January 8, 2020
Source: https://mereja.com/amharic/v2/196853

ኢዜአ – የብልጽግና ዋነኛ ማጠንጠኛ ኃብት ወይም ጥሪት ማፍራት ነው የሚሉት አያሌዎች ናቸው። በምሁራን አስተያየት ግን ይህ እውነት አይደለም። ኃብት ማፍራት የብልፅግና መገለጫ ከሆኑት መሰረቶች መካከል አንዱ እንጂ ብቸኛው የብልፅግና ማመልከቻ እንዳልሆነ ነው ምሁራኑ የሚያብራሩት።
በምሁራኑ አተያይ አንድ አገር ወይም ማህበረሰብ አደገ ወይም በለጸገ የሚባለው ማህበራዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካን ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔታዎቹ ላይ የላቀ እድገት በማስመዝገብ በዜጎች ሁለንተናዊ ህይወት ላይ እርካታ ሲፈጠር ነው።
ይህንን ተከትሎም ለአጠቃላይ ሰብአዊነትና የሰው ልጅ ደህንነት የሚቆረቆር በስነ-ልቦና የዳበረ አእምሮ መፈጠሩ ሲረጋገጥ ማህበረሰቡ በልፅጓል ወይም በብልፅግና ጎዳና ላይ ነው ሊባል ይችላል ይላሉ ምሁራኑ።
”ብልጽግና የዜጎች ሥጋዊ፣ የስምና የነጻነት ፍላጎቶችን በቀጣይነት ማሟላት እንዲችሉ አቅማቸውን ማሳደግ ነው” የሚለው ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፃ ሀሳቡን የበለጠ ያዳብረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ የፍልስፍና ተማሪው ዮናስ ዘውዴም ብልፅግና ዘርፈ ብዙና ሁለንተናዊ እድገት መሆኑን ይገልፃሉ።
ወደ ብልጽግና ለመጓዝ የሚከናወኑት ተግባራት ሁሉን አቀፍና እርስ በእርሳቸው በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው ይላሉ። ይሁንና ቅደም ተከተልም ሊኖራቸው ይገባል ባይ ናቸው አቶ ዮናስ።
‘በኛ አገር ምንድነው ያጣነው ምግብ፣ መጠለያ፣ ነጻነት ወይስ እኩልነት’ የሚለው መነሻ በትክክል ሲመለስ የብልፅግና ጎዳናን ያዝን ሊባል ይችላል ይላሉ አቶ ዮናስ።
በተለያዩ መፅሃፎቻቸውና በሚያስተጋቡት መንፈሳዊና ማህበራዊ ትንተናቸው የሚታወቁት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው የብልጽግና ጽንሰ-ሀሳብ “ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ስርዓታዊ” በማለት በሶስት ይከፍሉታል።
ቁሳዊ ብልጽግና አንድ ሰው በህይወት ሲኖር ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሲሟሉለት የሚያገኘው ሲሆን የሃይማኖት ተቋማት ነጻነት የባህል ውጤቶችና የቱሪዝም ሃብቶች ዕድገት ደግሞ መንፈሳዊን ብልጽግና የሚያመጡ ናቸው ብለዋል።
እንደ ዲያቆን ዳንኤል ገለጻ የቁሳዊም ይሁን መንፈሳዊ ብልጽግና ማሰሪያ ስርዓታዊ ብልጽግና ነው። ይህም የፖለቲካ ስርዓቱ፣ የሲቪል ሰርቪሱን ጨምሮ አጠቃላይ ተቋማት ግልፅነትና ጥንካሬን ያጠቃልላል ሲሉ ያብራራሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኡባንግ ሜቶ በበኩላቸው የአንድ አገር ብልጽግና የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በትክክል ሲከበሩና ፍትህ ሲሰፍን የሚመጣ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ኡባንግ ገለጻ አንድ አገር ወደብልጽግና ለማምራት በርካታ መሰናክሎችን ማለፍ ይጠበቃል።
ባደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ሰው በሰውነቱ ብቻ ክብር ማግኘት ሲችልና ነጻነቱ ሲረጋገጥለት ወደ ብልጽግና የመድረሻውን አቅጣጫ ይይዛል ባይ ናቸው።