…በደቡብ ክልል ቴፒ ከተማ ሰሞኑን የጸጥታ መደፍረስ አጋጥሞ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል።

የመዋቅር አደረጃጀት ጥያቄን መሠረት አድርጎ አለመረጋጋት ውስጥ በነበረችው ቴፒ ከተማ፤ ጥር 26/2012 .ም የልዩ ኃይል አባል መገደላቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ 8 ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

አንድ ስሙን የማንጠቅሰው የቴፒ ከተማ ነዋሪ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በተከሰተው ግጭት 8 ሰዎች መሞታቸውን እና ቢያንስ 12 የሚሆኑ ነዋሪዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ይናገራል።

ፋና ብሮድካስቲንግ የደቡብ ክልል የፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮን ጠቅሶ ባለፉት 2 ሳምንታት ቴፒ ከተማን ጨምሮ በተፈጠረው ግጭት የ7 ሰዎች ሕይወት አልፏል ሲል ዘግቧል።

ሌላኛው የቴፒ ነዋሪ ደግሞ ለቢቢሲ እንደተናገረው ረቡዕ ዕለት ለተፈጠረው ችግር ዋነኛ መንስዔው ከአንድ ወር በፊት በአካባቢው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ነውይላል።

ከአንድ ወር በፊት 1 ልጅ በአካባቢው ተገድሏል። ይህንን ተከትሎ በቴፒ የአገልግሎት ተቋማትና መንገዶች ለ21 ቀናት ተዘጋግተው ነበርየሚለው ይህ የቴፒ ነዋሪ ረቡዕ ዕለት ግን የተዘጉት አገልግሎቶች እንደ አዲስ ተከፍተው ሰውም ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው መግባት ጀምሮ ነበር።

ነገር ግን ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ የአካባቢው የልዩ ኃይል አዛዥና አንድ ሌላ የልዩ ኃይል አባል ወደ አንድ ምግብ ቤት በማምራት፤ ምግብ በመመገብ ላይ የነበረን ወጣት ትፈለጋለህበማለት ይጠሩታል።

በዚህ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ልጁ ሲቪል ወደ ለበሰው የልዩ ኃይል አዛዥ በማምራት በስለት ወግቶት ሸሸቶ አመለጠበማለት የግጭቱን መነሻ ያስረዳሉ።

በስለት የተወጋው ጸጥታ አስከባሪ ኃይል አባል ሕይወቱ ማለፉን እና ከዚያ በኋላ በተወሰደ እርምጃ የተቀሩት ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና ሰዎች መቁሰላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የሸካ ዞን ፕሬስ ሴክሬታሪያት አቶ አስማማው ኃይሉ ለቢቢሲ ሟች የሃምሳ አለቃ ዘማች ቁንሲል መሆናቸውን እና በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በጥይት ተመትተው ተግድለዋል ብለዋል።

እንደ ፕሬስ ሴክሬታሪያቱ ከሆነ የሃምሳ አለቃው የተገደሉት ቆጫ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አደባባይ ላይ ነው።

ጸጥታ አስከባሪ ሲገደሉ የተኩስ ልውውጥ እንደነበረም አስረድተዋል።

አቶ አስማማው ጭመረው እንደተናገሩት፤ ክልሉ የመዋቅር ጥያቄን እንሁን ላይ አልቀበልም ብሎ ምላሽ ሰጥቶ እንደነበረ ተናግረዋል።

የዞን አስተዳደር ጥያቄያችን ይመለስልንየሚለው የነዋሪው ጥያቄ ለጸጥታ መደፍረስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ጥያቄው ለዓመታት የዘለቀ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ በቴፒ ወረዳ ዙሪያ ያሉትን 22 ቀበሌዎች ጨምሮ የአስተዳደር መዋቅሩ ወደ ዞን ከፍ እንዲል የነዋሪዎች ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቅርብ ወራት በፊትም የሰላም ሚንስትሯና የክልሉ ገዥ ፓርቲ ሊቀ መንበር በሥፍራው ተገኝተው ከሕዝቡ ጋር ተወያይተው ምላሽ እንደሚሰጥበት ቃል ገብተው ቢሄዱም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የደቡብ ክልል የጸጥታና አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ እስካሁን 68 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው የተወሰኑት ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት በማድረግ እርቅ ፈጽመው መለቀቃቸውን የተቀሩት ደግሞ ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑን ለፋና ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአከባቢው ያለው የጸጥታ ስጋት ተከትሎ የጤና ባለሙያዎች፣ የባንክ ሰራተኞች እና ነጋዴዎች የመሳሰሉ ሠራተኞች አከባቢውን ጥለው እየሸሹ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።