የታገቱት ተማሪዎች ነጻ ይውጡ!
ለታገቱት ልጆቻችን፣ እህትና ወንድሞቻችን ድምጽ የሆናችሁ ሁሉ ሕዝባዊ ወገናዊነታችሁ ይቀጥል!
በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን መከታተል ሳይችሉ ቀርተው ወደቤታቸው ለመመለስ መንገድ የጀመሩ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች እገታ ተሰማ። እነሆ እገታው ከተካሄደ ሁለት ወራት ቢያልፉም እስከአሁን ስለሁኔታው የጠራ መረጃ የለም። ይህ የሀገር ማፈሪያ የሆነና ለማንም ኢትዮጵያዊ፣ በተለይም ለወጣቶቹና ለወላጆቻቸው አስደንጋጭ እና የስቃይ ምንጭ ለሆነ ጉዳይ ከመንግሥት በኩል ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱ እጅግ አሳዛኝ ነው። ምክንያቶቻችን ምንም ይሁኑ ምንም በዚህ አሳዛኝ ክስተት ላይ አፋጣኝ አቋማችንን በመግለጽ ለተማሪዎቹ ድምጽ ሳንሆን፣ በመንግሥትም ላይ ተጽእኖ መፍጠር ሳንሞክር ሁለት ወራት ያለፉብን፤ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳችንን ዞር ብለን እንድናይ ግድ ግድ ይለናል። ባለፉት ሁለት ወራት ለታገቱት ተማሪዎች ድምጽ ለመሆን ሳታሰልሱ የጣራችሁ ወገኖች የብዙዎችን ዝምታ ልትሰብሩ በመቻላችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል። ባለፉት ጥቂት ቀናት ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ የሁሉም መነጋገሪያ ሊሆን በቅቷልና!
የተፈጠረው ጫና የመንግሥት ባለስልጣናት ዘግይተውም ቢሆን ወደሥፍራው እንዲሄዱም ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጥሯል። ሆኖም ዛሬም ቢሆን በጉዳዩ ላይ ይህ ነው የሚባል ግልጽ መረጃ አልተገኘም። ስለዚህም ታጋቾቹ ያሉበት ሁኔታ በአፋጣኝ ግልጽ እንዲደረግና ይህ ታላቅ የሀገር ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ፣ ልጆቻችንም በሰላም ወደየቤተሰቦቻቸው ይመለሱ ዘንድ ኢሕአፓ ይጠይቃል ይተጋልም፤ በተለያዩ መንገዶች ከምትታገሉ ወገኖችም ጎን እንደሚቆም ቃል ይገባል። የሚደረገው ትግል ለወቅታዊው ችግር መፍትሄ የሚሰጥና በአጠቃላይ በአገራችን ውስጥ ለተፈጠረው የዘረኝነት እና የጥላቻ አባዜ ዘላቂ መድሀኒት እንዲሆን ረጅም ጉዞ መራመድ እንዳለበትም ፓርቲያችን ያምናል።
ኢትዮጵያ በሰላምና በአንድነት ለዘላለም ትኑር!
ቆንጂት ብርሃን
የኢሕአፓ መሪ