ባፈለው የፈረንጆቹ ዓመት ኢንተርኔት በመዝጋት የከሰሩ ሃገራትን ዝርዝር ይፋ ያደረገ አንድ ጥናት “ዓለም በዚህ ምክንያት 8 ቢሊዮን ዶላር ከስራለች” ብሏል።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ኢንተርኔትን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የዘጉ ሃገራት ቁጥር ከምን ጊዜውም የላቀ ነው ሲል ኔትብሎክ የተባለው አጥኚ ድርጅት ይፋ አድርጓል።
ጥናቱ ላይ እንደተጠቀሰው በተለያዩ ሃገራት 122 ጊዜ ኢንተርኔት የተቋረጠ ሲሆን በጠቅላላ 22 ሺህ ሰዓታትን እነዚህ ሃገራት ያለ ኢንተርኔት አሳልፈዋል ብሏል።
ባለፉት 12 ዓመታት ጥናቱ ውስጥ የተካቱት መንግሥታት በሃገር ደረጃ ወይም በክልል ደረጃ ኢንተርኔትን ሆን ብለው አጥፍተዋል፤ ዋነኛው ዓለማው ደግሞ ተጠቃሚውን ፌስቡክ ከመሳሰሉ ከማህበራዊ ድር አምባዎች ለማገድ ነው።
ድርጅቱ የኢንተርኔት አዘጋግ ሂደቱን በሁለት ይከፍለዋል። አንደኛው ሙሉ በሙሉ የኢንተርኔቱን ባልቦላ መቁረጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማሕበራዊ ድር–አምባዎችን ከጥቅም ውጭ ማድረግ ነው።
ፌስቡክ፣ ዋትስአፕ፣ ትዊተር፣ ዩቲዩብ እና መሰል ድር አምባዎች ቢታገዱም ተጠቃሚዎች ‘ቪፒኤን‘ በመጠቀም ሊያገኟቸው ይችላሉ።
ጥናቱ ይፋ ባደረገው መሠረት አብዛኛዎች የኢንተርኔት መቋረጦች ከተቃውሞ እና አለመረጋጋት እንዲሁም ምርጫ ጋር የተያያዙ ናቸው። የባልቦላው መዘጋት በተለይ ‘በደሃ‘ ሃገራት በልማዳዊው ገበያ ላይ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ጥናቱ ደርሶበታል። ይህ ማለት ጥፋቱ ጥናቱ ላይ ከተቀመጠው በላይ ሊሆንም ይችላል ማለት ነው።
የኢንተርኔት መዘጋቱ የሰው ልጅ የመናገር ነፃነትን የሚገፍ ነው የሚለው ድርጅቱ ኢንተርኔት መዝጋቱ ለበለጠ አመፅ እንደጋበዘ ታዝቤያለሁ ይላል።
በዚህ ረገድ መካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪቃ ኢንተርኔት በመዝጋት የሚስተካከላቸው አልተገኝም። ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገራት ደግሞ ተከታዩን ደረጃ ይእዛሉ። እስያ በሶስተኛ ደረጃ የምትገኝ ሲሆን የደቡብ አሜሪካ ሃገራት በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ድርጅቱ ኢንተርኔት የዘጉ ሃገራትን ዝርዝር፤ ያጡትን ገንዘብ [በዶላር] እንዲሁም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከዚህ እንደሚከተለው አስቀምጧል።
-
ደረጃ
የሃገራቱ ስም ዝርዝር
የከሰሩት ገንዘብ [በዶላር]
የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር
1
ኢራቅ
2.3 ቢሊዮን
18.8 ሚሊዮን
2
ሱዳን
1.8 ቢሊዮን
12.5 ሚሊዮን
3
ሕንድ [የተወሰኑ ቦታዎች]
1.3 ቢሊዮን
8.4 ሚሊዮን
4
ቬንዝዌላ
1 ቢሊዮን
20.7 ሚሊዮን
5
ኢራን
611 ሚሊዮን
49 ሚሊዮን
6
አልጄሪያ
200 ሚሊዮን
19.7 ሚሊዮን
7
ኢንዶኔዥያ
188 ሚሊዮን
29.4 ሚሊዮን
8
ቻድ
125 ሚሊዮን
1 ሚሊዮን
9
ስሪ ላንካ
84 ሚሊዮን
7.1 ሚሊዮን
10
ምያንማር [የተወሰኑ ቦታዎች]
75 ሚሊዮን
100 ሺህ
11
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
61 ሚሊዮን
7 ሚሊዮን
12
ኢትዮጵያ
57 ሚሊዮን [1.8 ቢሊዮን ብር]
19.5 ሚሊዮን
ዚምባብዌ፣ ሞሪታኒያ፣ ፓኪስታን፣ ግብፅ፣ ካዛኪስታን፣ ቤኒን፣ ጋቦን፣ ኤርትራ እና ላይቤሪያ ሌሎች በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ ሃገራት ናቸው።
NURPHOTO
ከማሕበራዊ ድር–አምባ አንፃር ሲታይ ደግሞ ዋትስአፕ የተሰኘው መልዕክት መላላከያ ብዙ ሃገራት የዘጉት ሆኖ ተመዝግቧል። ፌስቡክ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፤ ኢንስታግራም ትዊተር እና ዩቲዩብ ተከታትለው ይመጣሉ።
ኢራቅ፣ ሱዳን፣ ሕንድ እና ቬንዝዌላ ኢንተርኔት በመዝጋታቸው ምክንያት 1 ቢሊዮንና ከዚያ በላይ ያጡ ሃገራት ሆነው ተመዝግበዋል። ይህም ምጣኔ ሃብታቸው ላይ ከፍተኛ ድቀት እንዳደረሰ የድርጀቱ መረጀ ያመለክታል። አራቱም ሃገራት ሕዝባዊ ተቃውሞን ለማብረድ ሲሉ ነው የኢንተርኔታቸውን ባልቦላ የቆረጡት።
ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ኢንተርኔቷን ለ274 ሰዓታት ዘግታለች። በተለይ ወርሃ ሰኔ ላይ [አማራ ክልል እና አዲስ አበባ ላይ ከተከሰተው የባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ] ኢንተርኔት በሃገሪቱ ለተወሰኑ ቀናት ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ነበር።
ከዚያ ባለፈ ሃገር አቀፍ የተማሪዎች ፈተና በሚኖርበት ወቅት ኢንተርኔት በበርካታ የሃገሪቱ ክፍሎች ተቋርጧል። ነገር ግን ኢንተርኔቱን የሚያስተዳድረው ኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ መንገሥት ይፋዊ መግለጫ አልሰጡም።
ከሃገር አቀፍ የኢንተርኔት መቋረጦች ባለፈ በተመረጡ አካባቢዎችም ተጠቃሚዎች ለቀናት ከኢንተርኔት ጋር ተቆራርጠው ቆይተዋል። ይህም ኢትዮጵያን ባላፈው ዓመት ብቻ 2 ቢሊዮን ብር ገደማ አሳጥቷታል።
ተያያዥ ርዕሶች