Sunday, 26 January 2020 00:00

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ

   ‹‹ወደ ድል የምንሻገርበት ፈተና ስለሆነ ተስፋ እንዳትቆርጡ››

መንግሥት ከጋሞ ሥርዓት ቢማር፣ አገር ለዚህ ሁሉ ቀውስ አትዳረግም ነበር

አገርና ሥልጣኔን የገነቡ አባቶች ሊፀለይላቸው ሲገባ እንዴት ይረገማሉ?!

ተማሪዎቹ ሁሉ ‹‹ሁለተኛ እጃችንን ለጥፋት አናነሳም›› ብለው ቃል ገብተዋል

በጋሞ ባህላዊ ሥርዓት ካኦ ታደሰ ዘውዴ፤ ከዘር ሲቀባበል በመጣው የንግስና ሥርዓት 15ኛው ካኮ (ንጉስ) ናቸው፡፡ በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊው ትምህርትና እውቀት የታነፁ ናቸው፡፡ በማኔጅመንትና በኢኮኖሚክስ ሁለት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፤ በህግ ትምህርትም ዲፕሎማቸውን ካገኙ በኋላ አቃቤ ህግናዳኛ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ለጥምቀት በዓል ወደ 60 የሚጠጋ ቁጥር ያላቸውን የጋሞ አባቶች፣ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪ ህብረት ተወካዮች፣ የዩኒቨርስቲው መምህራን ተወካዮችና የወጣት ተወካዮችን በመምራት፣ ‹‹የጋሞ አባቶች የሰላምና የአንድነት ጉዞ” አድርገዋል ከአርባ ምንጭ እስከ ጎንደር፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ካኦቶ ታደሰን በጉዞውና ባከናወኗቸው የሰላምና እርቅ ሥራዎች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡

የጐንደር ጉዟችሁን ከማንሳቴ በፊት አንድ ጥያቄ ላስቀድም፤ በጋሞ ባህል አንድ ካኦ የሚቀየረው ምን ሲሆን ነው?
በስርዓታችን አንድ ካኦ የሚቀየረው በዋናነት እድሜውን ሲጨርስ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ስሞት የመጀመሪያ ወንድ ልጄ ይተካል፡፡ ነገር ግን ከዚያ በፊት ካኦዎች የጋሞን ስርዓት ከጣሱ፣ ለምሳሌ ሴሰኛ ከሆኑና ሚስታቸውን አስቀምጠው ከወሰለቱ፣ አካለ ጐደሎነት ካለ፣ ሀሰተኛ ፍርድ ከበየኑ፣ ፍትህ ካዛቡና በጥቅም ፍርድ ከሰጡ፣ ለወገን መፍረድና ማድላት ከታየባቸው… ከዚህ ድርጊት እንዲታቀቡ በአማካሪዎች ይነገራቸዋል:: ምክሩን ተቀብለው ካስተካከሉ እሰየው፤ ካልሆነና በዚያው ጥፋት ከቀጠሉ አማካሪዎቹ ወይም ባህላዊ ምክር ቤቱ ካኦውን ከስራው ያግድና ያስቀምጣል፡፡ ከዚያም የካኦው ታናሽ ወንድም ወይም የደረሰ ልጅ ካለ፣ ሥርዓቱን በሞግዚትነት ይመራል፡፡ ካኦው ታግዶ ቁጭ ይልና የሰራውን ሃጢያት ተናዝዞ፣ ንስሀ ገብቶ ሲጨርስ፣ ህዝቡ ከተቀበለውና ትክክለኛ የባህሪ ለውጥ ከታየ፣ ህዝቡ እንደ አዲስ ያመጣና ቦታው ላይ ያስቀምጠዋል፤ መምራቱንም ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ የእኛ ባህላዊ ንግስና ብዙ ፈተና ያለበት፤ ብዙ ቁጥጥር የሚደረግበት፤ ልቅ ያልሆነ ትልቅ ንግስና ነው፡፡ ያልተማከለ አስተዳደር ያለበት፣ የስልጣን ተዋረድ ያለውና ለዘመናዊው አመራር ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡ መንግስትም ከጋሞ ስርዓት ጊዜ ወስዶ ቢማር፣ አገር ለዚህ ሁሉ ቀውስ አትዳረግም ነበር፡፡ ቅድም እንደነገርኩሽ፤ ከኔ በፊት 15 አያቶቼ ነግሰው አልፈዋል፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ አውሮፓዊያን እደጃችን ላይ መጥተው ድንኳን ተክለው ያጠኑ ነበረ፡፡ የእኛ አያቶች ምን እንደሚሰሩ አያውቁም፡፡ ነገር ግን አንድና ሁለት አመት ቆይተው ብዙ ነገሮችን ያጠናሉ:: ታሪካችንን፣ ባህሉን፣ የአስተዳደር ስርዓቱን ሁሉ አጥንተዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ነገር ወስደው ዛሬ ለዓለም መልሰው እያስተማሩ ነው ያሉት:: ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ በመሆኗ፣ አሁን ዓለም ላይ የሚታየው የህንፃ ዲዛይን ከጋሞ ባህላዊ ቤት የተቀዳ ነው፡፡ ድንኳናቸውንም ብታይ፣ ወይ ክብ ነው ወይም ደግሞ ሬክታንግል ነው፡፡ የጋሞ ቤት ክብ ነው፡፡

ከዛሬ 10 ዓመት በፊት አንድ አውሮፓዊ ፕሮፌሰር መጥቶ ሲያጠና፣ በስራችን ምክንያት አውሮፓን አሜሪካንና አፍሪካን ለልምድ ልውውጥ አዘዋውሮናል፡፡ በዛን ጊዜ ምን እንዳለኝ ልንገርሽ… “ይሄ የእናንተ ሀብት ነው፤ ሌላው ቀርቶ ከድንኳን ሰሪዎች የፈጠራ መብት ባለቤትነት (ፓተንት ራይት) ቢኖራችሁ ኖሮ፣ ዛሬ ህዝባችሁን ሙሉ የሚመግብ ሀብት ታገኙ ነበር፡፡ ስልጣኔ በሙሉ የተወሰደው ከዚህ ነው” ብሎ በአንደበቱ ነግሮኛል፡፡ እኛ ራሳችንን ባህላችንን ንቀናል፤ ‹‹ይሄ ኋላ ቀር ነው፤ ይሄ አልሰለጠነም›› እንላለን፡፡ ግን ትክክል አይደለም፡፡ እኔ ዘመናዊውን ትምህርትም ተምሬያለሁ፡፡ ከአንድም ሁለት ዲግሪ አለኝ፤ በማኔጅመንትና በኢኮኖሚክስ ማለት ነው፡፡ በህግም ዲፕሎማ አግኝቼ፣ ዳኛም አቃቤ ህግም ነበርኩኝ፡፡ ባህልን ከዘመናዊ እያሰናሰልኩ ነው የምሰራው፡፡ ዘመናዊውን ከባህሉ እያቻቻልኩ ነው ስሰራ የቆየሁት፤ ዝም ብዬ ባህላዊውን ንግስና ይዤ ብቆይ ኖሮ እዚህ አልደርስም ነበር:: ዓለም ምን ይፈልጋል? ትውልዱ ምን ይላል? የሚለውን ጠንቅቆ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ አሁን እዚህ መጥተን የምናስተላልፈው መልዕክትም፤ ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ሥልጣኔ ያስፈልጋል፡፡ ስልጣኔ ግን መሰረታችንን ሊያሳጣንና ሊያስጥለን አይገባም፡፡ አገር በቀል እውቀት፣ አገር በቀል ዕፅዋት፣ አገር በቀል አመጋገብ… ትልቅ ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል በህንፃ ግንባታ ሲካን፣ ደቡቡ ክፍል ደግሞ በአልባሳት ጥበብ የተካነ ነው፡፡ አመጋገብንም ብትወስጂ፤ በእኛ አካባቢ አንድ የመጨረሻ ደሃ የሚባል ገበሬ፣ በቀን ውስጥ ስድስትና ሰባት አይነት ምግብ ይመገባል፡፡ ይህን የሚመገበው ከጓሮው ነው፡፡
የአገሪቱን ወቅታዊ ችግር እንዴት ያዩታል?