ከሚማሩበት የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ ሳለ ማንነታቸው ባልታወቀ ወጣቶች የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም ምላሽ አላገኘም።
ተማሪዎቹ ከታገቱ 50 ቀናት አልፏቸዋል። ከሶስት ሳምንታት በፊት ከእገታው ያመለጠችው አስምራ ለቢቢሲ አማርኛ ድምጿን ስትሰጥ ከደንቢ ዶሎ ወደ ጋምቤላ የማመላለሻ አውቶብስ ውስጥ ሳሉ መታገታቸውን ታወሳለች።
በወቅቱ ተማሪዎቹ ሲታገቱ እሷን ጨምሮ በቁጥር 18 እንደነበሩ ከእነዚህም መካከል 13ቱ ሴቶች እንደሆኑ የምታወሳው አስምራ እሷ ካመለጠች በኋላ ሁኔታውን ደንቢ ዶሎ ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ወዲያኑ ማስረዳቷን ታነሳለች።
ብዙዎቹ ቤተሰቦች ተማሪዎቹ ስለመታገታቸው የሰሙት ሕዳር 24፤ 2012 ዓ.ም. ነው። ከታገቱ በኋላ ለሁለት ሳምንታት በስልክ ያገኟቸው እንደነበርም ይናገራሉ። ከዚያ በኋላ ግን ተማሪዎቹ ያሉበትን ሰማሁ ያለ አልተገኘም።
ይህንን ተከትሎ ጥር 2፤ 2012 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ ንጉሱ ጥላሁን በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው ቀርበው 21 ተማሪዎች መለቃቀቸውን፤ ነገር ግን 6 ተማሪዎች አሁንም በአጋቾች እጅ እንዳሉ ተናገሩ። ይህን ተከትሎ ያናገርናቸው የታጋች ተማሪ ቤተሰቦች ግን ከመንግሥትም ሆነ ከልጆቻቸው ምንም የሰሙት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ አማርኛ አረጋገጡ።
ከዚያ በኋላ ባሉ ሁለት ሳምንታት የታጋቱትን ተማሪዎች በተመለከተ ከመንግሥት የወጣ ይፋ መረጃ የለም።
አብዛኛዎቹ ተማሪዎች አማራ ክልል በምትገኘው የአዲስ ዘመን ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። የተማሪዎችን መታገት ተከትሎ ከቀናት በፊት ወደ አዲስ ዘመን ያቀናው የቢቢሲ ዘጋቢ ከተማዋ ሃዘን እንዳጠላባት ይናገራል።
የታጋች ቤተሰቦች ፊታቸው ጠቁሮ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው ነው ያገኘኋቸው የሚለው ዘጋቢያችን ቤተሰቦችን ማነጋገር እጅግ አሳዛኝ እንደነበር ያስረዳል።
ከታጋች ተማሪዎች መካከል የአንዷ አባት የሆኑት ግለሰብ «በጥር 2 ተለቀዋል ስንባል ደስ ብሎን ነበር፤ ነገር ግን እስካሁን ከልጆቻችን ጋር አልተገናኘንም። መንግሥትም ያለን ነገር የለም። ገድለውብን ይሆናል ብለን እየፈራን ነው። በዚያ ላይ ልጆቹ አይተውት የማያውቁትን ነገር ሲያዩ ይደነግጣሉ ብለን ሁላ እናስባለን። ሞተውም ከሆነ እውነቱን ነግረውን ቤተሰብ ጋር ተሰባስበን አልቅሰን እርማችንን ብናወጣ ይሻለናል፤ እንዲህ በየቀኑ ምን ሆነው ይሆን እያልን በሰቆቃ ከምንኖር” ይላሉ።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው ከታገቱ ተማሪዎች ወላጆች መካከል የተወሰኑትን አነጋግሬአለሁ ይላሉ። ምክትል ርዕሰ–መስተዳድሩ፤ እንደ ሀገር ተማሪዎችን ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት አናሳ በመሆኑ ፈጥኖ መፍትሔ ማግኘት አልቻለም ባይ ናቸው።
«በተለይም አከባቢውን የሚያስተዳድረው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የፌዴራሉ መንግሥት ትኩረት መስጠትና ተማሪዎችን ማስለቀቅ አለባቸው።» በማለት ለክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
የማሕበራዊ ሚድያ ጩኸት
የተማሪዎች መታገት ከተሰማ ወዲህ ጀምሮ በማሕበራዊ ሚድያዎች በተለይም በፌስቡክና ትዊተር አለፍ ገደም ያሉ ዘመቻዎች መካሄድ ጀምረው ነበር። ከጥቂት ቀናት በፊት ጀምሮ ግን የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ጩኸታቸውን በሰፊው ማሰማት ጀምረዋል።
ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችም ዘመቻውን ተቀላቅለዋል። በተለይ ትዊተር በተሰኘው ድር–አምባ #Bringourgirlsback #Bringourstudentsback #WhereAreTheStudents? #ተማሪዎችየትገቡ? የተሰኙ ዘመቻዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።