January 9, 2020

Source: https://mereja.com/amharic/v2/197376

ውሃ የምትጠጣ ሴት

ድክምክም ሲልዎት አልያም ቆዳዎ ደረቅ ከሆነ ይፈወሱ ዘንድ አብዝተው ውሃ እንዲጠጡ ተመክረው ይሆናል። ይህ ለአስርት አመታት ሲዘወተር የነበረ አካሄድ ዘመኑ ሳያልፍበት አልቀረም፤ ሳይንሳዊ መነሻ ላይኖረውም ይችላል ተብሏል።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ አካባቢ ሰዎች ለማግኘት ውድ የነበረውን ውሃ ለመጠጣት ሲሉ ከሞት አፋፍ ይደርሱ ነበር። የተወሰኑ በሀብት የደረጁ ሰዎች ብቻ ጥማቸውን በውሃ ይቆርጡ ነበር።

ነገር ግን አሁን ነገሮች ሁሉ ተቀያይረዋል። በመላው ዓለም የሚገኙ አዋቂዎች የሚጠጡት የውሃ መጠን ጨምሯል። በአሜሪካ የታሸገ ውሃ ከጣፋጭ መጠጦች በላይ እየተቸበቸበ ነው።

የውሃ እጥረት ዋነኛው የዓለማችን ስጋት

የንፁህ ውሃ ችግር ካለባቸው ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በየቀኑ አንድ ሊትር ውሃ የምንጠጣ ከሆነ የመልካም ጤንነት ምስጢር ነው፣ ብዙ ጉልበት እና ጥሩ ቆዳ እንዲኖረን ያደርጋል፣ ክብደት ይቀንሳል፣ ካንሰርም ያጠፋል የሚል ዲስኩር ስንሰማ ኖረናል።

በደንብ ያልተረጋገጠው ህግ ውሃ ካልሆኑ መጠጦች በተጨማሪ 240 ሚሊ ሊትር በሚይዝ ብርጭቆ በቀን ስምንት ግዜ ውሃ እንድንጠጣ እንመከራለን። አጠቃላይ ድምሩ በቀን 2 ሊትር አካባቢ ነው።

ይህ ልማድ ሳይንሳዊ ግኝቶች ላይ የተመሰረተ አይደለም። ታድያ ይህ አስተሳሰብ ከየት መጣ? ጥቂት ከማይባሉ አስርት ዓመታት በፊት የተዘጋጁ ሁለት መመሪያዎችን በተሳሳተ መልኩ ከመተርጎም የተነሳ ይመስላል።

በአውሮፓውያኑ 1945 የአሜሪካ ምግብና የአመጋገብ ስርዓት ቦርድና ብሄራዊ የጥናት ካውንስል እንዳሳሰበው አዋቂዎች ለእያንዳንዱ በምግብ ውስጥ ለሚገኝ ካሎሪ አንድ ሚሊ ሊትር ውሀ መውስድ እንዳለባቸው ይመክራል።

አዋቂ ሴቶች ለ2 ሺ ያህል ካሎሪ ሁለት ሊትር፣ ወንዶች ደግሞ ለሁለት ሺ አምስት መቶ ካሎሪ ሁለት ከግማሽ ሊትር ፈሳሽ እንዲወስዱ ይመክራል። ይህ ማለት ግን ውሃ ብቻ ሳይሆን እስከ 98 በመቶ ውሃ ያላቸው ፍራፍሬ እና አትክልትንም ያጠቃልላል።

በ1974 የተዘጋጀው ‘የአመጋገብ ስርዓት ለጥሩ ጤና’ የሚለው ታዋቂ መፅሐፍ ውስጥ ማርጋሬት ኤምሲ ዊልያምስ እና ፍሬድሪክ ስቴር የተባሉ የአመጋገብ ስርዓት ባለሙያዎች በተባባሪ ፀሃፊነት ተሳትፈዋል።

በዚሁ መጽሐፋቸው አንድ አዋቂ በቀን ከ6 እስከ 8 ብርጭቆ ውሃ መጠጣት አለበት ሲሉም ምክረ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል። ነገር ግን እነሱ የፃፉት ፍራፍሬና አትክልት እንዲሁም ለስላሳ መጠጥና ቢራንም ቢሆን ይጨምራል ብለው ነው።

ያልታወቁት ከወር አበባ ጋር የሚከሰቱ የባህሪ ለውጦችና አደገኛ ውጤታቸው

በርግጥ ውሃ ጠቃሚ ነው፤ የሰውነታችንን ሁለት ሶስተኛ ክብደትንም ይይዛል። ሰውነታችን ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችና አላሰፈላጊ ቆሻሻዎችን ያጓጉዛል፣ የሰውነታችንን ሙቀት ይቆጣጠራል፣ ሰውነታችን እንዲለሰልስና መገጣጠሚያዎቻችን ላይ የሚፈጠርን መጎርበጥ እንዲቀንስ ያደርጋል፣ ሰውነታችን ውስጥ የሚካሄድ የኬሚካል ውህደትን ያግዛል።

ሰዎች ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ በላብ፣ በሽንትና በትንፋሽ በኩል ሰውነታቸው ውስጥ ያለው ውሃ እየቀነሰ ይሄዳል። በሰውነታችን ውስጥ በቂ የውሃ ክምችት እንዳለን ማረጋገጥ ድርቀትን ለመከላከል ወሳኝ ነው።

ከ1-2 በመቶ የሰውነታችንን የውሃ መጠን ስናጣ ድርቀት እንደሚያጋጥመን ይታወቃል። የድርቀት ምልክቶችን ማወቅ ቀላል ነው፤ ሰውነታችን እንደገና ፈሳሽ እሰከሚያገኝ ድረስ ድርቀቱ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል። የተለመደ ነገር ባይሆንም ድርቀት ለሞት እስከማብቃትም ሊያደርስ ይችላል።

ውሃ

ለአመታት በቂ መረጃ ሳይቀርብበት ሲተች የነበረው የውሃ አጠጣጥ ሕግ ጥም ሲሰማን በአደገኛ ሁኔታ ሰውነታችን ደርቋል ብለን እንድናምን አድርጎናል።

የአንድ ጤናማ ሰው ጭንቅላት በራሱ የውሃ እጥረትን አነፍንፎ መለየት ይችላል። ጥምን በማነሳሳት ውሃ እንድንጠጣ ያደርገናል። ሆርሞኖች በማመንጨትም ኩላሊታችን ሽንታችንን በማወፈር ውሃ እንዲቆጥብ ምልክት ይሰጣል።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን ነዳጅ. . . ውሃ!

ሰውነታችንን የምናሰተውል ከሆነ መቼ እንደሚጠማን ይነግረናል ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

ብዙ ውሃ መጠጣት ግን ጠቃሚ ነው?

ሰውነታችን ከሚያስፈልገው የውሃ መጠን በላይ መጠጣት ድርቀትን ከመከላከል ባለፈ ሊሰጠው ስለሚችለው ጥቅም በአስተማማኝ መልኩ የተገኝ መረጃ እስካሁን የለም።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ተገቢውን የውሃ መጠን መጠጣት ክብደትን ለመቆጣጠር ይረዳል።

አንድ የተመራማሪዎች ቡድን፣ ክብደት መቀነስ የሚፈልጉ ሰዎችን በሁለት ምድብ አድርገው ሙከራ ሰርተው ነበር። አንደኛው ቡድን ላይ የሚገኙት ሰዎች ጤናማ የሆኑ ምግቦችን ብቻ እንዲበሉ ተደረጉ። በሁለተኛው ምድብ የሚገኙት ደግሞ ከጤናማው ምግብ በተጨማሪ ግማሽ ሊትር ውሃ ከምግብ በፊት እንዲጠጡ ተደርገዋል።

በጥናቱ መጨረሻ ላይ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት ደግሞ ግማሽ ሊትር ከምግብ በፊት የጠጡት ሰዎች ካልጠጡት በተሻለ ክብደት ቀንሰዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት ሰውነታቸው በጣፋጭ ነገሮች ፋንታ ውሃውን እንደ ኃይል ምንጭነት በመጠቀሙ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ግን ብዙ ሰዎች የማይረዱት አንድ ነገር አለ። ሰውነታችን ከሚፈልገው በላይ ውሃ ስንጠጣ ተያያዥ ጉዳቶች አሉት።

በክረምት ሲዘንብ የመሬት ሽታ ለምን ያስደስተናል?

ውሀ በየቀኑ መጠጣት ለሰውነታችን ያለው አስፈላጊነት ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም ለምሳሌ ከከባድ የሰውነት እንቅስቃሴ ወይም አልኮል መጠጥ ከጠጣን በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ውሃ መጠጣት ጉዳት ያስከትላል።

‘ሃይፖናትሬሚያ’ በመባል የሚታወቀው ይህ የጤና እክል ኩላሊቶቻችን ውሃን በአግባቡ እንዳያስወግዱ ያደርጋቸዋል።

ስለዚህ ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ውሀ መጠጣት አለብን ብለን በግድ ሳይሆን መጠጣት ያለብን፤ ሰውነታችን ተፈጥሮአዊ ጊዜውን ጠብቆ ውሀ አጠጡኝ ሲል መሆን ያለበት ባይ ናቸው።