January 8, 2020
ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ወደ ንግድ ሥርዐት እንዲገቡ የሚያስችለው ዝግጅት መጠናቀቁን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀዉ ሁለቱን አገራት ወደ ህጋዊ የንግድ ስርአት ለማስገባት መመሪያዎች ተዘጋጅተዉ ለመንግስታቱ ተልከዋል ብሏል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ የኢትዮጵያን እና የኤርትራን ህዝቦች የንግድ ልዉዉጥ እንዲያደርጉ ሁለት አይነት ሥርዐት መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡
የመጀመሪያዉ በሁለቱ ዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ኢምባሲ በኩል የሚመራ ህጋዊ የሆነ የንግድ ሥርአት መዘርጋት ነዉ ተብሏል፡፡
ሁለተኛዉ አሰራር ደግሞ የጠርፍ ንግድን የሚመለከት ሲሆን በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ የሚገኙ ዜጎችን የሚያስተሳስር እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
እነዚህን ሁለት አሰራሮች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የንግድ መመሪያ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለኤርትራ መንግስት መላኩንም ሰምተናል፡፡
ይህ ሰነድ የምርቶቹን አይነት ፤የንግዱን ሁኔታ እና አጠቃላይ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ግንዛቤ ዉስጥ ያስገባ እንደሚሆንም ተጠቅሷል፡፡
በተለይም የጠርፍ ንግዱን በሚመለከት የህብረተሰቡን ፍላጎት መረዳት እና የንግድ ልዉዉጡ በምን አይነት መልኩ መተግበር እንዳለበት ለማወቅ ዉይይት ይደረጋል ነዉ የተባለዉ፡፡
አዲስ የሚጀመረዉ የኢትዮ ኤርትራ የጠረፍ ንግድ ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ከጂቡቲ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆንም አቶ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአየር ትራንስፖርት እንደሚገናኙ የሚታወቅ ሲሆን በየብስ እና በሌሎች መንገዶች ለመገናኘት እየተሰራ እንደሆነም ሰምተናል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም