስጥ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
3.ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ ያካሄዱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች በአዲሱ አዋጅ 1162 ላይ የተቀመጠውን የጠቅላላ ጉባኤ መስፈርት በሟሟላት እስከ ጥር 2013 ዓ.ም ድረስ አጠናቀው ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
4.ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ ያካሄዱ ክልላዊ ፓርቲዎች በአዲሱ አዋጅ 1162 የተቀመጠውን የጠቅላላ ጉባኤ መስፈርት ለሟሟላት እስከ ታህሳስ 2013 ድረስ አጠናቀው ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
5.በቦርዱ ያልተመዘገቡ ነገር ግን በቀድሞው ህግ በሂደት ላይ ያሉ፣ በቀድሞ መሟላት ያለበትን አጠናቀው በአዲሱ አዋጅ ያሉትን መስፈርቶችም ጨምረው በጋራ ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
6.አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎችን ህጉ ላይ ያለውን የመስራች አባላት ቁጥር ከሟሟላት መስፈርት ነጻ ናቸው ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሁሉም የተመዘገቡ እና በሂደት ላይ ያሉ የፓለቲካ ፓርቲዎች ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርትና እና ጊዜ ገደብ የሚገልጽ ደብዳቤ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ለሁሉም ፓርቲዎች የሚያደርስ ይሆናል፡፡
የፓርቲዎች ምዝገባ መመሪያውን ከሰር ከሚገኘው ማስፈንጠሪያ ላይ ማውረድ ይችላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ