ታጠቅ መ ዙርጋ ፤
3 February 2020
የሀገራዊና የሕዝባዊ ሉዓላዊነታችን ጸሮች፣አጥፊዮቻችንና ገዳዮቻችን እንደ ብርቅዬ መሪዮቻችን፣ልጆቻችን ወይም ወንድሞቻችን አድርገን ፥ ስናንግሥ፣ ስናሞካሽ፣ስናዳንቅ ወዘተ..ኖረናል። በዚህ አርእስት አጭር መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።በቅድሜያ ከመልዕክቴ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት የአገራችን ፖለቲካዊ ታሪካችን ወይም ኩነቶች በጣም አጠር አጠር ባለመልኩ አስጨብጣለሁ።
ሀ) መንግሥቱ /ሃይለማርያም ፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለረዥም ዓመታት ታግሎ ያገኘውን ድል፤ መስከረም ሁለት 1967 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግሥት የቀማበትን ቀን የአብዮት ቀን ብሎ ሰየመው።ከዚያ በመቀጠል ዙፋኑን ይቀናቀኑኛል ፣ እንደልቡ እንዳይልጋልብ እንቅፋት ይሆኑብኛል ያላቸውን ሁሉ በጥይት መመንጠር ጀመረ።
ለነጻነት፣ለፍትኅ፣ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓት ወዘተርፈ አርበኞች የነበሩ፤ ከግለኝነት የፀዱ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የኖሩ፤ ከ300,000 -500,000 የሚደርሱ ዕንቁ ዜጎች ጨፈጨፈ (carnaged)። የገደለበትን ጥይት ዋጋ ክፈሉኝ ብሎ አንድ አስክሬን በ250 ብር ሸጠ። ሟቾቹ 250 ብር የመክፈል አቅም ከሌላቸው ቤተሰብ የሆኑትን አስክሬናቸው ቆሻሻ በሚሰበስብ መኪና ወደ አንድ ጫካ ወይም ዋሻ እየተወሰዱ ለጅቦችና ለአሞሮች ተሰጡ ፤ በአንድ የጅምላ መቃበር ተቀበሩ ።
ወላጅና ዘመድ አዝማድ እንዳያለቅስና የሃዛን ልብስ እንዳይለበስ ተከለከለ። የሚያለቅስና የሃዘን ልብስ የሚለብሱትን ለመሰለልና ለማሰር የቀበሌ ካድሬዎች አሰማሩ። ወንድም ተጠርጥሮ ሊዙት እቤት ስሄዱ ካልተገኘ፣ ምንም ማታውቀው እህት ወስዶ መግደል። ታላቅ ወንድም ተጠርጥሮ ሊዙት ካልቻሉ ታናሽ ወንድም ወስደው መግደል። ባል ተጠርጥሮ እሱ ካጡት ሚስት ወስዶ መገደል። ልጆች ተጠርጥረው እነሱ መያዝ ካልቻሉ አባትና እናት ወስዶ መግደል ። አንድም ፣ ሁለትም፣ ሶስትም፣ አራትም፣ አምስት ም ፣ ስድስትም ልጅች የነበሯቸው ወላጆች፣ ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት ባልሞላ ግዜ ሁሉንም ልጅ አልባ አደረጓቸው ። እናቶች መውለዳቸውን የረገሙት፣ እንደ ሃጥያት የቆጠሩበት፣ መካን መሆን እንደ ጸጋ የተቆጠረበት ግዜ።
በደርግ ዘመን ከ12 -40 ዓመት ዕድሜ ከነበረው ትውልድ አብዛኛው ዘር ሳያስቀጥል ፤ልጅ አልባ ሆኖ አለፈ። በሰው ልጅ ታሪክ ሬሳ/አስክሬን ስለሽጠ ገዢ ሰምቼም አንብቤም አላውቅም።
ለነዚያ ዓይነት የመንግሥቱ ፍጹም ፋሽስታዊ ድርጊቶች አፀፋ ማመጽ ፣መሸፈት፣እምቢይ ማለት ሲገባ፦
1) መስከረም ሁለት 1967 ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቁጣ ቀን መሆኑን እየታወቀ ፣የአብዮት በዓል በመባል በየዓመቱ በውድም ሆነ በግድ ፤ከታላቁና ከቆራጡ መሪያችን ጋር ወደፊት ! እያልን ለ17 ዓመታት በመፈክር እያዳነቅን፣ እያጋነን ፣እያሳበጥን ወዘተርፈ አከበርን ።
2) ለመጨፍጨፍ ሲያቅድ ወይም ካስጨፈጨፈ በኋላ ሕዝብ እሰይ ፣ ጥሩ ሥራ እየሰራህ ነው ወይም ደግ አድርገሃል እንዲልለት ፣ በቀበሌ ካድሬዎች ጠመንጃ አፈሙዝ ተከቦና ተገፍቶ መስቀል አደባባይ ከጠዋት እስከማታ በፀሃይ ሲያንቋቁት፣ ዝናብ ሲያስደበድቡት፣ፀረ–አብዮተኞች ይመንጠሩ! በፀረ አብዮተኞች ላይ እንዘምታልን! በአናርኪስቶች ላይ እንዘምታለን! ወዘተርፈ እያለ ይውል ነበር።
ለ) ወያኔዎች፦ ወያኔዎች ሶስት ፀረ ኢትዮ– ሉዓላዊነትና ፀረ ሕዝባዊ አንድነት) መርሆች ይዘው ነው በረሃ/ጫካ ገብተው ለ17 ዓመታት ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር የተዋጉት ። ( 1) ትግሬ እነሱ ከሚሉት የአማራ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት (2) በኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ፦ የፖለቲካ፣የኢኮኖሚ፣ የባህል፣የቋንቋ ወዘተርፈ የኢ–እኩልነት መብቶች የሚፈቱት ብሄር ብሄረሰቦች ተለያይተው በመኖር ብቻ ነው (3) ኤርትራን ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነጻ አደርጋለሁ ብሎ ለተነሳው ኢሳያስ አጋር ለመሆን።
በመሆኑም ከላይ የጦቆምኩትን 3ኛውን ዓላማቸውን ያሳኩት ገና ጫካ እያሉ ነው። ኤርትራን ካስገንጠ ሉና የባህር በሮቻችን ካስወስዱ በኋላ ነው ወደ አዲስ አበባ የገሰገሱት።
ወያኔዎች ግንቦት 20 1983ዓ.ም የፋሽስቱ መንግሥቱ ሃ/ማ ዙፋን ለመረከብ አ/አ ሲገቡ የወያኔዎች ደባ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ ሁሉንም የአ/አ ሕዝብ ባሆንም ከመንግሥቱ የከፉ አይሆኑም በማለት እህልና ውሃ በማቅረብ እንኳን ደኅና መጣችሁ ብሎ የተቀበላቸው ማኅበረስብ እንደነበረ ተስተውሏል ።
ግንቦት 20/1983 ዓ. ም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን በሞኖፖል እየገዙ – ለማጥፋት፣ለመከፋፈል፣ ለመግደል ፣ ለመበዝበዝ ወዘተርፈ የሚያስች
ሥልጣን የተቆናጠጡበት ቀን ነው ።ከዚያ ዕለትና ዓ/ም ጀምሮ ፦ ከወል (ታሪክችን፣ባህላችን፣ሕባዊ አንድነታችን ፣ማኅበራዊ ትሥሥራችን፣አውደ በአሎቻችንና ሥነ–ልቦናችን) ለማፋታት፣ ለማለያየትና ለማድፍረስ ፤
-
አገር በቀል የዘር መድሎ/አፓርታይድ ፣ የብሄር ቋንቋን ተኮር የአገዛዝ ክልል እና የብሄር ብሄረሰቦች ክብረ በዓል ቀን ሥርዓት(system) ዘረጉ። የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ማለት እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰቦች ስለተናጥል ማንነት እንጂ ስለጋራ ማንነት ወይም እሴቶች እንዳያስቡ ለማድረግ የታቀደ አስተምሮት (discourse) ነው ።
-
አበይት የንግድና የኢኮኖሚ ዘርፎች <በገዢዮችና በገዢ ጎሳዎች ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መመርያ ነድፏል።
-
ታሪካችንና ባንድራችንን አንቋሽው ተረኩ፣ ሰንደቅ ዓላማችን የሰይጣናዊ እምነት ተከታዮችን (the satanic cult) ምልክት ባለበት ሰንደቅ ዓላማ ተኩት።
-
ማሰብና መጠየቅ የማይችል፣ የወያኔዎች ታዛዥና አገልጋይ ሆኖ መኖር የሚያስችል የትምህርት ሥርዓት አዋቀሩ።
-
እንደ መንግሥቱ ሃ/ማ እዩልኝ ስሙልኝ ሳይሉ እሱ የገደለውን ያህል በሥውር ገደሉ ፤ በጅምላ መቃብር ቀበሩ
-
የሂትለርን (the Aryan race ) ሞዴል/ናሙና በመጠቀም ፣ ትግሬአውያት ያልሆኑ ሚስቶች ትግሬአያውያን ከሆኑ ባሎቻቸውና በእነሱ መካከል ከተወለዱ ለጅ/ጆቻቸው ተነጥለው እንዲባረሩ ፖሊሲ/መመርያ አወጡ። በመሆኑም የቤተሰብ ሕይወት አናጉ፣ አቃወሱ ፣አካል ሰነጠቁ ።ይህንን በተመለከተ በዲስፖራውም ዓለም ብዙ ጉድ ታይቷል።
ለእነዚህ ድርጌቶች አጸፋ አመጽና እምቢተኝነት መሆን ሲገባው፤
አንድም በውድ፣ ሁለትም በፀረ–ሕዝብ ካድሬዎቻቸውን ቅስቀሳና አስገዳጅነት ፦ ለእኛ የመከራና የውርደት ቀን ለእነሱ የድል ቀን የሆነው ግንቦት 20 ሲያከብሩ ፤ ሕዝብ አደባባይ እየወጥ አከበርላቸ። ገዢያችን የነበረው የወደል ውሻው (top dog) መለስ ዜናዊ አገዛዝ በመደገፍ አደባባይ ወጥቷል ።
የምዕራባውያን ጋዜጠኞች፣የመንግሥታት መሪዮች (በተለይም በምዕራባውያንና በአረቦች) ፦ ባለራኢ መሪ! ባለልማት መሪ! ወጣት መሪ! ሙሉ አፍሪካ መግዛት የሚችል መሪ! የተማረ፣ የተመራመረ መሪ! በህክምና ሞያ የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረ መሪ፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ በተማረ ሰው ስትመራ የመጀመርያ ግዜ በተሰኙ መፈክሮችና ዲስኩሮች ተካበ/ተቆነነ። እነዚህን መፈክሮችና ዲስኩሮች በአገር ቤትም በዳያስፖራውም ዓለም በበርካታ ትግሬ ባልሆኑ ኢትዮጵያውያንም ሲደሰኮርና ሲለጠጥ አስተውለናል።
ይህንኑ አጥፊያችን ሲሞት ብሄሩ ወይም አገሩ አለቀሰለት ለማሰኘት ፦አካለ ስንኩላልንና ዱኩማንን ሳይቀሩ የሁሉንም የኢትዮትዮጵያ ክፍላተ ሃገራት ሕዝብ በነቂስ አደባባይ እንዲወጣ አስገድደው ለብርቅዬ መሪያቸውን ሲያለቅሱ ፤ እንባቸውን በተለቪን መስኮት እንዲታይ አደረጉ ።
ከዚህ በተጻራሪ – የብሪቲሽ ጠቅላይ ሚኒስተር ማርጋሬት ታቸር እ.ኤ.አ በ8 ኤፕሪል ሙታ እስከ 17 ኤፕሪል 2013 የተቀበረችበት ቀናት፣ በመሞቷ ያዘኑ ሲያለቅሱ ፤ በመሞቷ የተደስቱ አደባባይ ወጥተው ሲጨፍሩና ሲደንሱ ታይቷል። እ.ኤ.አ ከሜ 1979 -1990 በነበሩ የሥልጣኗ ዓመታት ፥ የሠራተኛ ማህበራት አዳከመች ፣ፋብሪካዎችና ኢዱስትሪዮች ወደግል በማዞር በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች ከሥራቸው ተወገዱ፣ ኮምኒቲ የሚባል ነገር የለም ሁሉ የግሉ ይሩጥ/ይኑር በማለት የ(social Darwinism Theory) ተግባራዊ በማድረግ ብዙ ድሆችና ችግረኞችን ጎዳች። ስልሆነም ያንን ጥቃት የደረሰባቸውና ያንን ይቃወሙ የነበሩ የማኅበረሰቡ አካሎች ( ‘we are happy you are gone, ,, ,, ,,’) በማለት በቤቷ ደጃፍ አበባ አኖሩ፣ በመሞቷ ድስታቸውን የሚገልጹ መፈክሮች እያሰሙ እና የውሸት የአስክርርን ሳጥን ተሽክመው የተቀብረችበት ቦታ ወስደው አስቀመጡ። ያ ሁሉ ሲሆን ከፖሊስም ሆነ ከፀጥታ አካል ምንም አልደረሰባቸውም። አይ ነጻነት! ነጻነት ማለት ይህ ነው ! በውቅቱ ከላይ በንጽጽር የገለጽኳቸውን ኩነቶች በእንግሊዘኛ ጽፌ ለድረ ገጾች ማሰራጨቴ አስታውሳለሁ ።
ሐ) ኢሳያስ አፈወርቂ (ለእኔ ኢሳያስ አፈ ጨርቂ) ፦ በቀን አንድ ግዜ መብላት ከማይችሉ የኢትዮጵያ – አርሶ አደሮች ፣ሰርቶ አደሮች ፣ንግዶ አደሮች ወዘተርፈ በተሰበሰበ ቀረጥ/ታክስ እስከ ዩኒብርስቲ የመማር ዕድል አግኝቷል። አሁን የደረሰብትን ቦታ ለመድረስ ማለት የኤርትራ ፕሬዝዴንት ለመባል ፣ በፈጠራ ታሪክ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነው ብሎ ፈረጅ።
ስለሆነም ፀረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አቋም አንግቦና ጠመንጃ አንስቶ እ.አ.አ ከ1961 – 1991 እንዲሁም ከ1998- 2000 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ባደረገው ጦርነት የግማሽ ሚሊየን (500,000) ኢትዮጵያውያንና ኤርትራ ውያንን ሕይወት መጥፋት እንዲሁም የ700,000 ኤርትራውያን መሰደድ ምክንያት የሆነ መሰሪ ሰው ነው።
ወያኔዎች ትግራይን ገንጥሎ ለማስተዳደር ሲደራጁ – ትጥቅ፣ እስትራተጂና ስልት በመንደፍ አደራጅቷቸዋል ። በተመሳሳይ ያለወያኔዎች እገዛ በምንም ታዓምር የኤርትራ ክ/ሀገራችንና ሁለቱ የባህር በሮቻችን በኢሳያስ ቁጥጥር ሥር አይውሉም ነበር።
ወያኔዎች የኢትዮጵያን በትረመንግሥት ለመጨበጥ ያስቻላቸው በዋናነት መንግሥቱ ሃ/ማርያም እና ግብረ አበሮቹ ቢሆኑም ወይም ወያኔዎች መንግሥቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረታቸው ስጦታ ቢሆኑም ኢሳያስ ለዚያ ምርኩዛቸው ነው ። ኢሳያስ የወያኔዎችን ጭንቅላት ኮትኳችም (mentor or the brainchild) ስለነበረ ፣ መንግግሥቱን ከዙፏኑ አባረው የአ/አበባን ቤተጥፋት ከተረከቡ በኋላ ወያኔዎች ኢትዮጵያን ለመቶ ዓመታት እንደሚገዙና እየገዙ ፦ እንዲያሽመደምዱ፣ እንድያዳክሙና እንዲበታትኑ ምክር የሰጠ ሰው ነው ። ‘ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰጥቼያቼአለሁ’ ብሎ በይፋ መፎከሩ ለዚህ ማስረጃ ነው ።
የሂትለርን (The Aryan race ) ሞዴል/ናሙና በመከተል የሌሎች ብሄር ብሄሰብ ተወላጅ ሚስቶች የነበርዋቸውን ኤርትራውያን ባሎች ሚስቶቻቸውን ኤርትራዊያት ባለመሆናቸው ብቻ ከልጆቻቸ ተነጥሎ እንዲባረሩ መመርያ ያወጣ ሌላው ሂትለር ፤ሌላ አካል ሰንጣቂ ፋሽስትአ ነው።
እ.ኤ.አ በ 1991 ኤርትራና ሁለቱ የቀይ ባህር በሮቻችን ሙሉ በሙሉ በኤሳያስ እጅ ከወደቁ በኋላ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ፤ ትጥቃቸውን ፈትተው ለሻቢያ ሠራዊት እጅ መስጠታቸ ውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል። የተባበሩት መንግሥታት የጦር እስረኛ/ኞች (prisoners of war) ሕግና የሰብአዊ መብት አንቀጽ 5 (Article5: No one shall be subjected to torture or to cruel, inhuman or degrading treatment or punishment) በማንም ሰው ላይ ሶቆቃ ወይም ጭካኔ ወይም ኢ–ሰብአዊ ወይም ስብዕናን ዝቅ የሚያደርግ ድርጊት ወይም ቅጣት መፈጸም የለበትም እንደማለት ይመስለኛል።
ከላይ የጠቀስኳቸውን ዓለም አቀፋዊ ሕጎች በመጻረር ወይም በመናቅ፤ ከፊሎቹ ባስረከቡትን መሳርያና ጥይት ወዲያውኑም ሲረሸኗቸው ከፊሎቹ ወደ በርሃ ወስደው የጉልበት ሥራ ሲያሰርዋቸው ፦ ምግብ፣ውሃና ህክምና በማጣት ማቅውና ተሰቃይተው መሞታቸውን ተነግሯል/ታውቋል።
ከድኽረ ኢትዮጵያን ቅርመታም በኋላ ኢሳያስና ወያኔዎች የተጣሉ ቢመስሉም ፣ የአንድ ሳንቲም ፊትና ኋላ እንደነበሩ ሳይገባቸው፣ በእዋህነት በኢሳያስ አጋዥነት ታግለውና ተዋግተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ ቀንበር ለማላቀቅ አልሞ ወደ አስመራ የተጓዙትን በርካታ ሃቀኛ ፀረ ወያኔ ተቃዋሚዮች ፤ ከፊሎችን ቀጥታ በመግደል ግማሾቹን እንደ ናዚዮች አስሮ ከባድ የጉልበት ሥራ በማሰራት አማቅቆና አመንምኖ በመግደል፤ በቤርሙዳ ትሪያንግል ሰምጠው እንደቀሩ መርከቦችና አይሮፕላኖች ሆነው ቀሩ ።
አብይ አህመድ የኢትዮጵያ የስልጣን ማማ ከጨበጡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት፦ በፀረ ኢትዮጵያና በፀረ–የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት መርህ ተሰልፈው ለረዥም ዓመታት ላይና ታች ሲኳትኑ የነበሩ፣ ስለኢትዮጵያና ሕዝቧ አንድነት ሲነሳ፣ ምን አንድ ያደርገናል ? በማለት የአሉታ ጥያቄ ሲያነሱና ፀረ–አንድነቶቹን ሲኮተኩቱ የነበሩ፣ ኢሳያስን ሲያሽሞነሙኑ የነበሩ ፣ባጠቃላይ በልፍስፍስ ኢትዮጵያዊነት አቋም እና በፀረ– ኢትዮ ጵያ መርህና ድርጊት ፤ ኢሳያስ የሚፈልገውን ሲፈጽሙና ለኢሳያስ ሲላላኩ የነበሩ ናቸው።
በመሆኑም ላለፉት ሰልሳ ዓመታት የአገራችን ነቀርሳ ከሆኑት እንዲሁም ላለፉት ስላሳ ዓመታት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለገጠማቸው ዘርፈ ብዙ ቀውሶች ምክንያቶች አንዱ ኢሳያስ ነው ።
ከላይ ለማሳየት የሞከርኳቸውን ኩነቶች /ድርጊቶች ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ተቆራኝተው የኖሩና በዚያ ውስጥ ያለፉትን ኢትዮጵያውያን ጠንቅቀው የሚያውቋቸውና በተለያዩ ፀሃፊዮች የተነግሩ ሃቆች መሆናቸው ባውቅም ፤ አንድም እንዲተወሱ ሁለትም በዚህ አርእስት ማስተላለፍ ከምፈልገው መልዕክት ጋር ስለሚዛመዱ ለንጽጽ ር ፈለኳቸው ። ስለሆነም የዚህ ጽሁፍ አርእስት ዋና መልዕክት ከዚህ ይቀጥላል።
ኢሳያስ አዲስ አበባ፣ባህር ዳርና ጎንደር ሲጎበኝ የተደረገለትን አቀባበል ሳስበው ያመኛል።በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ከላይ የጠቀስኳቸውና ያልጠቀስኳቸው ዓይነት የከፋ ግፎች ሲፈጸመ ለኖረ ሰው የዚያን ዓይነት የእልልታና የፈንጠዝያ አቀባበል ይገባው ነበርን? (does he really deserve such thrilled reception or welcome) ። የተደረገለት አቀባበልና መስተንግዶ እንደ አንድ አጥፊያችን ሳይሆን፤ እንደ አንድ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ውለታ የዋለ ብርቅዬ ወንድማችን/ወዳጃችን የመጣልን ወይም እየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ከተማዎች የረገጠ ይመስል ነበር።
ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ መደረግ የነበረባቸው ሁለት በጣም አነስተኛ ቅድመ ሁኔታዎች ፦ (1) ኢሳያስ የኢትጵያን ሕዝብ ተማጾ ይቅርታ መጠየቅ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠይቆ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አውንታ ማግኘት
2) ላደረሰው ክህደትና የግፍ እሳት በትንሹም ቢሆን የሚያቀዘቅዝ ካሳ ለምሳሌ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቆመ መንግሥት ባልነበረን ወቅት ከተወሰዱ የባህር በሮቻችን አንዱ የአሰብ የባህር በራችን መመለስ ።
ያ ባልሆነበት ያንን ዓይነት ምንቀረሽ የአክብሮት አቀባበል እነዚያ ግዙፍ ግፎቹና ደባዎች፤ እስይ እንኳን አደረካቸው ማለት አይሆንምን? እንደ አንድ ሕዝብ የማሰብ ብቃታችን አይፈታተንምን?የዚያ ግፍ ጠባሳ ያለበት ትውልድ ሙተው አልቆ ይሆን? ወይስ ፋሽስቱ መንግሥቱና ባንዳው መለስ እንዳደረጉት ሕዝቡ ተገዶ ነው የወጣው?
ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ፣ የፍልስጤሞች ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ የእስራኤል ፕሬዝደንት የነበረው ናታ ኛሁ ፤ የፍልስጤሞችን ዋና ከተማ ‘ራማላህ’ እንዲጎብኝ ቢጋብዝ ኢትዮጵያውያንን ለኢሳያስ ያደረጉትን ዓይነት አቀባበል ያደርጉ ይሆን ? ከይጎዝላቪያ የመገንጠል ታሪካዊ መብት ቢኖራቸው እንኳን ባልመረጧቸው ገዢዮቻችውን ፈቃድ ብቻ – የኮሶቮን፣ የኩሬሺያን፣ የቦሲኒያን ወዘተርፈ መሪዮች ወደ ቤልግሬድ ቢሄዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢሳያስ ያደረጉትን ዓይነት አቀባበል ያገኙ ይሆን?
ኢሳያስ ያለቅድመ ሁኔታና ያለሕዝባዊ አውንታ ባልመረጥናቸው ገዢዮቻችን ተጋብዞ ስለመጣ ተቀባዮችና አስተናጋጆቹ ፦ የኢሕ አድግ ባልሥልጣናት ፣ውለታ የዋለላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ለምሳሌ (ኦነግና ግንቦት 7)፣ በእነዚህ ከተማዎች የሚኖሩ ኢሳያስን አፍቃሪ ኤርትራውያን ብቻ ዝቅባለ ደረጃ (low profile level) መሆን በተገባው ነበር።
ኢሳያስ በእነዚህ የአገራችን ከተማዎች የተደረገለት ጀግናዊነት የተላበሰ ወይም ሄረዊክ አቀባበል፤ በዓለም መንግሥታት፣ መሪዮችና ዲፕሎማቶች ከተረሳበት ወደ መኖሩን እንዲታወስ አሸጋግ ሮታል ። ኢሳያስ ወደ አ/አ ሲመጣ እና ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ወደ አስመራ ሲሄዱ ፤ግንኙነቱ ሕዝብ ለሕብ ለማቀራረብ የሚል ሽፋን ነው የተሰጠው ።
የኢሳያስ ዓይነት አምባገነን ገዢዮች ሕዝብ ለሕዝብ ያናክሳሉ እንጂ ሕዝብ ለሕዝብ የማገናኘት ስብዕና የላቸውም ። እውነተኛ/ኦርጋኒክ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚገኝው በዲሞክራሲያዊ መርህና አስራር ተመርጠው ሕዝብ በወከላቸው መሪዮች መሪነት ብቻ ነው። ያንን ሁኔታ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ስለሌለ ፣ የኤርትራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸውን ተቀላቅሎ መኖር ከፈለጉ በመጀመርያ ሰው በላው ኢሳያስ ማስወገድ። በመቀጠል ምሥራቅ ጀርመኖች እንዳደረጉት ማለት በእነሱና በምዕራቡ ጀርመን የተጋረደውን ግንብ እንዳፈራረሱ ፤በታንክ የታጠረው የኢትዮ–ኤርትራ ድንበር በአመጽ ማስከፈት ይኖርባቸዋል።
በእኔ ግምት ወደ ኢሳያስ አቤቱታ የተከደበት ምክንያቶች ሶስት ናቸው ፥ (1) አሜሪካን፣ፕ/ብርሃኑ ነጋን፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ኦነግን ለማስደስት (2) ከወያኔዎች ጋር መልሶ እንዳያብር (alliance) እንዳይፈጥር ከመፍራት (3) የወጪና የገቢይ ሸቀጦቻችን ማራገፌያ ወደብ እንዲያከራየን ለመለመን።
ኢሳያስ ከወያኔዎች ጋር መልሶ ይወዳጅ ይሆን? ምን ለማግኘት ወይም ምን ጥቅም በማሰብ? በትግራይ ከሚመረተው የህል ክምችት ለኤርትራን ሕዝብ ዳቦ ለማቅረብ? ከኢትዮጵያ ከዘረፉትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ከተበደሯቸው ብዙ ብሊየን ዶላርና ይሮ ክምችት ያካፍሉኛል ብሎ ከማሰብ? ወደ ትግራይ ተወስዶ ከተከማቸው የጦር መሳርያና ወታደራዊ ቁሳቁስ ያካፍሉኛል ብሎ ከማሰብ? በትግራይ ከተመረቱ የኤሌትሮኒክስ፣ የኮምኒኬሸን፣ የኢንዱስትሪ ፣የግብርና ወዘተርፈ ቴክኖሎጂዮች እጠቀማለሁ ብሎ ከማሰብ ? በጋራ ኢትዮጵያን ዳግም ውግተውና ወረው ሃብቷን ለመቀራመት በማሰብ? ለእኔ የማይታሰቡ የሩቅ ጭሆቶች ናቸው ። ለመላምንቶቹ አንባቢ የመሰለውን ሊል ይችላል።
ለግማሽ ምዕተ ዓመት ፥ ሕዝባዊ አንድነታችን ያናጉ፣ሃገራዊ ሉዓላዊነታችን የቆራረሱና ዳርድንበራችንን የደፈሩና ያስደፈሩ ፣ አገር በቀል የአፓርታይድ ሥርዓት የዘርጉ ፣የገፍ የጅምላና የተናጥል ግድያ፣ መከራ፣ ሰቆቃ፣ የገፍ እስር፣ የገፍ መፈናቀል፣ ቀውስ፣ ሽብር ባጠቃላይ መሪር ሃዘንና ቁጣ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ ስላሰፈኑ ሦስቱ ነቀርሳዎች ስለ (መንግሥቱ ሃ/ማ ፣መለስ ዜናዊ እና ኢሳያስ አፈጨርቂ) በየቀኑ ተጽፎ ባይ ደስ ይለኛል ። ምክንያቱም (1) በነዚያ ጨለማ ሥርዓቶች ውስጥ ያለፈን ትውልድ በሙሉ ሙቶ አፈር እስኪለብስ ፤ እነዚያ በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግሩ ግፎች እንዲያስታውሳቸው (2) መንግሥቱ ሃ/ማ በዋናነት ወጣቱና የተማረውን ዜጋ በመመንጠር ኢትዮጵያን ሲያፈርስና ሲያዳክም፤ በጨቅላ ዕድሜ ከነበረው ትውልድ እስካሁን ያለው ትውልድ ስለሶስቱ የኢትዮጵያና ሕዝቧ ነቀርሳዎች ጥፋት/ካርኔጅ ጠንቅቆ አውቆ ለነገው ትውልድ እንዲያስተላልፍ (3) መንግሥቱ ጀግናና አገር ወዳድ እንደሆነ አሁንም በካድሬዎቹ የሚነዙ ፕሮፓጋንዳዎች ፤ፍጹም ውሸትና ተረት ተረት እንደሆነ ይህ ትውልድ እንዲውቅ። ሕዝቡን ጨፍጭፎ አገር ወዳድ መሪ ማለት ልጆቿን ገላ ጥሩ እናት ወይም ምዕምናን አስጨርሶ ጥሩ ቄስ ወይም በጎችን በቀበሮች አስበልቶ ጥሩ እረኛ ወዘተርፈ እንደማለት አይሆንምን?