Monday, 27 January 2020 00:00

Written by  ዮሃንስ ሰ

ባለፉት ዓመታት፣ በርካታ አደገኛ ቀውሶች የተደራረቡባት አገራችን፣ ለጥቂት “ብትተርፍም”፣ እስካሁን ገና ሙሉ ለሙሉ ያልተረጋጋችና ያላገገመች አገር ናት፡፡ ዘንድሮ እንደገና፤ በፖለቲካ ምርጫ ሰበብ፣ ለሌላ ዙር የጥፋት ቀውስ ከዳረግናትና ከታመሰች፣ መዘዙ ይበዛና፤ መከራችን ይከብዳል፡፡ለወትሮውም፣ ከችጋር ጋር የተቆራኘው የዜጐች ኑሮ፣ በአምስት ዓመታት ተከታታይ ቀውሶች ሳቢያ፣ ክፉኛ እየተናጋ ምንኛ እንደተጐሳቆለ፣ ማንም ሊክደው አይችልም፡፡ በዋጋ ንረት ምክንያት ብቻ፣ የስንቱ ሰው “ቁጠባ” የቱን ያህል ዋጋ እንዳጣ፣ የስንቱ ሰው የስራ ጅምር፣ የግንባታና የኢንቨስትመንት ውጥን በእንጥልጥል እንደቀረ፣ የስንት ሚሊዮን ዜጐች የእለት ጉርስ እንደሟሸሸ አስቡት፡፡
በአምስት ዓመት ልዩነት፣ ኑሮ፣ በእጥፍ ተወዷል፡፡ አንድ ሺ ብር ስንከፍልባቸው የነበሩ ነገሮች፣ ዛሬ ሁለት ሺ ብር ይፈጃሉ እንደማለት ነው፡፡
እንደምንም ተጣጥሮና ቆጥቦ፣ “ባጃጅ እገዛለሁ” ሲል የነበረ ወጣት፣ የቆጠበው ገንዘብ፣ ከትናንት ዛሬ፣ በዋጋ ንረት ሳቢያ እየረከሰ፣ ጥረቱ ከንቱ ይሆንበታል፡፡ “ግማሽ ያህል” ነበር ያኔ የሚጐድለው፡፡ አምስት አመት ሙሉ ቆጥቦ፣ “አሁን አሟላሁ!” ሲል፤ ለካ” በዚሁ ጊዜ ውስጥ፣ “ብር” ረክሷል፡፡ የባጃጅ ዋጋ፣ ከእጥፍ በላይ ንሯል፡፡ እናም፤ የወጣቱ ቁጠባ ከንቱ ሆነ:: ዛሬም፤ “ግማሽ ያህል ይጐድለዋል” ባጃጅ ለመግዛት፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በዋጋ ንረት ሳቢያ፣ በየከተማው፣ ግንባታ እየተቋረጠ፣ ኢንቨስትመንት እየተጓተተ፣ የፋብሪካ ስራ እየተስተጓጓለ፣ ብዙዎች ለኪሳራ ተዳርገዋል፡፡
ነባር ቢዝነሶች ተሰናክለው፣ ነባር የስራ እድሎች ተዘግተዋል፡፡ የግል ኢንቨስትመንቶች ተደናቅፈው፣ አዳዲስ የስራ እድሎች ከጅምር ተጨናግፈዋል፡፡
አዎ፤ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ መንግስት ጥሯል፡፡ የመንግስትን ወጪ እንደቀድሞው አለቅጥ ከሳማበጥ፣ በጀቱንም መረን ከመልቀቅ ታቅቦ፣ አደብ ለመግዛት ሞክሯል፡፡ ገንዘብ አለመጠን ከማተምና ብድር ከማግበስበስም ቆጠብ ብሏል፡፡
ነገር ግን፣ የገንዘብ ህትመት በአግባቡ ተመጥኖ፣ ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር ተስተካክሏል ማለት አይደለም፡፡ የብር ህትመት ከቀድሞው ባይብስበትም፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሰላም እጦት ጭምር በመዳከሙ፤ በገንዘብ ህትመት ሳቢያ የሚፈጠረው የዋጋ ንረት ከፍተኛ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ፣ በዋጋ ንረት ምክንያት ብቻ፣ በአገር ኢኮኖሚና በዜጐች ኑሮ ላይ የሚደርሰው ጉዳት፣ እጅግ ከባድ እንደሆነ ለመግለጽ ፈልጌ ነው፡፡ በዚህ ላይ፣ በመንግስት የቢዝነስ ተቋማት አማካኝነት የሚመጣው ጥፋትም አለብን፡፡
የመንግስት የቢዝነስ ድርጅቶችና ፕሮጀክቶች፣ በጥቂት አመታት ውስጥ የፈጠሩት ችግር፣ በዓይነትም በመጠንም፣ አገሪቱን ከዳር ዳር አዳርሶ ኢኮኖሚውን አብረክርኳል:: ያባከኑት ሃብት፣ በቢሊዮን በቢሊዮን ብር እየዘገኑ እንደዘበት የመበተን ያህል ነው:: በማግስቱ ከዚህም ከዚያም እየተበደሩ እንደገና ያባክናሉ፡፡ ይሄውና አገሪቱ የእዳ ክምር ተጭኗታል፡፡ ይህንን ግዙፍ ችግር፣ ለማቃለል እየተሞከረ መሆኑ ጥሩ ነው፡፡
ግን ከባድ ስራ ነው፡፡ በግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶችና በመንግስት የቢዝነስ ድርጅቶች በኩል የሚከሰተውን የሃብት ብክነት፣ ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ ይቅርና፤ በግማሽ ያህል ለመቀነስ እንኳ፣ አመታትን ይፈጃል፡፡ የተወሰኑ የስኳር ፕሮጀክቶችን ለግል ኩባንያዎች የመሸጥ እቅድ፣ በወር በሁለት ወር የሚያልቅ ቀላል ስራ እንዳልሆነ እያየነው ነው፡፡
አላማን ሳይስቱ፣ አባካኝ የመንግስት ቢዝነሶችን የመሸጥ እቅድ እንዳይጓተት እየተጉ፣ ግን ደግሞ በጥድፊያ ለመገላገል “ከህግና ስርዓት” ሳይወጡ፣ ለበርካታ ዓመታት በጽናት መጓዝን ይጠይቃል የሃብት ብክነትን የመቀነስ አላማ:: ለዚህም ሰላም ያስፈልጋል፡፡