15 January 2020
‹‹ደመወዝ እንከፍላለን እንጂ እኛ የአዲስ አበባ ፖሊስን አናስተዳድርም››
ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ
‹‹ለሕዝባችን ደኅንነት ሲባል ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ተቀራርበን እንድንሠራ ሊደረግ ይገባል››
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ በሆነችው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ አልፎ አልፎ ለሚያደርገው ቁጥጥር የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ሰኞ ታኅሳስ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በመጥራት የሥራ ክንውናቸውን ሲገመግም፣ በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ ትኩረትን ከሳቡ የውይይት ርዕሶች መካከል ነበር። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ማን ሊያስተዳድረው ይገባል የሚለው ጉዳይም አወዛግቧል፡፡
በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ሰብሳቢነትና የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ብቻ በተሳተፉበት በዚህ የግምገማ መድረክ፣ በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራው የከተማ አስተዳደር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን አቅርቧል።
ምክትል ከንቲባው ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ የቋሚ ኮሚቴዎቹ ሰብሳቢዎች ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተቀበሏቸውን ቅሬታዎች፣ እንዲሁም ራሳቸው ባከናወኗቸው የክትትልና ቁጥጥር ተግባራት ያስተዋሏቸውን ችግሮች ለአስተዳደሩ ካቢኔ አባላት በጥያቄ አቅርበዋል።
የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በከተማዋ ስለሚስተዋሉ የተደራጁ ስርቆቶች፣ እንዲሁም እየተስፋፋ የሚገኘውን ውንብድና በመግታት ረገድ የከተማ አስተዳደሩ ውስንነትን በተመለከተ ያነሱት ጉዳይ አንዱ ነበር። ይህ ጉዳይ ትኩረት ካልተሰጠውና በዲሲፕሊን ካልተመራ አስቸጋሪ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ በወቅቱ በአጽንኦት በመስጠት አሳስበዋል። ሌሎች የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችም በተለይ ከሕገወጥ የመሬት ወረራ መንሰራፋትና አስተዳደሩ ይህንን በመከላከል ረገድ ያለበትን የሕግ ማስከበር ውስንነት አንስተዋል።
የከተማ አስተዳደሩን እየመሩ የሚገኙት ምክትል ከንቲባ ታከለ በከተማዋ እየተስተዋለ ነው የተባለውን የተደራጀ ዘረፋና ውንብድና በተመለከተ፣ አስተዳደሩ ሕግን ከማስከበር አንፃር ያለበትን የሕግ ክፍተት በዋናነት በማንሳት ምላሽ ሰጥተውበታል። ‹‹የከተማዋ ፀጥታና ደኅንነት መከበር እንዳለበት እኔም አምናለሁ፤›› ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ ‹‹ነገር ግን የአዲስ አበባ ፖሊስን የምንመራው እኛ አይደለንም። የሚመራው ፌዴራል ፖሊስ ነው። የእኛ ድርሻ ደመወዝ መክፈል ብቻ ነው፤›› ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ተጠሪነት ወደ ከተማ አስተዳደሩ ቢመጣ ችግሩን ለመፍታት ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፣ ይህንን በተመለከተ ለፌዴራል ፖሊስ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር አስረድተዋል። ‹‹የአዲስ አበባ ፖሊስ በከተማ አስተዳደሩ ሥር እንዲሆን ጥያቄ አቅርበን ነበር። ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር ባይመጣ እንኳን ውክልና ስጡንና በባለቤትነት የከተማውን ፀጥታ እናስከብር ብለን ጠይቀናል፡፡ ነገር ግን አልሰጡንም፤›› ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ይህ ቢሆንም የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ አስተዳደሩ የራሱን ሚና ከመወጣት እንዳልተቆጠበም ገልጸዋል። ይህንንም ሲያስረዱ፣ ‹‹አስተዳደሩ በራሱ መንገድ ወጣቶችንና ነዋሪዎችን በኢመደበኛ አደረጃጀት በአነስተኛ ቡድኖች በማደራጀት አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ እያደረገ ነው፤›› ብለዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ በከተማ አስተዳደሩ ሥር ባለመሆኑ የከተማዋን ደኅንነት ከማስከበር አንፃር ክፍተት እየፈጠረ ስለሆነ፣ ፓርላማው ያለውን የሕግ ክፍተት በማስተካከል እንዲያግዛቸውም ጥያቄ አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከላይ የተገለጹት ቅሬታዎችን በአንድ በኩል ሲያሰማ፣ የፌዴራል ፖሊስም የአዲስ አበባ ፖሊስን በመምራትና የከተማዋን ፀጥታ ከማስከበር አኳያ ችግር እየገጠመው መሆኑን፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመልክቶ ነበር።
የፌዴራል ፖሊስ ያለውን ቅሬታ ያስታወቀው ቋሚ ኮሚቴው ታኅሳስ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን የሥራ እንቅስቃሴ፣ በኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት በአካል ተገኝቶ በገመገመበት ወቅት ነው። ‹‹ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር ያለን ትስስር የላላ ነው›› ሲሉ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አቶ እንደሻው ጣሰው በወቅቱ ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸው ነበር።
አክለውም፣ ‹‹ለአስተማማኝ ሰላምና ለሕዝባችን ደኅንነት ሲባል ተቀራርበን የምንሠራበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም በዚህ ረገድ የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይገባል፤›› ሲሉ በአጽንኦት ጠይቀዋል። የፌዴራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ያለው ግንኙነት ችግር ያለበት በመሆኑ ቋሚ ኮሚቴው መፍትሔ እንዲበጅለት የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ፣ አቶ እንደሻው በወቅቱ ለቋሚ ኮሚቴው አሳስበው ነበር።
በሥራ ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ1996 ዓ.ም. ባወጣው ደንብ መሠረት የተቋቋመ ነው፡፡ ደንቡ፣ ‹‹የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማለት የአዲስ አበባ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ነው፤›› የሚል ትርጓሜ በድንጋጌዎቹ አስቀምጧል። ነገር ግን ስለ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መቋቋም በሚያትተው ምዕራፍ ሥር፣ የፖሊስ ኮሚሽኑ ተጠሪነት ለፌዴራል ፖሊስ መሆኑን ይደነግጋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሥልጣንና ተግባርን በሚዘረዝረው ክፍል ሥር ኮሚሽኑ በከተማው አስተዳደር ጥቅሞችና ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የመከላለከል፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችንና ተቋማትን የመጠበቅ፣ በኮሚሽኑ ሥልጣን ሥር የሚወድቁ የወንጀል መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ማጠናቀርና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ለከተማ አስተዳደሩ ማቅረብ ዋነኞቹ ናቸው።
ኮሚሽኑ በፌዴራል ፖሊስ አቅራቢነት በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር (በአሁኑ አደረጃጀት ሰላም ሚኒስቴር) አንድ ኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር እንደሚሾምለት ይደነግጋል። የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ሥልጣንና ተግባርን በሚዘረዝረዘው ምዕራፍ ሥር ደግሞ፣ ከንቲባው የኮሚሽኑን ሥራ በበላይነት የመምራትና የመቆጣጠር፣ ከኮሚሽኑ የሚቀርብለትን ዓመታዊ ዕቅድና በጀት እንዲሁም የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስ የሚሰጠውን አስተያየት በማካተት ተገቢው ውሳኔ እንዲሰጥበት ለከተማው ምክር ቤት ማቅረብና ኮሚሽኑ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የከተማው ነዋሪዎች ቅንጅትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ዋነኞቹ መሆናቸውን ደንግጓል። የኮሚሽኑ ኮሚሽነርን ሥልጣንና ተግባር በተመለከተ የተቀመጠው ድንጋጌ ደግሞ፣ የኮሚሽነሩ ተጠሪነት ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆኖ የኮሚሽኑን ሥራ በበላይነት መምራትና ማስተዳደር በዋነኝነት ተደንግጓል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን በባለቤትነት ለማስተዳደር፣ እንዲሁም የከተማዋ ሰላምና ደኅንነትን የማስጠበቅ ኃላፊነት ከእነ ተጠያቂነቱ ለመውሰድ የከተማ አስተዳደሩ የሚያቀርበውን ጥያቄ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ደግሞ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት መካከል የተፈጠረውን ተቃርኖ በተመለከተ የፓርላማው ግንዛቤ ምን እንደሆነ ለማወቅ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ የከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ ተገቢነት እንዳለው ገልጸዋል።
‹‹አዲስ አበባ ሰላሟ የተጠበቀ ከተማ እንድትሆን ካስፈለገ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን የማስተዳደርና ትዕዛዝ የመስጠት ኃላፊነት የከተማዋ ከንቲባ ሊሆን ይገባል፤›› ሲሉ አቶ ተስፋዬ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሰጥተዋል። በበርካታ የዓለም አገሮች ያለው አሠራርም ይኸው እንደሆነ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ኮሚሽኑን የማስተዳደርና የመምራት ኃላፊነት በውክልና ለከተማ አስተዳደሩ ሊሰጠው ይገባል ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።
ምክትል ከንቲባው ያነሱትን የሕግ ክፍተቶች ለመፍታት ፓርላማው ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ፣ አፈ ጉባዔ ታገሰ በውይይቱ ወቅት አስረግጠው ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሥራ አፈጻጸሙንና እያካሄደ ስለሚገኘው የተቋማዊ ሪፎርም ሥራዎች የተመለከተ ሪፖርት ታኅሳስ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።
በወቅቱም በአገሪቱ ያለውን የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ በተመለከተ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በኢትዮጵያ ያልተፈጠረ ችግር አልነበረም፡፡ አገሪቱ በሶሪያ የተፈጠረውን፣ በየመንና በሶማሊያ የተስተዋለውን ሁሉ ዓይታለች፤›› ብለዋል።
በማከልም፣ ‹‹እንደ አገር መቀጠል የቻልነው በሕዝቡ ጨዋነትና በፖሊስ ሠራዊቱ ፅናት ነው፤›› ብለዋል። በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የሚገኙ የፀጥታ ተቋማት ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ ተቀራርበው እየሠሩ እንደሚገኙ የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ በፖለቲካ አመራሩ በኩል ግን አሁንም መግባባት እንደሌለና በዚህ አካባቢ ያለው በሽታ ተለይቶ ሊታከም እንደሚገባው በአጽንኦት ተናግረዋል።
እሳቸውን ጨምሮ በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ የሚገኙ አመራሮች በሙሉ በተናጠል አባል ከነበሩበት የፖለቲካ ፓርቲ መውጣታቸውን ገልጸው፣ ወደ ተቋሙ የሚመጡ ኃላፊዎችም ሆኑ የሠራዊት አባላት ፖሊስ ብቻ ሆነው እንዲያገለግሉ፣ በግለሰብ ላይ ያልተንጠለጠለና ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከማንኛውም የፖለቲካ ተቋም ጋር ግንኙነት ሳይኖረው በነፃነት የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ የሚሠራ ተቋም ለመፍጠር ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል