January 8, 2020

Source: https://mereja.com/amharic/v2/196645

“የኢትዮጵያን የአንድነት መሠረት ያስቀመጠች ቤተ ክርስቲያን ናት”

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ የኢትዮጵያን የአንድነት መሠረት የጣለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት በማለት ተናገሩ።

የቢሮ ኃላፊው ይህን የተናገሩት የማኅበረ ቅዱሳን የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን ስርጭት መጀመሩን አስመልክቶ ድጋፍ እና ትብብር ላደረጉ አካላት በዮድ አቢሲኒያ የባህል አዳራሽ ታኅሣሥ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ባዘጋጀቀው መርሐግብር ላይ ነው።

“የምንሠራው ታሪክን፣ ቅርስን፣ ኪነ ጥበብን፣ ሥነ ምግባርን በመጠበቅ ልጆቻችንን ከባዕድ ባህል ወረራ መጠበቅ ከሆነ ይህን በተግባር ለመግለጥ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውጭ አይታሰብም” ብለዋል።

“ወጣቶች ሃይማኖታቸውን፣ ምግባራቸውን፣ ባህላቸውን፣ ማንነታቸውን እንዲጠብቁ የማኅበረ ቅዱሳን የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን ስርጭት መጀመሩ ትልቅ እገዛ ያደርጋል” ያሉት የቢሮ ኃላፊው “ቤተ ክርስቲያን ኪነ ጥበብን ለማዳበር ብዙ ሠርታለች። እነ ቅዱስ ያሬድን ያህል የዜማ ሊቅ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት” በማለት ተናግረዋል።

“ራሴን ጨምሮ የብዙ ከያንያን ታሪክ ከቤተ ክርስቲያን ጋር የተገናኘ ነው” ያሉት ኃላፊው “ቤተ ክርስቲያን ኪነ ጥበባዊ ይዘት ያላቸውን ጉዳዮች በትያትር፣ በፊልም እና በሌሎች መሰል ዘመኑ ያስገኛቸው የቴክኖሎጅ ውጤቶች ማስተዋወቅ ይኖርባታል።መንግሥት መሥራት የነበረበትን ቤተ ክርስቲያን እየሠራችልን በመሆኑ ማገዝ ይኖርብናል” ብለዋል

“ቤተ ክርስቲያን የቱሪዝም መፈጠሪያ በመሆኗ ምንም ነገር ሳንከፍላት ሥራችንን እየሠራችልን ነው። የሁሉ ነገር ምንጭ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ጥበቧን በትክክል ለምእመናን ማድረስ ስለሚኖርባት የቴሌቭዥን ጣቢያው ጥራትና ጥበብን አጣምሮ መያዝ ይኖርበታል” በማለት ተናግረዋል።

Source – Mahibere Kidusan – ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል